የአዲስ አበባ መሬት ‘ፆም ማደር’ እንዳይቀጥል

0
793

መሬት በካሬ እስከ 300 ሺሕ ብር በሚሸጥባት አዲስ አበባ እስከ 20 ዓመታትን ለልማት በሚል አጥረው ፆም ያሳደሩ ʻባለሀብቶችʼ በርካታ ነበሩ። በከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ መቀመጫ ፊት ለፊት እንዲሁም በአራት ኪሎው የጠቅላይ ሚንስትሩ መቀመጫ ቤተ መንግሥት ግንባር ላይ ዓመታትን ታጥረው የነበሩት ቦታዎች መንግሥት በባለሀብቶች ላይ ጥርስ አልባ እንደሆነ ሲያሳብቁበት ነበር። በተለይም ለልማት በሊዝና በሌሎችም መንገዶች በርካታ ቦታዎችን ለባለሀብቶች ያስተላለፈው የከተማ አስተዳደሩ እንዳሰበውና እንደተገባለት ውል የታሰቡት የልማት ቱርፋቶች መሬት ላይ ባለመገለጣቸው ጭንቅ ውስጥም ገብቶ እንደነበር ማሳያዎች አሉ። ይኸውም ለባለሀብቶች ተደጋጋሚ የስድስት ወራት ማስጠንቀቂያን ከመስጠት ዘሎ ቦታዎቹን ወደ መንጠቅ ለመግባት እጅና እግሩ ተሳስሮ የነበረ መሆኑ ነው። ነባሩ አስተዳደር የሰጠው ስድስት ወራት ማስጠንቀቂያ ሲያልቅ ሌላ ስድስት ወርን ከመጨመር ሳይዘልም አሁን ከተማዋን የሚመራው ካቢኔ በአዲስ ተዋቅሯል።

አዲሱ አመራር ከተደነቀበት አንዱ እርምጃውም ከአንድም ኹለት ከንቲባና አያሌ ካቢኔ ተቀያሮ ያለማውን መሬት አጥረው ካለልማት ካኖሩት ባለሀብቶች ለመንጠቅ ያልደፈሩትን ከስድስት ወር ዕድሜ ባነሰ መንገድ ሲባክኑ የነበሩ ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ ለማስገባት መድፈሩ ነው።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ እስከ ወረዳ መዋቅር ያሉትን አመራሮች ይዘው በአዳማ የኹለት ቀናት ግምገማን ሲያደርጉ፥ በማጠቃለያው የተናገሩትም ቀድመን ያነሳነውን ድፍረት የሚያሳይ ነው። የከተማ አስተዳሩ በኅዳር 2011 መጀመሪያ ቀናት ከ20 ዓመታት በላይ በፒያሳና ሸራተን አዲስ ሆቴል ፊት ለፊት ታጥረው የቆዩትን ቦታዎች አጥር በማፍረስ ወደ መሬት ባንክ ማስገባት መጀመሩ ይታወሳል። በሌሎችም አካባቢዎች እንዲሁ ረጅም ዓመታትን ታጥረው የዳዋ ሲሳይ የሆኑ ቦታዎችን አስተዳደሩ መንጠቁ አይዘነጋም። በዚህም ምክትል ከንቲባው እስከ ታኅሣሥ 2011 የተሠራውን የአስተዳራቸውን የስድስት ወራት ሪፖርት ለከተማዋ ምክር ቤት ሲያቀርቡ ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ካሬ ሜትር በላይ ቦታዎች ወደ መሬት ባንክ ማስገባታቸውን እንደገለፁ ይታወሳል።

