ሀይማኖት እና ፖለቲካ ከትላንት እስከ ዛሬ!

0
1838

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችና የተለያዩ ክስተቶች፣ ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ያላቸውንና የነበራቸውን በጎ ግንዛቤ ጥርጣሬ ውስጥ የከተተ ነው። ይልቁንም ሀይማኖትን ‹መሠረት አድርገው› የተነሱ ግጭቶች፣ ‹ሀይማኖተኛ ነን የምንለው እንዲህ ሆነን ነው?› ብለው ብዙዎች እንዲጠይቁ ግድ ብሏል። የእምነት ቤቶች ተቃጥለዋል፣ አማኞች በሀይማኖታቸው የተነሳ ተገድለዋል። ይህ በኢትዮጵያ የታየ መራራ እውነት ሆኗል።

ብዙዎች ሕዝቡ በሰላም እየኖረ ነው፣ ችግር የሚፈጠረው ፖለቲካው ጣልቃ ሲገባ ነው የሚል ዕይታ አላቸው። ፖለቲካው ይልቁንም መንግሥት ሀይማኖቶችን ለራሱ ጥቅም እያዋለ ነው የሚሉ ቅሬታዎችም ይሰማሉ። በሌላ በኩል ሀይማኖትም የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እጁን እያስገባ ነው፣ ፖለቲካዊ ኃይልን የማግኘት ምኞት አለው የሚል እይታም አለ።

ሀይማኖትና ፖለቲካ ምን እና ምን ናቸው? አብረው መሄድ ይችላሉ ወይም የግድ አንዱ የሌላው የበላይ መሆን አለበት? በኹለቱ መካከል ልዩነት ሲፈጠርስ ምን ሊደረግ ይገባል? ጥናቶችና ምሁራን በዚህ ላይ ምን ይላሉ? የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት የተለያዩ ጥናቶችን በማጣቀስ የፖለቲካ ሳይንስ ባለሞያን በማናገርጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕስ አድርጋዋለች።

‹የመሬቱ እውነት›
ለማነጻጸሪያነት በሚበቃ መጠን የሌሎች አገራትን ልምድ ጠልቆ መመልከት ባይቻልም፣ እንደ ኢትዮጵያ የሀይማኖት ብዝኀነትን ከነውበቱ የያዘ አገር አለ ለማለት ያዳግታል። አዎን! ብዝኀ ሀይማኖት ያለባቸው አገራት እንዳሉ እሙን ነው። ነገር ግን ያንን ልዩነት በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ፣ በትዳር ተሳስረው፣ ‹አንቺም በሀይማኖትሽ እኔም በሀይማኖቴ› ብለው የተጣመሩ ወይም ቤተ እምነታቸውን በአጥር ብቻ ለይተው ተጎራብተው የሚኖሩ ሕዝቦች መገኛ አገራት ብዙ አይደሉም። ጥቂት ናቸው ለመባልም ያንሳሉ። ለዛም ነው ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ልዩ የምትባለው።

‹‹ባለቤቴ የክርስትና እምነት ተከታይ ኦርቶዶክስ ነበር። እኔ ደግሞ እስልምና ነው ሀይማኖቴ። ልጆቻችን ነፍስ ካወቁ በኋላ ከኹለታችን የፈለጉትን ሀይማኖት መርጠው ይከተላሉ። እኔ ልዩነታችን ትዝ ብሎኝ አያውቅም። እኔም የእሱን አከብራለሁ፣ እሱም የእኔን ያከብራል። ቤታችን የሕዝብ ከሆኑት በዓላት በተጨማሪ የኹለቱም ሀይማኖቶች በዓላት ይከበራሉ። ከዛ ውጪ ትዳር፣ ሕይወትና ፍቅር አንድ አድርጎን ነው የምንኖረው።›› ያሉት የአራት ልጆች እናት ፎዚያ አወል ናቸው።
ኑሮአቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት ፎዚያ፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ከሆነው ባለቤታቸው ጋር ለሥራ ከቦታ ቦታ ብዙ ይንቀሳቀሱ እንደነበር ያስታውሳሉ።

