የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ማኅበር በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ግልጽና ኅቡዕ ጥቃቶች እንዲቆሙ ሲል አሳሰበ።
ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ መንግሥት ጋዜጠኞች ሥራቸውን በማከናወናቸው ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግበትን ምስጢራዊ አሠራሩን ሊፈትሽ ይገባል ብሏል። እንዲህ ያለው ድርጊት ለመንግሥትም ሆነ በጠቅላላው ለአገር የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ይልቁንም መንግሥት እዘረጋዋለሁ ብሎ ከሚያምነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማኅበር ውጥኑ የሚቃረን መሆኑንም ማስታወስ እንደሚገባ ጠቅሷል።
ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ከሚሠሩበት ቦታ ወይም መኖሪያ ቤታቸው ያለፍርድ ቤት ማዘዣ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል ታፍነው የሚወሰዱበትና ደብዛቸው እንዲጠፋ የሚደረግበት ሁኔታ መደጋገሙ በኢትዮጵያ የፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱ በራሱ የመገናኛ ብዙኃን ስጋት እንዲሆን አድርጎታል ሲል በመግለጫው ስጋቱንም አስታውቋል።
‹ጋዜጠኛን ከሕግ ውጭ ሰውሮ ማቆየት ይቁም!› ያለው ማኅበሩ፣ አክሎም ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከቀናት በፊት ማንነታቸውን ባልገለጹ የመንግሥት ሰዎች ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ውስጥ ተይዞ መወሰዱንና የት እንዳለ አለመታወቁን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ መልስ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጿል።
ጋዜጠኛው በምን ጥፋት ተጠርጥሮ እንደተያዘና ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ካለመነገሩ በላይ የት እንደሚገኝ አለመታወቁ፤ ከዚህ ቀደምም ማኅበሩ ሲቃወመው የቆየው በሌሎች ጋዜጠኞችም ላይ የደረሰው መሰል ድርጊት አካል ሆኖ እንዳገኘውም ጠቅሷል።
‹‹በተለይ የማኅበራችን መሥራች አባል የሆነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ታፍኖ ተወስዶ እንዲሰወር የተደረገው የዓለማችን የፕሬስ ነጻነት ሳምንት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ መንግሥት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኀን ላይ ጥቃት እንደከፈተ ያስቆጥረዋል። ለጊዜው ከሕግ አግባብ ውጭ መንግሥትና በመንግሥት ሥም የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሱት ጥቃት የሕዝብ ዐይንና ጆሮ የሆነውን ሚዲያ ሊያሸማቅቀው ቢችልም፤ ውሎ አድሮ ራሱ መንግሥትን ዋጋ የሚያስከፍለው መሆኑን መዘንጋት የለበትም።›› ሲልም ማኅበሩ አሳስቧል።
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ያጠፋው ጥፋት ቢኖር እንኳን የፍትሕ አካላት እንደማንኛውም ተጠርጣሪ በሕግ ቁጥጥር ሥር ሊውልና ዳኝነት ሊሰጠው ይገባ ነበር። ነገር ግን ከተያዘበት ቀን ጀምሮ የት እንደሚገኝ እንኳን ሳይገለጽ ቀናትን ማሳለፉ የመብት ጥሰት ብቻ ሳይሆን መንግሥት ይህን ያልተገባና አደገኛ አዝማሚያ በጋዜጠኞች ላይ ማድረሱን እንደመብት እየቆጠረው እንደሚመስል ነው ማኅበሩ በመግለጫው የጠቀሰው።
ማኀበሩ ከዚህ ቀደምም የጋዜጠኞች በተደጋጋሚ እየታሰሩ መፈታት እየተባባሰ መሆኑን ማሳወቁ ይታወሳል። ይልቁንም የካቲት 8/2014 ባወጣው ዘገባ፣ በኢትዮጵያ የፕሬስ ነጻነት መሻሻሎች እየታየበት የነበረ ቢሆንም ለማሳያነት በ11 የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች ላይ የደረሱ እስራቶችን ጠቅሶ ዳግም እየተሸረሸረ ነው ብሎ ነበር።
በኢትዮጵያ ዘንድሮ የፕሬስ ነጻነት ቀን ለ31ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል።
ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014



