‘ነብይ ዤሮ’

0
682

ዕለቱ እሁድ፣ ቦታው ባለግርማ ሞገሱ የአዲስ  አበባ ቴአትርና ባሀል አዳራሽ፣ ሰዓቱ ስምንት ተኩል፤ ቴአትር በተጠማ ተመልካች አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቷል። መብራቶች ጠፍተው ለአፍታ አዳራሹ ጨልሟል፤ ወዲያውም የመድረኩ መጋረጃ ተከፈተ።

መቼቱን የባሕር ዳርቻ አድርጎ የሚጀምረው ተውኔት ዋናው ገጸ ባህሪይ ደማቅ አረንጓዴ ካባ ለብሶ ይንጎማለላል። ጭንቅላቱን በነጭ ሻሽ የተጠቀለለ አንድ ከበሮ መቺ አብሮት ይታያል። ቃለ ተውኔቱ ዋና ገጸ ባህሪው በሕልሙ ሳይቀር እየመጣ ስላስቸገረው የቀድሞ ነብይ እየተረከ የሚጀምረው ʻነብይ ዤሮʼ የሚባል ርዕስ የተሰጠው ሙዚቃዊ ቴአትር ነው።

ነቢይ ዤሮ ራሱን የሃይማኖት መሪ ነኝ ብሎ ይጠራል። በናይጄሪያ ያለች የባህር ዳርቻ፥ ቀድሞ ነቢይ ከነበረው አዛውንት መሬት ነጥቆ በመሰለውና ልክ ነው በሚለው መንገድ የሚሠራ እና የራሱ ተከታዮች ያሉት ነቢይ ነው። ይህ ነቢይ ተከታዮቹ በጭፍን አብረውት የሚጓዙና እሱ ባላቸው መንገድ ብቻ የሚጓዙ ዓይናማ እውሮች መሆናቸውን በድፍረት ይናገራል። ከእናቱ ማሕፀን ጀምሮ ነብይ ሆኖ እንደተፈጠረ፣ ይህንንም ደግሞ ቤተሰቦቹ እንደተቀበሉት በምክንያትምነትም ባልተለመደ መልኩ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሰውነቱ ላይ ጸጉር በመብዛቱ መሆኑን ይተርካል። ዋና ገጸ ባህሪው ነብይ ዤሮ በቃለ ተውኔቱ ላይ ትንሽ አደግ እንዳለም ነጋዴ የመሆን ሐሳብ እንደመጣበት፥ ነብይነቱንም ሆነ ንግዱን ግን ጎን ለጎን ለማስኬድ እንደወሰነ ለተደራሲያን ያስረዳል። ዋናው ገጸ ባህሪይ ነብይ ዤሮ “ነብይ ለመባል በተደጋጋሚ የጌታን ሥም መጣራትና ልብስ መቀያየር በቂ ነው” በማለት በተዋቡ ቃላትና በመሳጭ ትወና ለተደራሲያን ሹክ ይላል።

በተደጋጋሚ “ዓለም የቴአትር መድረክ ናት፥ ተዋናዮቹም እኛ ሰዎች ነን” ሲባል የሚሰማውን ነብይ ዤሮ ቴአትር በእርግጥም ያረጋግጥልናል። በአገራችን ብሎም በዓለማችን እየተመለከትን ያለነውን የነቢይ ነን ባዮች መልክ፣ ቁመና ምግባር እና ተውኔታዊ ክንውኖችን በእውኑ ዓለም የሆነ እስኪመስል ድረስ ፍንትው አድርጎ ያሳያል – ነብይ ዤሮ። ተውኔቱ ተደራሲያን ራሳቸውን ዞር ብለው እንዲያዩ፣ ቆም ብለውም እንዲያስተውሉና እንዲፈትሹ የመስታወትነት ሚናውን ይጫወታል። የተውኔቱ ዋና ጭብጥ የሆነውን ʻያልሆኑትን ነኝ ብሎ በግብዝነት ለመታየት መሞከር፣ ጭፍን እምነትና አማኝነትንʼ በተውኔቱ የተለያዩ ክፍሎች በጥበባዊ ለዛና ትወና ተመልካች እንዲያይ፣ እንዲያዳምጥና በምናብ እንዲነጉድ ያደርጋል። ተውኔቱ በሃይማኖት መልኩ አድርጎ ያስቀምጠው እንጂ ተደራሲው መለስ ብሎ ራሱንና ዙሪያ ገባውን እንዲፈትሽ ያስገድዳል። በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የእውን ዓለም ምሁራኖቻችንን፣ ፖለቲከኞቻችንን፣ የመብት ተሟጋች ነን ባዮቻችንን የዕውነታው ዓለም ተውኔት እንድናስብ ብሎም እንድንመረምር ነብይ ዤሮ ያስገድደናል።