‹‹ብዙ እንንቀሳቀስ ነበር። ሰዎችም እኔና ባለቤቴ የተለያየ ሀይማኖት እንዳለን ሲያውቁ አዲስ አይሆንባቸውም። ግን ‹ቤተሰቦቻችሁስ ተስማምተዋል ወይ?› ብለው ይጠይቁኛል። አዎን ስላቸው ዋናው ፍቅር ነው ብለው ይመርቃሉ። አንዳንዶች ቅር የሚሰኙም አሉ። ያም ግን ልጆቻችሁ እንዴት ሊሆኑ ነው [በየትኛው ሀይማኖት ያድጋሉ] ከሚል ስጋት ነው። ፈጣሪ ግን አላሳፈረንም፣ መልካም ጠባይ ያላቸው አስተዋይ ልጆችን ሰጥቶናል።›› ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ በአንድ አነስተኛ የንግድ መደብር ውስጥ ያገኘቻቸው እኚህ እናት፣ በኢትዮጵያ እየሆነ ባለው ነገር በእጅጉ መከፋታቸውን አልደበቁም። የበለጠውን ያዘኑትና የተከፉት ደግሞ በፖለቲከኞችና በመሪዎች እንደሆነ ጠቅሰዋል።
‹‹በጣም ያሳዝናል። የትኛውም ሀይማኖት ጥፋትን አያስተምርም። ችግር የተፈጠረው በፖለቲካው ነው። ፖለቲከኞች ለምን ራሳቸውን ችለው እንደማይንቀሳቀሱ አላውቅም። አላህ ይህን ክፉ ጊዜ አሻግሮን ለልጆቼና ወደፊት ለማያቸው የልጅ ልጆቼ የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ እመኛለሁ።›› በማለት ነበር የተረዱትን የተናገሩት።

እንደ ፎዚያ ያሉ ብዙ ሰዎች አሉ። አዲስ ማለዳ በአጋጣሚ ባለትዳር የሆኑ ባለታሪኮችን አገኘች እንጂ፣ በጉርብትና፣ በጓደኝነት፣ በጋብቻ ዝምድና፣ በአብሮ አደግነት ወዘተ የተዛመዱ ሰዎችን መጥቀስ የኢትዮጵያን ሕዝብን የመቁጠር ያህል እንደሆነ የታወቀ ነው። ታድያ ማኅበረሰቡ እንዲህ ያለ አኗኗር ያለው ከሆነና መሬት ላይ ያለው እውነትም ይህ ከሆነ፣ በእርግጥ ፖለቲካ በሀይማኖት ጣልቃ እየገባ ነው ማለት ነው? ፖለቲካና ሀይማኖትስ ምንና ምን ነበሩ፣ ምንና ምንስ ናቸው?

ፖለቲካና ሀይማኖት፡ ምን እና ምን ናቸው
ውሂበእግዜር ፈረደ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። የእምነት ተቋም እና አገረ መንግሥት ወይም በዚህ አውድ ሀይማኖት እና ፖለቲካ፣ ሕዝብ የጋራቸው እንደሆነ በማስታወስ ጀመሩ።
በዓለም ታሪክ ሂደት የአገረ መንግሥት አመሠራረት ከቤተ እምነት ውስጥ ነበር ሲሉ ቀጠሉ፡፡ በተለይም የፊውዳል ስርአት በነበረባቸው አገራት ይህ ይስተዋል ነበር። በዛም ብቻ አይደለም፣ በአውሮፓ ሳይቀር የካቶሊክ ቤተክርስትያን ፖለቲካውን ይመራው እንደነበርም ጠቅሰዋል።
‹‹በሕዝቡ ዘንድ ለረጅም ጊዜ መሪ ወይም ገዢ ከላይ [ከሰማይ] ነው እንጂ ምድራዊ ኃይል ገዢ መሪ መሆን አይችልም የሚል አሳቤ ነበር፡፡›› ያሉት ውሂበእግዜር፥ ከዛ በኋላ ቀስ በቀስ የሴኩላሪዝም ጽንሰ ሐሳብ፣ በተለይም የማርክሲስት ሐሳብ ሲመጣ ዕይታዎች ተቀይረዋል። በዚህ መሠረት የሰማዩና የምድሩ መንግሥት የተለያዩ ናቸው። ሰማያዊውን የሚመራ ሀይማኖታዊ ሕግ አለ፥ ሕዝቡን የሚመራ ደግሞ መንግሥት የሚባል ተቋም አለ የሚል መረዳት ላይ መደረሱን አውስተዋል።