ከዚያ በኋላም ለሪል እስቴት ቤት ልማት ተሰጥተው በቤት ፈንታ ዳዋ ሲውጣቸው የኖሩ የከተማዋን ቦታዎች ከ29 የሪል እስቴት አልሚ ኩባንያዎች ለመንጠቅ መወሰኑን ተከትሎ ወደ መሬት ባንክ የገቡት ቦታዎች መጠን ከዚህም እንደሚልቅ እሙን ነው።
ከሰሞኑ ግምገማ ታዲያ ምክትል ከንቲባው ሲናገሩ አይደፈሩም የተባሉ ቦታዎችን አስተዳደራቸው ሲነጥቅ ከሚንስትሮችም ጭምር ‹ተው ይቅርባችሁ› ሲባሉ ነበር። በዚህም የቦታ መንጠቅ ሒደቱ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች የነበሩበት እንጂ አልጋ በአልጋ እንዳልነበር በመጠቆም አስተዳደራቸው ይህን በድፍረት በማድረጉ ታላቅ ኩራት እንደሚሰማቸው ተናግረዋል። ይህም በቀደሙት የአስተዳደሩ የበላዮች ያልተሞከረ በመሆኑ ለአዲሱ አስተዳደር አንዱ የጥንካሬ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ከነዋሪዎች በኩልም በርቱ ሊባሉ እንደሚገባ ያምናሉ።

ዳንኤል ሌሬቦ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ምኅንድስና ኮሌጅ ዲን ናቸው። ዳንኤል እንደሚሉት ያልለሙ ቦታዎችን ነጠቃው እጅግ የዘገየ ቢሆንም አዲሱ አስተዳደር የወሰደው እርምጃና ቁርጠኝነት ግን ሊደነቅ ይገባዋል። ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ መሬት ልማት ማኔጅመንት የአንድ ክፍለ ከተማ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ዳንኤል ለልማት ተብለው ከተሰጡ ቦታዎች ማካከል ለ20 ዓመታት ያለጠያቂ ታጥረው የነበሩ ቦታዎች በቅርቡ በተወሰደው እርምጃ መነጠቃቸውን በመጥቀስ ትልቅ እምርታ ነው ይላሉ። ግን ደግሞ እርምጃው የዘመቻና የአንድ ወቅት ሥራ ሆኖ እንዳይቀር ይሰጋሉ።

ከመንጠቅ ባለፈስ?
በእርግጥ አስተዳደሩ ሲባክኑ የነበሩ ቦታዎችን ወደ መሬት ባክ ማስገባቱ ቢደነቅለትም ምንድነው ሊሠራባቸው ያቀደው፣ አሁንስ ምን ላይ ናቸው የሚለው ጥያቄ መልሶ እየተነሳበት ነው። አስተዳደሩ ቦታዎቹን ለምን ለምን ዓይነት ልማት አቅዷቸዋል ለሚለው ጥያቄ ምልሽ የጠየቅናቸው በመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የመሬት ባንክና ማስተላፍ ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ ተስፋዬ ጥላሁን ጥያቄውን በበርካታ የመገናኛ ብዙኀን አውታሮች በየቀኑ እየተጠየቁ ስለመሆኑ በመግለፅ የተለየ ዕቅድ እንደሌለ ተናግረዋል። ይህም ማለት አስተዳደሩ ቦታዎቹን የነጠቀው አቅዶ አይደለም ማለት ነው። ቦታዎቹን ወደ መሬት ባንክ ከማስገባት ባሻገር ምን ይሠራባቸዋል የሚለውን እስካሁን የወጣ ዕቅድ የለም ወይ ለሚለው ጥያቄም ተስፋዬ “አዎ” የሚል ምላሽ ሰጥተውናል። እንዴትና በምን ምክንያት ነው አስተዳደሩ ረጅም ዓመታትን ያለ ጥቅም የቆዩ ቦታዎችን ወደ ልማትና ጥቅም ለመመለስ ዕቅድ የማያወጣው ለሚለው ሥራ አስኪያጁ ከዚህ በላይ ምላሽ ሊሰጡን አልፈቀዱም።

