የዓባያ ሐይቅ 1 ሺሕ 780 ሔክታር በእንቦጭ ተሸፍኗል

0
1019

ኢትዮጵያ ከጣና ሐይቅ ቀጥሎ በስፋቱ ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዓባያ ሐይቅ 1 ሺሕ 780 ሔክታር የውሃ አካል በእንቦጭ አረም መወረሩ ታወቀ።

የእንቦጭ አረም ሥርጭት በከፍተኛ ፍጥነት ከመጨመሩም ባሻገር በወንዞቻችን እና በሐይቆቻችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ነው ሲሉ የነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ ኀላፊ ሽመልስ ዘነበ ገልፀዋል። በሐይቁ ውስጥ በሚኖሩ ብዝኀ ሕይወትና በሚያሰግሩት ዓሣ መጠን ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ያብራሩት ኃላፊው, አረሙ እርስ በርስ በመጠላለፍ ሣር እንዳይበቅል ተጽእኖ መፍጠሩ እና በሐይቁ አቅራቢያ የእንስሳት መኖ ሣር እንዲጠፋ ማድረጉ በሐይቁ የሚተዳደሩ ማኅበረሰብ ክፍሎችን ስጋት ውስጥ እየጣለ ነው። ሆኖም ግን ኅብረተሰቡ እንቦጩን ለማጥፋት እርብርብ ከማድረጉም በላይ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ወደ ማዳበሪያነት በመቀያር የገቢ ምንጭ ቢያደርጉት የተሻለ ውጤት የሚመጣ ሲሆን ማኅበረሰቡ ይህን አማራጭ ሊጠቀም የሚችልበት መንገድ ቢፈጠር ጉዳቱን በተለየ መንገድ መቀነስ ይቻላል ሲሉም አክለዋል።

በስፋቱ 1 ሺሕ 180 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያለው ዓባያ ሐይቅ በእንቦጭ አረም ከተወረረ ዓመታትን ያቆጠረ ሲሆን እንቦጩን በመጠኑም ቢሆን ለመቀነስ በአርባ ምንጭ ከተማ ሰፊ ርብርብ እየተደረገ በመሆኑ እስከሁን 2 መቶ ሔክታር ማስወገድ ተችሏል።

የእንቦጭ አረም በሐይቆች ላይ እንዳይስፋፋ በክልል ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተሟላ ጥናት በማድረግ የእንቦጭ አረም የሚፈጠርበት ሁኔታ ምንጩን እና የሥርጭቱን መጠን በማወቅ ለመከላከልና የጉዳት መጠኑን ለመቀነስና ለመቆጣጠር የሚስችል በጥናት የተደገፈ የተቀናጀ ስትራቴጂ አልተዘጋጀም። ሆኖም ግን ትክክለኛ የማስወገጃ መንገዱን አርባ ምንጭ ዩንቨርሲቲ ጥናት እያጠና በመሆኑ ይህ ጥናት ተጠናቅቆ ወደ ተግባር ሲገባ ዩንቨርሲቲው ይፋ እንደሚረግ ጨምረው ገልፀዋል።

የቀድሞ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የእንቦጭ አረምን ለመከላከልና ለመቀነስ እንዲሁም አረሙ የሚፈጥርበትን ሁኔታ ምንጩንና የሥርጭቱን መጠን በመለየትና በመቆጣጠር ሐይቆችና ወንዞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው መጠበቅ ሲገባው ተገቢውን ሥራ ባለመሠራቱ የእንቦጭ አረም ሥርጭት በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩ ከፍተኛ ተፅዕኖና ጉዳት እያስከተለ ነው ሲሉ የፌደራል ዋና ኦዲተር ገመቹ ዳቢሶ ተናግረዋል።

በመጨረሻም አረሙን በዝናብ ወቅት ለማስወገድ የማይመች ከመሆኑም በላይ በሐይቁ ውስጥ አዞና ጉማሬን ጨምሮ በርካታ የሚተናኮሉ እንስሳት መኖር አረሙን ለማስወገድ ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት መፍጠሩን አስታውቀዋል።

በሌላም በኩል በዝዋይ ሐይቅ ዙርያ ካሉ ወረዳዎች በዱግዳ ወረዳ ባሉ 8 ቀበሌዎች የእንቦጭ አረም የተከሰተ ሲሆን በአጠቃላይ በዝዋይ ሐይቅ ላይ በአረሙ የተሸፈነው የውሃ አካል 40 ሔክታር እንዲሁም በጣና ሐይቅ፣ በአባ ሳሙኤል ግድብ፣ በቆቃ ግድብ፣ በአባያና ጫሞ፣ በባሮ፣ በአዋሽ እና በአባይ ወንዞች ላይ በመታየቱ በሐይቆች እና ወንዞች ላይ የተጋረጠ አደጋ እየሆነ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here