ከዚህ በኋላም ኹለቱ የተለያዩ ተቋማት ናቸውና አንዱ በሌላው ጣልቃ አይገባም የሚል ደረጃ ላይ ተደረሰ። ነገር ግን እነዚህ ኹለት ግዙፍ ተቋማት አሁንም በመካከላቸው ያለና የጋራቸው የሆነ ሕዝብ አለ። ኹለቱም የሚያገለግሉት ይህን ሕዝብ ሲሆን፣ የሕዝብ ደኅንነት እና ሰላም የሚያሳስባቸው ጉዳያቸው ነው። ያም ሆኖ ግን በ‹ሴኩላሪዝም› ሲስማሙ፣ በመካከላቸው አንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ አይገባም የሚል ድንበር ፈጥረው በዛ ተዋስነዋል።
‹‹የሕዝብ ደኅንነት የጋራቸው ነው። ኹለቱም ይመለከታቸዋል፣ በዚህ ላይ በጋራ ይሠራሉ። ይህ ማለት ግን መንግሥት በእምነት ጉዳይ ጣልቃ ይገባል ማለት አይደለም።›› ሲሉ ውሂበእግዜር ያስረዳሉ።

ሆኖም ግን አሁንም ትግል አለ ብለዋል። የግል ዕይታቸውን ሲያጋሩም፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ያለውን ሙግት ጠቅሰዋል። ‹‹ፍትሃዊው የሚሆነውና ይህን ዓለም ማስተዳደር ያለበት ሰማያዊ ኃይል ነው ወይስ ምድራዊ ኃይል ነው የሚለው ክርክር ረጅም ጊዜ የቆየ ነው፣ አሁንም ያከራክራል።›› ብለዋል።

አሊ ሙባረክ ፓኪስታናዊ የታሪክ ተመራማሪና ምሁር ናቸው። ታሪክ ሲጻፍ አንጻሩ ከብዙኀኑ ሕዝብ የሚነሳ መሆን አለበት በሚል ዕይታቸው እና በዛ ቅኝት በጻፏቸው በርካታ መጽሐፍት እውቅናን አግኝተዋል። እኚህ ሰው ‹ሀይማኖት እና ፖለቲካ፤ ግንኙነት፣ ልዩነትና ግጭት› በሚል ርዕስ ባስነበቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ ሀይማኖትና ፖለቲካ እኔ ለቅደም፣ እኔ ልምራ ሲባባሉ የሚፈጥረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