ምክትል ከንቲባው ወደ መሬት ባንክ ከገቡ አራት ወራት ስለሆናቸው ቦታዎች ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ አስተደደሩ ከመንጠቅ ባለፈ ቦታዎቹን አሁንም ወደ ምጣኔ ሀብት ማስገባት አለመቻሉን አምነዋል። አዲስ ማለዳ ከወራት በፊት ጀምራ ቦታዎቹ ላይ ምን ታስቧል፣ ቀድሞ ሥራ ላይ እንዲውል ከፀደቀው 10ኛው የከተማዋ መዋቅራዊ መሪ ፕላን ጋርስ እንዴት ተጣጥመው ይሔዳሉ የሚሉትን ጥያቄዎች ቦታዎቹ ላይ በበላይነት ውሳኔ የማስተላለፍ ሥልጣን ካላቸው ከንቲባው በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት የከንቲባ ጽሕፈት ቤትን ብ ት ጠይቅም “በቅርብ ሳምንት የታሰቡት ፕሮጀክቶች ይፋ ይደረጋሉ”የሚል ምላሽ ስታገኝ ሰንብታለች። ሆኖም እስካሁንም የተባሉት ፕሮጀክቶች ይፋ አልሆኑም።

ዳንኤል ቦታዎቹ ረጅም ዓመት ከልማት ተገልለው ቢቆዩም ያለፉት አራት ወራት ግን ዘገየ ተብሎ የሚያስወቅስ አለመሆኑን ያነሳሉ። ያለፈው ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማቸውና በተሻለ ለማልማት ምናልባትም እስከ አንድ ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል በመግለፅ፣ በእነዚህ ወራት ግን ጥልቅ ጥናት ማካሔድ እንደሚያስፈልግ፣ ብሎም የሌሎችን አገራት የተሻሉ ከተሞች ተሞክሮም መውሰድ ካስፈለገ ከራስ ጋር እንዲጣጣም አድርጎ በወጉ መመልከት እንደሚገባ ይመክራሉ።

ቦታዎች ሲነጠቁ ተያይዘው የሚመጡ የሕግ ክርክሮች እንደሚኖሩም በመጥቀስ አስተዳደሩ በተገባው ውል መሰረት ያልለሙ ቦታዎችን ጊዜውን ጠብቆ ለመንጠቅ የሕግ ድጋፍ (መብት) ቢኖረውም ከካርታ፣ ቀድመው ለሊዝ ከተከፈሉ ገንዘቦችና ሌሎችም ጉዳዮች ጋር የሚነሱና ወደ ፍርድ ቤት የሚያመሩ ክርክሮች እንደሚኖሩም ዳንኤል ያነሳሉ። ይህም ለሚፈጠሩ መዘግየቶች አንድ ምክንያት እንደሚሆን ያምናሉ።

ፆም አዳሩ እንዳይደገም ምን ይሁን?
የከተማ ልማትና ምኅንድስና ምሁሩ ዳንኤል “የከተማ ሀብት እጅግ ውስን የሆነው መሬት ነው” ካሉ በኋላ ይህን ውስን ሀብት በጠንካራ ሕግና ቁጥጥር ማስተዳደር እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ። ከዚህ ቀደም አንድም ለቦታዎች ረጅም ጊዜ ታጥሮ መቆየት ምክንያቱ የመሬት ዘርፍ ባለሙያዎች ከባለሀብቶች ጋር የሚኖራቸው አላስፈላጊ (የጥቅም) ግንኙነት ነውም ይላሉ።

ዋናው ግን በከተማዋ ከማዕከል እስከወረዳ ባለው መዋቅር ፍፁም መናበብ አለመኖር ነው። ለልማት የሚተላለፉ ቦታዎችን ውል መነሻ በማድረግ መቼ ይለማሉ፣ እስከመቼስ ተጠናቅቀው ለተፈለገው አገልግሎት ይውላሉ የሚለውን የተግባር ዕቅድ (action plan) አውጥቶ ከከንቲባ እስከ ወረዳ አመራር በጥብቅ መናበብ ከመከታተል ይልቅ ውልን ሼልፍ ላይ ሰቅሎ ነገር ዓለሙን የመርሳት ጥንውት ቦታዎቹን ለረጅም ዓመት ከልማት ውጭ ስለማድረጉ በማንሳትም ይህ ልማድ ሊታረም እንደሚገባው ዳንኤል አፅንኦት ይሰጣሉ። መሬትን ከመስጠት ባለፈ ማን ይከታተለዋል መቼስ ያልቃል የሚለው ላይ አስተዳደሩ በርትቶ መስራት እንዳለበት ያስገነዝባሉ። ያልለሙ የሬል እስቴት ቦታዎችን በተመለከተ ውሳኔ ለማሳለፍ ምክትል ከንቲባው ካቢኔያቸውን በሰበሰቡበት ወቅት ቦታዎቹ እስከዛሬ እንዴት ጦማቸውን አደሩ ያልናቸው ተስፋዬ አንዱና ዋናው ምክንያት በመንግሥት በኩል ክትትል ባለመደረጉ እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።

