አዲስ – አዳማ የፍጥነት መንገድ በእንስሳት ምክንያት የሚደርሰው አደጋ አሳሳቢ ሆኗል

0
986

ከአዲስ አበባ አዳማ ድረስ የተዘረጋው የፍጥነት መንገድ በሚያቋርጣቸው አካባቢዎች እንስሳት ወደ ዋና መንገድ በመግባት አደጋ እንዲደርስ ምክንያት መሆናቸውን የሕዝብ ማመላለሻ አሽከርካሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ። አሽከርካሪዎች ጨምረው እንደገለፁትም፤ መንገዱ በፍጥነት የሚነዳበት በመሆኑ እና እንስሳት መንገድ ላይ በሚያቋርጡበት ጊዜ ላለመግጨት በሚደረገው ጥረት ላይ ተሸከርካሪዎች ከቁጥጥር ውጪ ስለሚሆኑ አደጋው እንደሚደርስ አስረድተዋል።

የፍጥነት መንገዱ ግንባታው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት በሆነበት ጊዜ ከየትኛውም የእስሳት እንቅስቃሴ ነፃ መሆኑ መገለፁ የሚታወቅ ቢሆንም፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንስሳቶች በተለይም ደግሞ የቀንድ ከብቶች ወደ ዋና መንገድ በመግባት የአደጋ መንስኤ መሆናቸውን ገልጸዋል። ከአዲስ አበባ – አዳማ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና አሽከርካሪ የሆኑት በልሁ ልጅዓለም ለሰባት ዓመታትን አሽከርክረዋል። “የፍጥነት መንገዱ ከተከፈተ ጀምሮ አደጋውም ሆነ አዳማ ለመድረስ የሚፈጀው ጊዜ ቀንሷል፤ ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንስሳት ወደ ዋና መንገድ እየገቡ ችግር እየተፈጠረ ነው” በልሁ አያይዘውም ተመሳሳይ አደጋ ያጋጠማቸውን በሚመለከት፥ ኹለት አሽከርካሪዎች በፍጥነት እያሽከረከሩ በነበሩበት ወቅት አህያ መሃል መንገድ ላይ በመግባቱ ላለመግጨት ጥረት ሲያደርጉ እንደተገለበጡ እና አንደኛው አሽከርካሪ ሕይወቱን እንዳጣ አስታውሰዋል።

አዲስ ማለዳ በኢትዮጵያ የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ አስተዳደር ሥር የሚገኘው የአዲስ አዳማ ፍጥነት መንገድ ተዘዋውራ ለመታዘብ በሞከረችበት ወቅት ዋናው መንገድ ግራ እና ቀኝ ዳር የታጠረበት ሽቦ በስፋት ተቆርጧል፤ ቋሚ የአጥር ብረቶች ወድቀው ወይም ተነቅለው ተመልክታለች።

ይህን ጉዳይ በሚመለከት የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ የሆኑት ሮቤል አያሌው ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የሽቦዎችን መቆረጥ የሚስማሙበት ባለሙያው “የአካባቢው ማኅበረሰብ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ሽቦዎችን እየቆረጠ ከብቶችን በማስገባት በዋና መንገዱ ክልል ውስጥ ዳር እና ዳር ያለውን ሳር እንዲበሉ ያደርጋል” ሲሉ ይናገራሉ። አያይዘውም፤ ኢንተርፕራይዙ የኻያ አራት ሰዓታት የቁጥጥር ሥራ እንደሚሠራ ገልፀው እንስሳቶችን አልፎ አልፎ ከተቆጣጣሪዎች አምልጠው ሚገቡበት አጋጣሚ እንዳለም አክለዋል። ይሁን እንጂ የእንስሳቶች ወደ ዋና መንገድ መግባት በጉልህ የሚጠቀስ የአደጋ መንስኤ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ ይህን በሚመለከት የክፍያ መንገዶች ኢንተርፕራይዝ መንገዱ በሚያቋርጥባቸው የገጠር መንደሮችና ቀበሌዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በተለይም ደግሞ በትራፊክ ደኅንነት ዙሪያ እየሠራ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ያገኘቸው መረጃ ያመላክታል።

ከግንዛቤ ማስጨበጫዎች በተጨማሪ በአካባቢው ለሚገኙ አርሶ አደሮች የማዳባሪያ ድጋፍ እንደሚያደርግ ሮቤል ጨምረው ገልፀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here