እንደ አሊ ገለጻ፣ ሀይማኖት የፖለቲካ የበላይነቱን ካገኘ፣ ግቡ መለኮታዊ ስርዓትን ማስፈን ነው። እናም ሥልጣን ያገኘው በመለኮታዊ ኃይል መሆኑን በመግለጽ፣ ዓላማው ቅዱስ እንደሆነና ሕዝቡንም በመንፈሳዊ መርህ ነው መመራት ያለበት ይላል።
በአንጻሩ ፖለቲካ የበላይነትን ባገኘበት አውድ ደግሞ፣ ሕግ ይቀይራል፣ ፖሊሲና ስርዓት ይወጣል። በዚህም ፖለቲካው ‹የእኔ ግብ የማኅበረሰብ ፍላጎትና ጥያቄን ማሟላት ነው።› በማለት መመሪያውንም ከዓለም ስርአት አንጻር ይቀርጻል።
አሊ ከታሪክ ማህደር ተነስተው፣ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ጋር የተገናኙ ሦስት አካሄዶች አሉ ሲሉ ያስረዳሉ። ከእነዚህ መካከል አንደኛው ፖለቲካና ሀይማኖት በጋራ የሚሠሩበት ነው። በዚህም ኹለቱም ተባብረው የፖለቲካ ኃይልን ጠቅልለው ይይዛሉ።
በኹለተኛው ደግሞ ፖለቲካ የበላይነቱን የሚይዝበትና እንደውም ሃይማኖትን ለራሱ ጥቅም የሚያውልበት ነው። በሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ደግሞ በኹለቱ መካከል የሚፈጠር መለያየት ነው። በዚህም ኹለቱ አካላት እንደ ተቀናቃኝ ይሆናሉ።

ታድያ የታሪክ ተመራማሪው አሊ ይህን ነጥብ ሰብሰብ ሲያደርጉት፣ በሀይማኖትና በፖለቲካ መካከል ትስስር ሲፈጠር ፍጹም የሆነ አምባገነን ስርዓት ይፈጠራል ባይ ናቸው። በአንጻሩ ኹለቱ የተጋጩ እንደሆነ ደግሞ ኹለቱም ሰዎችንና ያላቸውን ሀብት በመጠቀም እርስ በእርስ ለመፎካከርና ኃይል ለማግኘት ይጥራሉ። በዚህም የተነሳ የሚጠቀሙበትን ሰው/ሕዝብ ከማኅበራዊ ሕይወት መስመር ያናጥቡታል።

ከኹለቱ በተለየ ግን ሀይማኖት በፖለቲካ ተጽእኖ ስር ሲወድቅ፣ ማኅበረሰብ ፍልስፍና፣ ሥነጽሑፍ እንዲሁም ሙዚቃ ላይ ያበረክታል ይላሉ። በእርሳቸው ዕይታ የሀይማኖት አቅም ሲቀንስ ወይም ገመዱ ላላ ሲል የሰዎች ነጻነት ይጨምራል።
ይህ በሌላ አገላለጽ ሀይማኖት ዘመን አመጣሽ የሆኑ እሳቤዎችንና አካሄዶችን የሚቀበል ባለመሆኑ ወይም ከብዙው የዴሞክራሲና መሰል ፖለቲካዊ ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ስለሚጋጭና አብዛኞቹንም ለመቀበል ስለሚቸገር፣ ከፖለቲካው ገለል እንዲል ይመከራል። እዚህ ላይ ውሂበእግዜር በበኩላቸው፣ በዓለማችን አሁንም ሀይማኖታዊ አገር የመገንባት ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የሀይማኖት ከፖለቲካ ተለይቶ መታየት አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ። ‹‹ያ መሆኑም ሀይማኖትን ተጋላጭና ደካማ አያደርገውም።›› የሚሉት አሊ ናቸው። እንደውም ከታሪክ መረዳት የሚቻለው ሀይማኖት በማንኛውም ጊዜ የፖለቲካን እርዳታ መጠየቅ ራሱ እንደሌለበት ነው ሲሉ በጥናታቸው ጠቅሰዋል። እርዳታን ከጠየቀ፣ ፖለቲካ ሀይማኖትን ሊጠቀምበት ያለምንም ማንገራገር እጁን እንደሚከት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።