የʼነብይ ዤሮʼ ቴአትር ከ55 ዓመት በፊት በእውቁ ናይጄሪያዊው ጸሐፊ ወሌ ሶይንካ የተፃፈ ሲሆን፥ ወደ አማራኛ የመለሰው ፈለቀ የማርውሃ አበበ ነው። በተለያዩ የመድረክ ቴአትሮች፣ የፊልምና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች እንዲሁም ዘጋቢ ፊልሞች ላይ በትወና፣ በዳይሬክትርነት፣ በደራሲነት ወይም ተርጓሚነትና በድምጽ በመሥራት የሚታወቀው ፈለቀ፥ ዶሮ ማነቂያ አካባቢ ተወልዶ ማደጉ ብዙ ዓይነት መጽሐፎች ለማንበብ ዕድል እንደሰጠው ምስክረነቱን ሰጥቷል። ነብይ ዤሮን በተመለከተ፥ ከተተረጎመ ኹለት ዓመት እንዳለፈው የሚናገረው ፈለቀ፥ ለመድረክ ይበቃል ብሎ ጨርሶ እንዳላሰበ ይናገራል። ፈለቀ “በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ተማሪዎች ተውኔቱን በሚገርም መንገድና ብቃት ሰርተውት በማየቴ፥ ቴአትሩ ለትልቅ መድረክ መብቃት እንደሚችል አመንኩኝ” ይላል።

ይህ ተውኔት ሲፃፍ ማንንም እንዲመስል ተደርጎ እንዳልተፃፈ የሚናገረው ፈለቀ፥ የተዋናዮች አልባሳትንም በተመለከተ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረጉን ይናገራል። በተጨማሪም ፈለቀ “ተውኔቱን ብዙ ተመልካች መጥቶ እንዲመለከትልን እንፈልጋለን” በማለት ምክንያቱን ሲያስረዳ ተውኔቱን ሥንሠራ እያንዳንዱ ተመልካች ራሱን የሚያይበት መስታወት እንዲሆነው ነው። እንክርዳድን ከስንዴ ለመለየት የሚያስችል ነው። “እኛ የሠራነው ለእንክርዳዶቹ ነው፤ ስለዚህ ተመልካች ሲመጣ እኔ ከየትኛው ነኝ፥ ከእንክርዳድ ወይስ ከስንዴ የሚለውን ጥያቄ እንዲጠይቅ ያደርጋል” የሚለው ፈለቀ፣ ተመልካች ራሱን ማየት ስለሚፈልግ በርካታ ተመልካች አለን ሲል ተናግሯል።

በቴአትሩ ላይ በተርጓሚነትና መሪ ተዋናይነት የፈለቀ አሻራ ትልቅ ቢሆርም፥ በዝግጅቱ ላይ የተሳተፈው የነብዩ ባዬም ብቃትም በተዋናዮቹ ጭምር ከፍተኛ እውቅና እንዲቸረው አድርጎታል። አራት ወራትን ወሰደው የልምምድ ዝግጅቱ፥ ከጀማሪ እስከ አንጋፋ ተዋናዮች ተሳትፈውበታል። በአጠቃለይ በተውኔቱ ላይ ዘጠኝ ዋና ገጸ ባህሪያት እና ሃያ ንዑስ ገጸ ባህሪያት ተሳትፈውበታል።

ነብይ ዤሮ ከሦስት ሰዓት የመድረክ ቆይታ በኋላ ሲጠናቀቅ በዝግጅቱ፣ በአተዋወን ብቃትና በያዘው ቁም ነገረኛ መልዕክት የረካው ተመልካች፥ ለስንብት ተዋናዮቹ ወደ መድረክ ብቅ ሲሉ አዳራሹን በጭብጨባ አናግቶት በቴአትሩ ላይ በሁሉም መስክ የተሳተፉትን ሞራል ከፍ አድርጓል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here