የሆቴልና ቱሪዝም ማሰልጠኛ ማዕከል የ50 ዓመት ጉዞ

0
784

ከማለዳ እስከ ረፋድ
የማለዳዋ ፀሐይ ምድርን ልታሞቅ በምሥራቅ ስታጮልቅ ከወፎች ጋር አብረው እየዘመሩ ወደ ሥራቸው የሚያቀኑ የአትክልት ተራ ነጋዴዎችን፣ እቃ ጫኝና አውራጆችን እንዲሁም የአይሱዙ ሹፌሮችን በማለዳ በሯን ከፍታ የምትቀበለው, ለጎዳና ተዳዳሪዎች ቤት የሆነችው፣ መዝናናት ላማረው አገርኛ ፊልሞችን የሚያሳዩትን ሲኒማ አምፔር፣ ማዘጋጃ ቤትና ኢትዮጵያ ሲኒማን አማርጣ የምታቀርበው፣ በመስታወት ግድግዳዎች ውስጥ የብርና የወርቅ ጌጣጌጦችን በሰቀሉ ሱቆችዋ የምታጌጠው ፒያሳ በውስጥዋ ብዙ ታሪካዊ ነገሮችን ይዛለች። ከእነዚህም መካከል የአፄ ምኒሊክና የአቡነ ጴጥሮስን ሐውልት ለአብነት መጥቀስ ይቻላል።

እንዲሁም የአዲስ አበባ እምብርት በሆነችው ፒያሳ፣ ከብሔራዊ ሎተሪ አጠገብ ይህ ሁሉ ሲሆን በዓመታት መካከል ሲታዘብ የኖረ ዕድሜ ጠገብ ታሪካዊ ግቢ አለ። በዚህ ግቢ ውስጥ ባለሦስት ፎቅ የሆነው ሕንጻ በነጭ ቀለም ቢዋብም ጉስቁልናው ጮክ ብሎ ይናገራል። ከአራት ዓመት በፊት ከደረሰበት የእሳት አደጋም ገና አለማገገሙን ሁለንተናው ይገልጻል። በተለይ ደግሞ በሕንጻው ሦስተኛው ፎቅ ላይ ያለው ሰገነት እንጨቶች ተገጣጥበው፣ በሩ የተገነጠለው ክፍል ኦና ሆኖ ከውጪ ሲታይ ሕንጻው ተራ ሕንጻ ሳይሆን ስድስት መንግሥታትን ያየ፣ ታሪካዊ ቅርስ መሆኑን ለሚያውቅ ኢትዮጵያዊ መገረምና ቁጭትን ይፈጥራል። ታሪኩን ለማያውቅ የውጪ አገር ዜጋ ደግሞ በነሐሴ 1898 በንጉሠ ነገሥት እቴጌ ጣይቱ የተቋቋመውና በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ጣይቱ ሆቴል መሆኑ ቢነገረው በቅርስ አያያዛችን ሳይታዘበን አያልፍም።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከእስራኤል መንግሥት ባገኘው ድጋፍ በ1961 የተቋቋመውን የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ማዕከል 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዐል ምክንያት በማድረግ, የጉዞውን መነሻ ሜክሲኮ ያደረገው ቡድን ከተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የተውጣጡ ጋዜጠኞችን፣ ከባሕልና ቱሪዝም የመጡ ተወካዮችንና በማዕከሉ በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች የሚገኙ ሰዎችን ይዞ ግንቦት 20 ከጠዋቱ 3:05 ሰዓት ላይ በዚሁ ታሪካዊ ግቢ ውስጥ ተገኝተዋል። ይህንን ቡድን ይዘው ወደ ሆቴሉ የውስጠኛው ክፍል የዘለቁት ዕድሚያቸው በሰባዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኙት ጫንያለው ገብረ መድን የተባሉ አስጎብኚ ሆቴሉን እቴጌ ጣይቱ ለእንግዶች ማረፊያ ይሆን ዘንድ አስበው እንዳስገነቡት ከታሪክ ማኅደር እየጨለፉ አጋሩን። እንደ ጫንያለው ገለጻ በወቅቱ 500 ሴቶች እንስራ ተሸክመው ለእንግዶች መታጠቢያ ሙቅ ውሀ ለማምጣት በየቀኑ ፍል ውሃ ይወርዱ ነበር። አስተናጋጆቹም በአበሻ ቀሚስና በጃኖ ደምቀው ያስተናግዱ ነበር። አሁን ግን ይህ ባሕላዊ አለባበስ ቀርቶ የአስተናጋጆቹ ዩኒፎርም በዘመናዊ ልብስ ተቀይሯል። የሆቴሉ ወንበርና ጠረጴዛም ዘመናዊ ናቸው። ሆቴሉ ሲሰራ ለውድ ጌጣ ጌጦች ማስቀመጫ ተብሎ የተሠራው ካዝና በዋናው የሆቴሎ መመገቢያ ክፍል ስለሚገኝ ታሽጓል። በአጠቃላይ ከወለሉ ንጣፍ በቀር ሆቴሉን ዘመናዊነት ተጭኖታል።