ሰሎሞን ጌጡ የተባሉ ፀሐፊ የታሪክ ተመራማሪውን ሐሳብ የሚደግፉ ነጥቦችን ‹ሀይማኖት እና ፖለቲካ› በሚል ርዕስ ባስነበቡት አንድ ጽሑፍ አንስተዋል። ኹለቱ አካላት እንደ ተቋም ስላላቸው ግንኙነት በሚያስረዱበት በዚህ ጽሑፍ፣ ‹‹መቼም ቢሆን በየትኛውም አገርና ሕዝብ ውስጥ ሀይማኖትና ፖለቲካ ሳይገናኙ ለየቅል ተጉዘው አያውቁም፡፡›› ያሉት ጸሐፊው፣ የግንኙነቱ ዓይነትና ደረጃ ግን ሊለያይ እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

‹‹ሀይማኖትና ፖለቲካ ተጓዳኝ የሆነ የኹለትዮሽ ግንኙነት አላቸው። የመንግሥትና ሀይማኖት መለያየት የሚለው የዴሞክራሲ ስርአት መርሆ የሚገልጽልን በዴሞክራሲ ስርአት ውስጥ መንግሥታዊ ሀይማኖት እንደሌለና ግለሰቦች የፈለጉትን እምነት የመከተል መብት እንዳላቸው ነው። እንጂ ፖለቲካና ሀይማኖት የተለያዩ እንደሆኑ ማሳያ አይደለም።›› ሲሉ ይሞግታሉ።

በኢትዮጵያስ ለምን?
ኢትዮጵያ ውስጥም ‹ስዩመ እግዚአብሔር› ተብለው የሚመሩ እንደነበሩ፣ ከላይ ከፈጣሪ ተመርጠው፣ እርሱ የቀባቸው ቅቡዓን ብቻ ናቸው መምራት ያለባቸው የሚል እሳቤ እንዳለ ውሂበእግዜር ያነሳሉ። በሌላ በኩል ‹የለም! ይህ ምድራዊ ነው፣ የምድሩን ዴሞክራሲ በሚባል ስርዓት ነው መመራት ያለበት እንጂ ሰማያዊው ለምድሩ አስፈላጊ አይደለም› የሚል ክርክር አለ ብለዋል።

ሰሎሞን በበኩላቸው በጽሑፋቸው እንዳካተቱት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም በፊውዳሉ ስርአት ሀይማኖትና ፖለቲካ የአንድ ሳንቲም ኹለት ገጽታዎች ነበሩ ማለት ይቻላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እርሳቸውም ይህን ጽሑፍ ባስነበቡበት ዓመት (2012) የነበረውና ያለውን የሀይማኖትና ፖለቲካ ግንኙነት ታድያ፣ ‹‹እንዳለመታደል ሆኖ ተመጋጋቢ የሆነ ለሁለንተናዊ ሰላም የሚረዳ የተአቅቦ የሁለትዮሽ ግንኙነት ሳይሆን፤ የፖለቲካው ፍፁም የበላይነት ያለበትና የሀይማኖት ተቋማትን የሚደፈጥጥ ብሎም የሚበዘብዝ በመሆኑ እጅግ አደገኛና ማኅበረሰቡን እና አገሪቷን ውስብስብ ወደሆነ ማጥ ውስጥ ሊከት የሚችል ነው።›› ሲሉ ገልጸዉታል።

ይህ እየሆነ የነበረበትን/ያለበትን መንገድ ሲያስረዱ፤ አንደኛው ምክንያት የፖለቲካ ዓላማ ነው ይላሉ። ይህም የሀይማኖት ተቋማትና የሀይማኖት አባቶች ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም የመንግሥትን ፕሮፓጋንዳና እሳቤ በቀላሉ በሕዝብ ላይ ለመጫን እና ለማስረጽ ነው። ይህም ኹለት መንገድ አለው ሲሉ የተለያዩ ጥናቶችን ጠቅሰው እንዲህ ይቀጥላሉ፤