ሌላው ቦታ ስላለ ብቻ እያነሱ ማልማት ለማይችሉና አቅሙ ለሌላቸው፣ ሲብስም የተረከቡትን ቦታ አሳልፈው ለሚሸጡ አካላት ከመስጠት መቆጠብን እንደሚጠይቅ የሚመክሩት ምሁሩ ዘርፉም በባለሙያ መመራት እንዳለበት ያሰምሩበታል። ከዚህ ቀደም መሬት ዘርፍ ላይ እውቀቱም፣ ልምዱም የሌላቸው ሰዎች እየተመደቡ በክህሎት ማነስ በሠሩት ስህተት ቤተሰባቸውን በትነው እስር ቤት የገቡም እንዳሉ ያስታውሳሉ።

ከዚህ በኋላ መሬት ከመሰጠቱ በፊት ቀድሞ መጠናት ያለበት የሚፈጥረው የሥራ ዕድልና አዋጭነት (በርካታ ሕዝብን የመጥቀሙ ጉዳይ) ነው የሚሉት ዳንኤል ከተማ ላይ ፎቅ መገንባቱ ብቻ ልማት አይደለም ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠረውን ቤት ፈላጊም ታሳቢ አድርጎ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ማዕከልን አንድ ላይ መገንባትን የሚጠይቀውን የቅይጥ ግንባታ አዲስ የከተማ ልማት ሥልት መተግበር እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ። በተጨማሪም በተላለፉ ቦታዎች ላይ የሚሠሩ ልማቶች አንድም በሥራ (ግንባታ) ሒደት፣ ኹለትም ወደ አገልግሎት ከገቡ በኋላ የሚፈጥሩት የሥራ ዕድልና የብዙኀን ሕዝብ ጠቃሚነት ዋና መመዘኛ መሆን እንዳለባቸውም ያሰምሩበታል።

ኅዳር 15 ምክትል ከንቲባ ታከለ በቲውተር ገፃቸው የሸራተን ፊት ለፊትና የፒያሳው ቦታዎች “በቀጣዮቹ ሳምንታት የሕዝብ መናፈሻ እና አረንጓዴ ቦታዎች እንደሚሆኑ መፃፋቸው ለብዙ መገናኛ ብዙኀን አውታሮች ዜና ሆኖ ነበር። ይሁንና እዚህ ላይ እነዚህ ቦታዎች ሥራ ላይ ባለው መሪ ፕላን ለዚህ አገልግሎት እንደማይውሉ ከመቀመጡ ባሻገር በምን አግባብና አዋጭነት ጥናት ነው ለዚህ አገልግሎት የታጩት የሚለው ምላሽ አላገኘም።

ዳንኤል መሪ ፕላን ሊሻሻል እንደሚችል በመጥቀስ ሊሻሻል የሚችለው ግን በአዲስ የሚተካው ዕቅድ በሚፈጥረው ሥራ ዕድል እና ለሕዝቡ በሚኖረው ጠቃሚነት ማሳመን ከቻለ ብቻ እንደሆነ ይገልፁና በዚያ ልክ ነው ወይ እየተኬደ ያለው ሲሉ ይጠይቃሉ። ከዚህ ቀደም በስሜት የሚወሰኑ እንደነበሩ በመግለፅ ለአረንጓዴ ቦታ የተባለውን ድንገት ትቶ ለሪል እስቴትና ሌሎችም አገልግሎቶች የማስተላለፍ ስሁታዊ ልምድ እንደነበር ይገልፃሉ።

