በለስ ወደ ውጭ መላክ ሊጀመር ነው

0
1289
  • አንድ ኪሎ የበለስ ምርት በአራት ዶላር ለገበያ ይቀርባል

በትግራይ ክልል አዲግራት ከተማ የተቋቋመው በለስ አጋሜ የተባለ ድርጅት ከሰኔ 2011 ጀምሮ በለስን በጭማቂ እና በማልማላታ መልክ በማዘጋጀት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ እና ወደ ጣሊያን ለመላክ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ድርጅቱ እስከአሁን በደረሳቸው ስምምነቶች አንድ ኪሎ የበለስ ምርት በኪሎ አራት ዶላር አካባቢ ሚሸጥ ሲሆን ፋብሪካውም በሰአት አራት ቶን በለስ የመፍጨት አቅም እንዳለው የበለስ አጋሜ ዋና ዳይሬክተር የማነ ካሕሳይ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከኹለት ሳምንት በኋላ በይፋ የሚመረቀው ድርጅቱ የበለሱን የውስጥ ፍሬ በማቀነባበር ለመዋቢያ የሚያገለግል ዘይት እንደሚያመርትም ታውቋል።

ዐሥራ አራት አባላትን ያቀፈው በለስ አጋሜ በተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ድጋፍ የተቋቋመ ሲሆን በ2008 ቢቋቋሞ የመልካም የግብርና ተግባራት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ባለመያዙ ምርቶቹን መለክ አልቻለም ነበር።

በአሁን ወቅት አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን እና ጣሊያን ከሚገኙት ተቀባዮች የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቶችን ብቻ እስኪላክላቸው እየጠበቁ እንደሆነ ገልጿል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የማነ ሲገልፁ በድርጅቱ ውስጥ የሚገኙት አባላት በበለስ ምርት የሰለጠኑ እና በንግድ ሥራ አመራር የላቁ እንዲሆኑ ሥልጠና መውሰዳቸውን ጠቁመው ሥልጠናው ሙሉ ወጪም በየተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት መሸፈኑን ጠቁመዋል።

በአዲግራት ዩኒቨርስቲ ‘በለስ ኢንስቲትዩት’ በሚል ራሱን የቻለ ተቋም ተቋቁሞ በክልሉ ውስጥ የሚመረተውን የበለስ ምርት ለማሳደግ አርሶ አደሮችን በመደገፍ እና ጠቃሚ ግብዓቶችን በማቅረብ ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ይህን በሚመለከት የማነ ሲያስረዱ ዩኒቨርሲቲው የረጅም ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝና በአሁኑ ሰዓት የሰርቶ ማሳያ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሆነ ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዩኒቨርሲቲው በበለስ ዙሪያ ከፍተኛ ምርምር እያካሔደ እንዳለ እና አዳዲስ የበለስ ዘርም በቅርቡ ለአርሶ አደሩ እንደሚያስተዋውቅ ይጠበቃል።

ድርጅቱ በለስን አቀነባብሮ ለአለም አቀፍ ገበያ ከማቅረብ ባሻገር የአገር ውስጥ ፍላጎትንም ለማርካት በዘመናዊ መንገድ እንደሚሠራ ጠቁሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here