‹‹የመጀመሪያው ብራያን ተርነር ነው፤ በ2013 ባቀረበው ጥናት እንደጠቀሰው ከፊል ሴኩላራይዜሽን (Partial Secularization) የሚባል ያለ ሲሆን፤ ይህ ማለት መንግሥት በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት እንቅፋት ይሆኑኛል የሚላቸውን አስተሳሰቦችን/አስተምህሮዎችን የሚያጠፋበትና በአዲስ የሚያዘምንበት መንገድ ነው። ኹለተኛው መንገድ ደግሞ በሰራዊት በቀለ ጥናት ላይ እንደሰፈረው (2018) መንግሥት በእጅ አዙር የሀይማኖት ተቋሙን የሚቆጣጠርበት እና የኔ የሚላቸውን ግለሰቦች/ የሀይማኖት አባቶች በመሾም የፈለገውን የሚፈጽምበት እና ጣልቃ የሚገባበት መንገድ ነው።›› ብለዋል።

አሁን በኢትዮጵያ ምን እየሆነ ነው?
ከአራት ዓመታት ገደማ ወዲህ በኢትዮጵያ አጀንዳ ሆነው ግጭት ከሚነሳባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ለሰዎች ስሜት ቅርብ የሆኑ የሀይማኖት እና የብሔር ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው። በቅርቡም በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ችግር ተከትሎ፣ ከዛም ተሻግሮ ወራቤ ደርሶ በርካቶች ሞተዋል፣ ቤተ እምነቶችም ተቃጥለዋል፣ ፈርሰዋል።

በመግቢያችን እንዳነሳናቸው ባለታሪካችን ፎዚያ ሁሉ፣ እነዚህ ሁሉ ጥፋቶች የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ውጤት ናቸው በሚለው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ውሂበእግዜር ይስማማሉ። ‹‹[ክስተቱ] የሀይማኖት ግጭት አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሀይማኖት ግጭት ሳይሆን ሀይማኖትን እንደ መሣሪያ የሚጠቀም የፖለቲካ ዓላማ ያለው ግጭት ነው።›› ሲሉም ገልጸውታል።

እንደውም ኢትዮጵያ የሀይማኖት መቻቻል ያለባት ብቸኛ አገር ናት ያሉ ሲሆን፣ የአብርሀም ነን የሚሉትን ኹለቱን ትልልቅ ሀይማኖቶች ማለትም ክርስትና እና እስልምና የያዘች፣ የእነዚህ ተቋማት ግንኙነትም የተገነባባት፣ የመጀመሪያው ሂጅራ የተካሄደባት፣ ክርስትናም ቀድሞ የመጣባት አገር ናት ሲሉ ዘርዝረዋል፡፡

‹‹ቀደምት የሚባሉት የሀይማኖት ተቋማት ለዘመናት የቆዩባት አገር ላይ ሀይማኖታዊ ግጭት አለ ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። ሀይማኖቶቹን የሚጠቀሙ የፖለቲካ ኃይሎች ናቸው ያስቸገሩት።›› በማለት ዕይታቸውን አጋርተዋል።
ነባራዊውን የኢትዮጵያን ሁኔታም አያይዘው አንስተዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም በብዙ መልኩ የመንግሥት የማስፈጸም አቅም አለ እየተባለ የሚወራው ከወሬ የዘለለ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ ይልቁንም ማንኛውም ሰው በኢትዮጵያ ባመነበት የማምለክ መብቱ ግን የተከበረ እንደሆነና፣ አንዱ በሌላው መብት ጣልቃ እንደማይገባና የየእምነቱን ስርአት ሲፈጽም ሌላውን በሚነካ መንገድ መሆን እንደሌለበትም ገልጸዋል። በአሁኑ ሰዓት ያለውንም ችግር እንደሚከትለው በግልጽ አስቀምጠዋል።

