- የደሞዝ ጭማሪ እና የቤት ጥያቄ ያነሱ መምህራን ሰልፈኞች መካከል ከፊሉ ታስረው ተፈትተዋል ተብሏል
አስተማሪዎች ለረዥም ዓመታት ሲያነሷቸው የነበሩ ጥያቄዎቻቸው መልስ ባለማግኘታቸው የሥራ ተነሳሽነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ለመምጣቱ ምክንያት መሆኑን የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር አስታወቀ። ይህ ደግሞ ለትምህርት ጥራት መጓደል የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ማኅበሩ ተናግሯል።
የመምህራን ደመወዝ ከሌሎች የሥራ ዘርፎች አንፃር ሲወዳደር በጣም ዝቅተኛ ነው ያሉት የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ፕሬዚደንት ደበበ ገብረፃዲቅ፣ ሙያውንም የማይመጥን ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በዚህም የተነሳ ኑሮ የተጫናቸው የከተማዋ መምህራን ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ያልተገቡ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን አክለው አስታውቀዋል።
መንግሥት መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ በማኅበሩ የተጠየቀ ሲሆን፣ የመምህራኑ ጥያቄዎች ከሆኑት መካከል የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የቤት፣ የደመወዝና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የሚሉት ይገኙባቸዋል።
መንግሥት የመምህራኑ ጥያቄዎች ተገቢ ናቸው ብሎ ቢያምንም ምላሽ ለመስጠት የዘገየ መሆኑን ማኅበሩ አስታውቆ፣ ስለሆነም መምህራን ከቃል የዘለለ የሚጨበጥ ተግባር ከመንግሥት እንደሚሻ አስገንዝቧል። መንግሥት የመምህራንን ደመወዝ ከሌሎች የሥራ ዘርፎች ጋር አገናዝቦ ፍትሐዊ እንዲያደርግም ተጠይቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ፌቨን ተሾመ፣ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች የመምህራኑ ብቻ አለመሆናቸውን በመግለጽ፣ ከዚህ በፊት 2000 ቤቶች ለመምህራን መተላለፋቸውንና በቀጣይም ሁሉም ነገር በሒደት እንደሚሆን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ጥያቄዎች ሲነሱ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ማገናዘብ እንደሚገባ የገለጹት ፌቨን፣ በመቶ ሺሕ ለሚቆጠሩ መምህራን በአንድ ጊዜ የደሞዝ ጭማሪና የቤት ጥያቄ ማንሳት ተገቢ አለመሆኑን አንስተው፣ ነገሮች በተቀመጠላቸው ጊዜና ዕቅድ መሔድ እንዲችሉ የመምህራኑም ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የመኖሪያ ቤት ችግርን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎችን ያነገቡ በሺሕዎች የሚቆጠሩ መምህራን ማክሰኞ በአዲስ አበባ ከተማ ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ከሰላማዊ ሰልፈኞቹ የተወሰኑት ለግማሽ ቀን ያህል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው መፈታታቸውን ከማኅበሩ አመራሮች ለማወቅ ተችሏል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቀው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር “የማውቀው ነገር የለም” ብሏል።
መምህራኑ ከደሞዝ በላይ የመኖሪያ ቤት አንገብጋቢ ችግር እንደሆነባቸውና ይህንንም በተደጋጋሚ ጠይቀው ምላሽ ማጣታቸውን ይልቁንም ለዘመናት በአፈና፣ በአካዳሚክ ነጻነት እጦትና በኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ማሳለፋቸውን የሰልፉ ተሳታፊዎች አውስተዋል።
በመላ አገሪቱ ከ508 ሺሕ በላይ አባላቶች አሉኝ የሚለው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የመምህራን የመኖሪያ ቤት ችግር እንዲፈታ ከ2007 ጀምሮ የመኖሪያ ቤት ፓኬጅ ፀድቆ ተግባራዊ የሆነ ሲሆን በዚህም ከ50 ሺሕ በላይ መምህራን በዚህ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየሠራሁ ነው ብሏል።
በ2009 መምህራንን ያላካተተው የደሞዝ ጭማሪም መልስ እንዲያገኝ እየሠራን ነው ያሉት፣ የማኅበሩ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) መምህራኑ እያነሱ ያሉት ጥያቄ ተገቢ ቢሆንም አካሔዱን ግን እኛ አናውቀውም፤ የማክሰኞ ሰልፍ ላይም ታሰሩ ስለተባሉ ሰዎች የምናውቀው ነገር የለም ብለዋል።
በማክሰኞው የመስቀል አደባባይ ድምፅን የማሰማት እንቅስቃሴ ላይ ከተገኙት ይልቅ በፖሊስ ተከልክለው የቀሩት እንደሚልቁ የሰልፉ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ሙከራ ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም።
ቅጽ 1 ቁጥር 30 ግንቦት 24 ቀን 2011



