የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እና ጤና

0
2134

የአደገኛ ዕፅና መድኃኒቶች ተጠቃሚነት ወይም የአደንዛዥ እፅ ሱስ አንድ ሰው ራሱን መቆጣጠር እስኪያቅተው ድረስ የሱስ አምጭ ንጥረ ገሮችን ለመውሰድ ፍላጎት ሲያድርበት እና ችግር የሚያስከትል እንደሆነ እያወቀ እነዚህን ንጥረ ነገሮች ሲወስድ ነው ይላል፤ በአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገጽ ላይ ያገኘነው ጽሑፍ። ይህም ተጠቃሚው የተለየ ጸባይ እንዲያሳይ፣ ማኅበራዊ ሕይወቱና ግንኙነቶቹ እንዲቃወሱ፣ ውስጣዊም ውጪአዊም ሰላምን በመንሳት እንዲረበሽ ያደርጋል።

ዶክተር ጃራ ሰማ በዚህ ላይ ከራሳቸው ሕይወት በመነሳት ለብዙዎች ልምዳቸውን ያካፍላሉ። እንዲህ ነው፤ ከአራት ዓመታት በፊት የኩላሊት ሕመም እና የመኪና አደጋ አጋጠማቸው። ይህንንም ሕመም ለማስታገስና ለመቋቋም በሐኪም መድኃኒት ይታዘዝላቸዋል። ያንንም ሕክምናው እስኪጠናቀቅ ድረስ በየእለቱ እንዲወስዱ ይባላሉ፤ የተባሉትን ይተገብራሉ።

ከተወሰኑ ወራት በኋላ የሕክምና ክትትላቸውን ጨርሰው መድኃኒቱን ማቆም እንደሚችሉና ማቆም እንዳለባቸው ተነገራቸው። ነገር ግን አልሆነም፤ ጤናቸው ቢመለስም ይወስዱት ከነበረው መድኃኒት ጋር መላቀቅ አልቻሉም፤ የመድኃኒቱ ሱሰኛ ሆኑ።
‹‹ያ ያደረሰብኝ ጣጣ በቤተሰብ፣ በሥራዬ በድርጅቴ ላይ ከባድ ፈተና አስከትሎብኛል፤ በራሴ ዐይቼዋለሁ። እኔ በአንዱ መድኃኒት እንዲህ የሆንኩኝ ወጣቶችና የብዙ የተለያዩ ዕፆች ሱሰኛ የሆኑት እንዴት ይሆናሉ የሚለው ያሳስበኝ ነበር።›› ሲሉ ይናገራሉ።

ዶክተር ጃራ ሰማ በአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እና ሱሰኝነት ይልቁንም በወጣቶች ሕይወት ዙሪያ ሥራዬ ብለው እየሠሩ ነው። ‹ከሱስና ሱሰኝነት የመንጻት ጥበብ› የተሰኘ መጽሐፍም አዘጋጅተው ለንባብ አድርሰዋል። በየተገኙበት ድምጻቸውን ከማሰማት ወደኋላ አይሉም።
ዓለማችን ዛሬ ድረስ እየከፋባት እንጂ እየተሻላት ያልሄደችበት ጉዳይ ቢኖር ይህ የአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት ጉዳይ አንደኛው ነው። እንደውም በዓመቱ የተጠቃሚውም የተጎጂውም ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

ስታቲስታ ባለፈው ዓመት በድረ ገጹ ባስነበበው ዘገባ፣ በአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2018 ሕገወጥ እጾችን ወይም መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ሰዎች ወደ 270 ሚሊዮን እንደሚጠጉ ጠቅሷል። በአፍሪካም ነገሩ ቀላል አይደለም። ኢናክት አፍሪካ ከኹለት ዓመት ገደማ በፊት ባወጣው ዘገባ፣ የአፍሪካ የሕገወጥ አደንዛዥ ዕጽ ፍጆታ በ30 ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ተብሎለታል።

እንደውም በ2050 አሁን ካሉት በተጨማሪ 14 ሚሊዮን አፍሪካውያን የዚህ ሕገወጥና አደንዛዥ ዕጽ ተጠቃሚዎች ይኖራሉ ተብሎ ትንበያ ተቀምጧል። ይህን ትንበያ እንዲኖር ያደረገውም አሁን ላይ የሚታየው የሕገወጥ ዕፅ ዝውውር በከፍተኛ መጠን መጨመር እንደሆነም ተጠቅሷል።

በዚህ መሠረት ምሥራቅ አፍሪካ ከዚህ ከፍተኛውን ቁጥር እንደምታስተናግድ ከወዲሁ የተገመተ ሲሆን፣ ምዕራብ አፍሪካ ደግሞ ትልቁን የሕገወጥ ዕፅ ዝውውር ገበያ ይዛ ትቆያለች ተብሏል።

እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዲከሰቱ ምክንያት የሆነው ደካማ የሕግ አፈጻጸምና የቁጥጥር ስርዓት እንደሆነ ይታመናል። እንዲሁም በየአገራቱ ድንበር ላይ ተደራጅተው ያሉ ወንጀለኞችና ለዚህ ግብይት መስፋፋት ተጠያቂ እንደሆኑም ተመላክቷል።