‹‹አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው ከዚህ በፊት ተጨቁኛለሁ፣ ከባድ ችግር ነበረብኝ፣ ሀይማኖታዊ ቦታ አልነበረኝም የሚል የፕሮቴስታንት ትርክት አለ። ያም በአገሪቱ እንቅስቃሴ ውሰጥ ገናና ሆኜ መታየት አለብኝ የሚል እንቅስቃሴ በጣም አደገኛ ነው፣ ትክክልም አይደለም። መታረም አለበት። ሁሉም የራሱ ቦታ አለው፤ በራሱ የአምልኮ ሁኔታ መንቀሳቀስ ይችላል፡፡ ይህን ወደ መንግሥታዊ ስርዓት ለመቀየር የሚደረግ እንቅስቃሴ አገሪቱን አደጋ ላይ ይጥላል።

በሌላ በኩል ከሱዳን የሚነሳው ‹እስላሚክ ወንድማማችነት› አራምጅ አለ። በሀይማኖታዊ እንቅስቃሴ የፖለቲካ ሥልጣን እቆናጠጣለሁ የሚል ይህ አክራሪ እስላማዊ እንቅስቃሴም ለአገሪቱ አደጋ ነው፡፡ በተጨማሪ ደግሞ አገሪቱ ውስጥ ነባርና ብቸኛ እኔ ነኝ፤ ከእኔ ውጪ ሌላ መደረግ የለበትም የሚል የኦርቶዶክስ አክራሪ እንቅስቃሴም አደገኛ ነው።›› ሲሉ አስቀምጠዋል።

ለፊቱ <ሀይማኖት የግል አገር የጋራ>
እንደ ውሂበእግዜር ገለጻ፣ ኢትዮጵያ መመራት ያለባት፤ ሁሉን አካታች በሆነ መንገድ ‹አገር የጋራ ሀይማኖት የግል› በሚለው በቆየውና ነባሩ መርህ ነው። የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችም ሥልጣን ላይ ስላሉ የእምነት ተቋማትን እያፈረሱ፣ ደግሞም ሁሉንም እያፈረስን እንደ አዲስ እንሠራለን የሚለው እንቅስቃሴ አደገኛ ነው ብለዋል። አደጋ የሚመነጨው/የመነጨው ከዚህ ነው ብለውም ያምናሉ። ከምንም በላይ ግን እንደ ሕዝብም፣ እንደ መንግሥትም ከሶሪያ መማር እንደሚገባ መክረዋል።

የሶሪያ ዜጎች ከአገራቸው ወጥተው አሁን እኛ ጋር እየለመኑ ነው። ይህን የሚፈልግ ሰው የለም። ስለዚህ እምነት የግል ነው፤ አገር የጋራ ነው። የጋራ አገራችንን ወደ ልማትና ወደ ሰላም የመምራት የጋራ ርዕይ አለን፤ ታላቅ አገር እንድትሆንልን እንፈልጋለን። በእምነታችን ደግሞ ማንም ጣልቃ ሳይገባብን መቀጠል እንችላለን ብለዋል።

አንዱ በሌላው ጣልቃ የሚገባበት ወይም የፖለቲካ ሥልጣን የያዙና የሀይማኖት ዝንባሌ (አፊሊዬሽን) ያላቸው ሰዎች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው በተቋማት የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት ማቆም መቻል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በሌላ መንገድ ሕዝቡ በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንዱ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ያለው ሀይማኖት መሆኑን ማወቅ አለበትም ብለዋል።

‹‹ሕዝቡ አገሪቱ ውስጥ ያልጠራ የፖለቲካ ትግል እየተደረገ መሆኑን ማወቅ አለበት። ለዚህም የፖለቲካ ኃይሎች እምነትን ወይም ሀይማኖትን እና ብሔርን የመሳሰሉትን ስሱ የሆኑ ነገሮች ለፖለቲካ ቅስቀሳና ትርምስ ለመፍጠር እንደሚጠቀሙት ተረድቶ፣ እያንዳንዱ ሰው በተረጋጋ መንገድ ያለውን ሁኔታ መረዳት አለበት።›› በማለት ውሂበእግዜር መልእክትም አስተላልፈዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here