“መዋቅራዊ ፕላን ንድፍ ላይ ብሩህ ራዕይ አለን” የሚሉት ዳንኤል በተግባር ለማየት ግን ጠንካራ ትግበራ እንደሚያስፈልግ ያስረግጣሉ። ለዚህም ከትምህርት ተቋማት ጋር መተባበር እንደሚያስፈልግ በመግለፅ ዩኒቨርሲቲያቸው በጥናትና ምርምርም ሆነ በባለሙያዎች ሥልጠና ከተማዋን እንደሚያግዝ አክለዋል። በተደጋጋሚ ከሚነሱ ችግሮች መካከል አንዱ የዩኒቨርሲቲ፣ መንግሥትና ኢንዱስትሪ ትስስሩ የላላ መሆን ነው። በዚህም የሚደረጉ በርካታ ጥናቶች ከመደርደሪያ ሳይወርዱ አቧራ መጥገብ ዕጣ ፈንታቸው እንዲሆን ተገድደዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ዩኤን ሀቢታት ʻTHE STATE OF ADDIS ABABA 2017ʼ በሚል ኹለት ዓመታትን የፈጀው ጥናት ሪፖርት ይፋ በሆነበት ሰነድ ከአዲስ አበባ መሐል ከተማ ውስጥ 80 በመቶው እንደገና ፈርሶ ሊገነባ የሚገባው ወይም ያልለማ (ʻቆሻሻʼ) አካባቢ የሚባል እንደሆነ ያስረዳል። 70 በመቶ ቤቶችም መሰረታዊ የሚባል የልማት አቅርቦት የሌላቸውና አብዛኞቹም የቀበሌ ቤቶች ናቸው። ይህን ገፅ ለመቀየር መጠነ ሰፊ የመልሶ ማልማት ሥራ ቢጀመርም አንድም ነዋሪዎችን ከመሐል ከተማ ወደ ዳር በመግፋት ኹለትም አካባቢውን በስሜት አፍርሶ ሳያለሙ ረጅም ዓመታትን በማቆየት አስተዳደሩ ይወቀሳል። በመሆኑም አሁንም ያንን ማረም እንጂ አዲስ ጥፋት ከመፈፀም መቆጠብ እንደሚገባ ምክረ ሐሳቦች ተቀምጠዋል።

ወደ መሬት ባንክ በገቡ ቦታዎች ላይ አስተዳደሩ የተወሰኑ ቦታዎችን ለጊዜያዊ ፓርኪንግ ፈቅዷል። ይሁንና በአዲስ አበባ ልምድ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ ሥራ ከተጀመረ በኋላ ሀብት አካብቶ ወደ ሌላ ዘርፍ ተሻገሩ ሲባል የሙጥኝ የማለቱ ነገር ነገ ከነገ ወዲያ ወጣቶቹ ልቀቁ ቢባሉ ምን ያክል ፈቃደኛ ይሆናሉ፣ የሚያመጣው እሰጣ ገባስ የሚለውም ሊታሰብበት የሚገባ መሆኑን የሚያነሱ አሉ። በተጨማሪም ቦታዎቹ ለፓርኪንግ ሲሰጡ እንደካሳንችስ አካባቢ ባሉት ቦታዎች ላይ ሰዎች በራሳቸው ፍቃድ ቦታ ተከፋፍለው የንግድ ቦታዎችን በእንጨት እርብራብ መሥራታቸው ይታወሳል። አስተዳደሩ ፈጥኖ ማፍረሱ እንደተጠበቀ ሆኖ ቦታዎቹ ለመሰል ሕገ ወጥ ተግባራት እንዳይዳረጉም ከተማዋ ፈጥና ቦታዎቿን ወደ ሕጋዊ ልማት ማስገባት እንዳለባት ይመከራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 23 ሚያዚያ 5 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here