ታድያ ነገሩ በአፍሪካውያን ጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ እድገትና ልማት ላይም የራሱ የሆነ አሉታዊ አሻራ ማሳረፉ አይቀሬ ነው። ከዛም ባለፈ በሱስ ውስጥ ለሚገኙና ከዛ ለመላቀቅ ለሚፈልጉ ዜጎቿም አፍሪካ የተሟላና ተደራሽ ሊሆን የሚችል የጤና አገልግሎት የላትም።
ከዛም አልፎ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሆኑት ሳይቀር ከሕገወጥ የዕፅ ማዘዋወር የሚገኘው ገቢ ተካፋይ ናቸው። ይህም የቁጥጥር ሥራውን ጥርጥር ወስጥ ከመክተት አልፎ፣ ጭራሽ ነገሩ እንዲስፋፋና ጥፋቱ እንዲበረታ እድል የሚከፍት ነው።

አደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነት እና ጤና
አደገኛ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች ከሚያጋጥማቸው የጤና እክል መካከል አንዱ የአዕምሮ ሕመም ነው። የጥፋተኝነት መንፈስ፣ ፍርሃት፣ ድብርት፣ ብስጭት፣ ራስን ለማጥፋት መነሳሳትና የመሳሰሉ ስሜቶች ከአደንዛዥ ዕፅ ተጠቃሚነትና ሱሰኝነት የሚመጡ ናቸው።
በዚህ ደግሞ በአብዛኛው ተጠቂ እና ተጋላጭ ሆነው የሚገኙት ወጣቶች ናቸው። ከዚህ ጋር በተያያዘ በብዛት ከሚታዩ የአዕምሮ ሕመሞች መካከል ድባቴ በላቀ ሁኔታ ትኩረት የሚያሻው እንደሆነ የጤና ክብካቤ ባለሞያዎች ያሳስባሉ። ይህም ታማሚው አላስፈላጊ ውሳኔዎችን እንዲወስን የሚያደርግ ነው።

ከኹለት ዓመት በፊት የተደረገ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመለክተው በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ በየዓመቱ ሰባት ሺሕ በላይ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ። ከዚህም ከግማሽ በላይ የሚሆነው በአዲስ አበባ የሚከሰት ነው።

ከአማኑኤል አእምሮ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ እንደሚገልጸው፤ አደንዛዥ ዕፆች የአእምሮን ጤናን ሊያውኩ የሚችሉት በተለያየ መንገድ ነው። ለምሳሌ የአልኮል መጠጥ ከፍተኛ ተጠቃሚነት የድብርት፣ የጭንቀት፣ የመርሳት፣ ስንፈተ ወሲብ፣ የእንቅልፍ ማጣትና የመሳሰለውን ያስከትላል። በአካል ጤና ላይም የጉበት፣ የልብ፣ የደም ቧንቧ፣ የጨጓራ በሽታ፤ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ የቁም ቅዠት፣ የደም ግፊት መጨመር፣ በሽታን የመከላከል አቅም መቀነስ የመሳሰሉ የጤና እክሎችን ያስከትላል።

ካናቢስ (ሃሺሽ ወይም ማሪዋና) ሌላው ብዙ ተጠቃሚ ያለው አደገኛ ዕፅ ነው። ይህም በአንድ ዘመን በተለይ በሕንድ፣ በቻይና እና በመካከለኛው ምሥራቅ ለብዙ ዓመታት እንደ መድኃኒት ያገለገለ ነው። ይህም ከላይ እንደተጠቀሰው የአእምሮ ሕመምን ያስከትላል።
ትንባሆ በዚህ የሚካተት ነው። ትንባሆ የልብ ሕመምን በዋናነት የሚያስከትል ሲሆን፣ የሳንባ ነቀርሳ፣ የአፍ ጠረንና የፊት መበላሸት፣ የጉሮሮና የምግብ ማስተላለፊያ ቧንቧ ነቀርሳ፣ የስኳርና የጨጓራ ሕመም፣ የደም ሕዋሳት ችግር እና የሰውነት ቁስለት በዋናነት የሚጠቀሱ መሆናቸውን ሆስፒታሉ አክሎ በጽሑፉ አንስቷል።

ነፍሰ ጡር የሆነች ሴት ሲጋር የምታጨስ ከሆነም ጽንሱ ላይ ብዙ ችግሮች ይከሰታሉ። ከዚህም መካከል የፅንሱ የልብ ምት መቀነስ፣ ጊዜው ሳይደርስ መወለድ፣ ማስወረድ፣ የመተንፈሻ አካላት ችግር፣ የፅንሱ ክብደት አነስተኛ መሆን እና የሚደርሰው የአየር መጠን መቀነስን ያስከትላል።

ይህ በፅንሱ ላይ የሚደርስ ችግር ተብሎ ይዘርዘር እንጂ በእናትም ላይ የጤና ጉዳት የሚያደርስ ነው። የወር አበባ መዛባትና መብዛት፣ የልብ ሕመም እንዲሁም በድንገት ራስን መሳት የመሳሰሉ እክሎችን እናት ልታስተናግድ ትችላለች።

የፀረ አደንዛዥ ዕፅ ቀን ዘንድሮ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚከበር ሲሆን ‹ጤና ለፍትህ፤ ፍትህ ለጤና› በሚል እንደሚከበር የዓለማቀፍ ኹነቶች መዝጋቢ የሆነው ‹ዓለማቀፍ የክዋኔ ቀናት – International Event Day› የተሰኘ አውታር አስነብቧል። በተያያዘ ይኸው ገጽ የተባበሩት መንግሥታትን ዋቢ አድርጎ በዓለም 230 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የዕፅ ሱሰኛ መሆናቸውን ገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here