በአንጻራዊነት የሆቴሉ የታችኛው፣ የመጀመሪያውና ኹለተኛው ወለል በጥሩ ይዞታ ላይ ቢገኝም ወደ ሦስተኛው ወለል ስንዘልቅ ግን የገጠመን የተለየ ነገር ነበር። በዚህ ወለል ላይ የሚገኘው ክፍል ውስጥ ንግስቲቷ የሚያርፉበትና ስብሰባዎች ይደረጉበት የነበረ ሲሆን አሁን ግን አቧራ የጠገበ፣ የተበላሹ የኮምፒውተር እቃዎችና ቆሻሻ ቁሳቁሶች የታጨቁበት በእሳት የተጎዳ ዘመናዊነትም ሆነ ባሕላዊነት የማይታይበት አሮጌ መጋዘን ሆኗል። ጫንያለው ይህ ክፍል እቴጌ ጣይቱና አፄ ምኒሊክ ከተማዋን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አሻግረው የሚያዩበት ቦታ እንደነበርና እርግቦችም ይኖሩበት እንደነበር ይናገራሉ። አክለውም ሐዘን ባጠላበትና ቁጭትን ባዘለ ድምጽ “አሁን ግን ያው የምታዩትን ይመስላል። የቴኒስ መጫወቻ የነበረው ቦታ ፈርሷል በአጠቃላይ አሁን ያለበት ሁኔታን ስናይ ወድሟል ማለት ይቻላል። የሚመለከተው አካል ተገቢውን ትኩረት ካልሰጠው ቅርስነቱና ታሪካዊነቱ እየደበዘዘ ሔዶ ጨርሶ እንዳይጠፋ ስጋት አለኝ” ይላሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጣይቱ ሆቴል ከሞላ ጎደል ጥሩ ይዘት ላይ ያለ ቢሆንም ታሪካዊነቱን የሚመጥን በቂ ትኩረት ግን ይፈልጋል።

የሀምሳ ዓመት ጉዞና ተግዳሮት
ሰዎች ለግል ጉዳይ፣ ለጉብኝት፣ ለስብሰባ፣ ለሥራና መሰል ጉዳዮች ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ ጊዜ የውጪ አገር ጎብኚዎችም ሆኑ ለሌላ ጉዳይ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚሔዱ ተጓዦች ምቹ የማደሪያ ስፍራ ማግኘት ቀዳሚ ምርጫቸው ነው። ይህንን የተረዱት እቴጌ ጣይቱ ለውጪ አገር ጎብኚዎች ማረፊያ ይሆን ዘንድ ነበር እቴጌ ጣይቱ ሆቴልን የመሰረቱት።
እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ከተመሠረተ ከ63 ዓመት በኋላ የተቋቋመው የሆቴልና ቱሪዝም ማሠልጠኛ ማዕከል የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በወቅቱ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ የሰለጠነ የሰው ኀይል ፍላጎት ለማሟላት ነበር። ይህ በኢትዮጵያ በሆቴልና ቱሪዝም መስክ ሥልጠና በመስጠት ፈርቀዳጅ የሆነው ተቋም ከራስ ሆቴል ጥቂት ክፍሎችን በመከራየት ነበር ሥራውን የጀመረው። የትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ኤፍራተስ ይባላሉ ነበር። ይህ ተቋም ላለፉት 50 ዓመታት ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሠለጠነ የሰው ኀይል በማቅረብ ለአገራችን የሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረከተና እያበረከተ ያለ አንጋፋ ተቋም ቢሆንም ጉዞው ግን ከተግዳሮት የጸዳ አልነበረም። ምንም እንኳን በ1989 ከመንግሥት ፈቃድ አግኝቶ ገነት ሆቴልን ለሆቴልና ቱሪዝም ማስተማሪያ ሞዴል አድርጎ በመገንባት ከሌሎች ማሠልጠኛ ተቋሞች ተማሪዎች መተው እንዲለማመዱ ፍላጎት ቢኖረውም ከመንግሥት በቂ በጀት የለም በሚል ሰበብ 20 ዓመት ሙሉ ምንም እንቅስቃሴ ሳያደርግ ጥናቱን ሼልፍ ላይ አስቀምጦ አለ። በተጨማሪም ምንም እንኳን ቀደምት ተቋም ቢሆንም ወደ ከፍተኛ ተቋም በማደግ ፈንታ ከተቋምነት ወደ ማዕከልነት ከደረጃው ዝቅ ብሏል።

በ1963 የማዕከሉ የመጀመሪያ ዓመት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል የነበሩት ብርሃኑ ሞገስ ሥልጠናው አሁን ወዳለበት ስፍራ ከመሔዱ በፊት ራስ ሆቴል ጀርባ የሚገኘውን የሆቴሉን ዋና ሥራ አስኪያጅ መኖሪያ የነበረውን ቪላ በወቅቱ የቱሪስት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ከሆኑት ሀብተስላሴ ታፈሰ ጋር በመነጋገር የሆቴል መማሪያ ክፍል እንዲሆን መደረጉን ይናገራሉ። የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበሩት ዴቪድ ኤፍራትን ጨምሮ አብዛኞቹ አስተማሪዎች እስራኤላውያን የነበሩ ሲሆን ተመራቂ ተማሪዎቹም በአገር ውስጥና በውጪ አገልግሎት መስጠት ችለዋል። አሁን ግን ይህ የማስተማሪያ ቤት ፈርሶ በምትኩ ሌላ ፎቅ ተሰርቶበታል።

የሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሠልጠኛ ማዕከል የሕዝብና ዓለማቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር የሆኑት አስቴር ተክሌ “ከዚሁ ተቋም ጋር በትብብር ሥራ የጀመሩት በኬንያና በኔዘርላን የሚገኙ ኡታሊ (utaly) ኮሌጅና ኔዘርላንድስ ቱሪዝም ኮሌጅ የተባሉ ተቋማት የኛን የትምህርት ካሪኩለም ተጠቅመው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነት ሲያድጉ, እኛ ግን ካሪኩለሙን እንዳንጠቀም ተደርገን ከተቋምነት ወደ ማዕከልነት ዝቅ ተደርጎ በቴክኒክና ሞያ ካሪኩለም እንድንጠቀም ተደርገናል” ብለዋል። ማዕከሉ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋምነት ለማደግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄው ከተመራ 3 ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አላገኘም። በመሆኑም ከዐሥራ አምስት ቀን በፊት በድጋሚ ደብዳቤና ተያያዛዥ ሰነዶችን አስገብተው በጎ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

አስቴር ተቋሙ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች በተጨማሪ ኢንደስትሪው እንደ አንድ ሴክተር ዘርፈ ብዙ ችግሮች ይታይበታል ይላሉ። ከእነዚህም መካከል አብዛኛውን ጊዜ በሆቴልም ሆነ ቱሪዝም መስክ ላይ የተሠማሩ ሰዎች በሞያው ዙሪያ በቂ ሥልጠና ያገኙ ሳይሆኑ የሌላ ሞያ ባለቤት ሆነው በዘመድ የተቀጠሩ በመሆናቸው አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ደንበኛ በሚፈልገው ደረጃ እንዳይሆን ያደርገዋል ብለዋል። አክለውም ባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ላይ የሚመደቡትም ሰዎች ስለዘርፉ ያላቸው እውቀት አነስተኛ መሆኑ ለጉዳዩ በቂ ትኩረት እንዳይሰጡ አንዱ ምክንያት እንደሆነ እቴጌ ጣይቱ ሆቴልን በምሳሌነት በመጥቀስ ያስረዳሉ።

መልካም አጋጣሚዎች
ምንም እንኳን ችግሮች ቢኖሩም የሆቴልና ቱሪዝም ኢንደስትሪው ከተግዳሮቱ ጎን ለጎን መልካም አጋጣሚዎችም አሉት። ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በቢሾፍቱ የተገነቡት ሪዞርቶች ናቸው። ከእነዚህ ሪዞርቶች መካከል ኩሪፍቱ ሪዞርት አንዱ ሲሆን በቢሾፍቱ በሚገኘው ሪዞርቱ ብቻ ለ400 ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በባሕር ዳር፣ አዳማ፣ ሰመራና ጅቡቲ በሚገኙ ቅርንጫፎቹም ለተጨማሪ ሠራተኞች የሥራ ዕድል አመቻችቷል። በተጨማሪም በኢስት አፍሪካ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውና 74 ሺሕ ካሬ ላይ ያረፈው ‘ወተር ፓርክ’ በቀጣዩ ወር ሥራ ሲጀምር በሰዓት 1985 ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን ይህም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን የቱሪስት ፍሰት ይጨምራል ተብሎ ይገመታል። ለ550 ሠራተኞችም ተጨማሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። ከኩሪፍቱ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘው ፒራሚድ ሆቴል ደግሞ 200 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን በ260 ሚሊዮን ብር ከጎኑ እየሠራ ያለው የማስፋፊያ ግንባታ ሲጠናቀቅ ደግሞ ከ200 በላይ ሠራተኞች ይቀጥራል ተብሎ ይጠበቃል።

በአጠቃላይ የሆቴሎች ግንባታ ለአርክቴክቸሮች፣ ለኢንጂነሮች፣ ለሆቴል ባለሞያዎችና ሌሎች ተያያዥ ሞያዎች የሠራ ዕድል የመፍጠር አቅም አለው የሚሉት አስቴር መንግሥት በፖሊሲ አቅጣጫ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራበት አሁን የሚያየውን የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስና የአገሪቱን ኢኮኖሚ በማነቃቃት ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ብለው ያምናሉ። በዚሁ ጉዳይ ላይም ከዛሬ ሰኔ 1 እስከ ሰኔ 3በሚከበረው የተቋሙ የወርቅ እዮቤልዮ ላይ እንደሚናገሩና ጥናታዊ ጽሁፎችም እንደሚቀረብ አስቴር ተናግረዋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here