- መደበኛ የቀጠና ኹለት ሙሉ በፖሊስ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገላቸው
በኢትዮጵያ ወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ነባር አማኞች እና ከአዲሱ አመራር የአስተዳደር ሠራተኞች ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደገቡ ታወቀ። ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት በቤተ ክርስቲያኗ የተፈጠረው አለመግባባት በ2006 የወጣውን ቤተክርስቲያኗን መተዳደሪያ ደንብ መሻሻል ተከትሎ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በኹለት ጎራ ተከፍሎ ውዝግብ ውስጥ የገቡት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የተሻሻለውን መተዳደሪያ ደንብ በማይቀበሉ ምዕመናን እና ነባር አመራሮች ላይ ዕገዳ እስከመጣል ተደርሷል። በዚህም መሰረት ደንቡን አያሠራም የአጥቢያዋንም መብት ይገድባል በሚል ቅሬታ ያቀረቡትን የቀጠና ኹለት ሙሉ ወንጌል አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን መሪዎችን መታገዳቸው ታውቋል። በዚህ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ከሚገኙት 11 አባላት ያሉት የአመራር አካላት ሰባቱ ቅሬታ ያቀረቡ ሲሆን አዲሱ የሙሉ ወንጌል አመራር ቀሪ አራት አባላትን በመደገፍ በሰባቱ ላይ ከአመራርነት ከማገድ ባለፈ ከቤተ ክርስቲያን አባልነትም እስከመሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እንደወሰደባቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በግንቦት 24/2011 ቀጠና ኹለት አጥቢያ ቤተ ክስቲያን አባል የሆኑ አንድ ፓስተርና አንድ ቤተ-ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች በፖሊስ መደብደባቸውን እና መንገላታት እንደደረሰባቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ሰዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግዋል።
የቀጠና ኹለት አጥቢያ ቤተ- ክርስቲያን አባላት በጉዳዩ ላይ በማካሔድ ላይ የነበሩት ስብሰባ “ከበላይ የመጣ ቀጭን ትዕዛዝ ነው” በሚል በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ እንዲበተን መደረጉን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አያይዘውም ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ መደበኛ የቤተ ክርስቲያኗ የአምልኮ ሥነ ስርዓቶች በፖሊስ ከፍተኛ የሆነ ጥበቃ እየተደረገባቸው እንደሚካሔዱ አስታውቀዋል።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ ሙሉ ወንጌል አማኞች ቤተ-ክርስቲያን ከ2006 ጀምሮ ስትጠቀምበት የነበረውን መተዳደሪያ ደንብ በታኅሳስ 12-13/2011 በተጠራ ጠቅላላ ጉባኤ የተሻሻለ ሲሆን፤ ተሻሻለ የተባለው አዲሱ ደንብ የአካሔድ ጥሰት፣ የሕግ ክፍተት እና የአስተምህሮ እና ሥነ ምግባር ስህተቶች አለባቸው በሚል ለአለመግባባቱ መንስኤ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ነባር የቤተ-ክርስቲያን አባላትና መሪዎች ቅሬታ ቢቀርብም ሥልጣን ላይ ባሉ አመራሮች ተቀባይነት ሊያገኝ እንዳልተቻለ ታውቋል። ይህን በሚመለከትም ከታህኅሣሥ 19/2011 ጀምሮ ለሰላም ሚኒስቴር በተለያዩ ደረጃ ላሉ ኀላፊዎች ተደጋጋሚ ደብደዳቤ ደንቡ እንዳይፀድቅ ደብዳቤ ቢፃፍም አጥጋቢ ምላሽ ባለመገኘቱ የቤተ-ክርስቲያኗ ኅልውና አደጋ ውስጥ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የቤተ ክርስቲያኑ አባላት ይናገራሉ።
እንደ ምንጮች ገለፃ በአሁኑ ሰዓት የምዕመናን የመንፈሳዊ ሕይወት እንደተጎዳና አሁንም ድረስ በመኖሪያ ቤታቸው ድረስ በፖሊስ ኀይላት ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው እየደረሰባቸው ከመሆኑም በላይ ይህን በመፍራትም አንዳንድ ግለሰቦች መኖሪያቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጥለው ሌላ ቦታ ተጠልለው እንደሚገኙም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ሙሉወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን ፕሬዘዳንት ፓስተር ይልማ ዋቄን በስልክ በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ እንደማይመለከታቸው በመጥቀስ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011



