የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቧንቧ ውሃን ሳያክሙ እንዳይጠጡ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

0
882

የዝናብ ወቅት መምጣቱን ተከትሎ በተለይም በጎርፍ ምክንያት የመጠጥ ውሃ መስመሮች መበከል ሊያጋጥማቸው ስለሚችል ኅብረተሰቡ ለመጠጥ የሚጠቀመውን ውሃ ማከሚያ በኬሚካሎች በማከም ወይም አፍልቶ እንዲጠቀም የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት አሳሰበ።

ከውሃ መበከልና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ እና አዲስ ከተማ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች በአጠቃላይ 13 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ተይዘው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

የበጋ ወራቱን ተከትሎ ከወራት በፊት በፈረቃ መሰራጨት የጀመረው የከተማዋ የውሃ አቅርትቦት የዝናብ ወቅት በመምጣቱ ደግሞ በተለይም ከማስተላለፊያ ቧንቧዎች መበላሸትን እና መዛግ የተነሳ የቧንቧ ውሃን በቀጥታ ለመጠጥ እንዳይውል ተከልክሏል። በአዲስ አበባ የተለያዩ በጎርፍ ምክንያት ባእድ ነገሮች ወደ መስመር ከመግባት ባሻገር ጎርፉ ወደ ግድቦች እንደሚገባም ይታወቃል።

በተመሳሳይ በኮሌራ ምክንያት በኦሮምያ ክልል በምዕራብ ሐረርጌ ዞን በጭሮ ወረዳ 32፣ ኦዳ ቡልቱም ወረዳ 96 እንዲሁም በበዴሳ ከተማ 10 በአጠቃላይ 138 ሰዎች ለሕመም የተዳረጉ ሲሆን የአንድ ሰው ሕይወት በበሽታው ምክንያት ማለፉም ታውቋል።

እንዲሁም በአማራ ክልል በዋግህምራ ዞን አበርገሌ ወረዳ 82፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ጠለምት ወረዳ 112፣ በበየዳ ወረዳ 3 በአዊ ዞን ጓንጓ ወረዳ 1 በአጠቃላይ 198 ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉንም አስከትሎ በትግራይ ክልል በምሥራቃዊ ዞን ከልታውላሎ ወረዳ 8 ሰዎች በበሽታው ሲጠቁ በሶማሌ ክልል ቦክሎማዮ ወረዳ 33 ሰዎች የአተት ወረርሽኝ ምልክት ታይቶባቸዋል።

በተለያዩ ክልሎች ላይ እየደረሰ ያለውን በሽታ መንስኤ ለማረጋገጥ በታካሚዎች በተወሰደው ናሙናዎች የላብራቶሪ ምርመራ ተደርጎ በአማራ ክልል 2፣ በትግራይ ክልል 2፣ በኦሮምያ 5 እንዲሁም በአዲስ አበባ 3 ሲሆን በአጠቃላይ 12 ናሙናዎች ወረርሽኙን ያስከተለው ቪብሮ ኮሌራ የተሰኘ ባክቴርያ እንደሆነ ይጠቁማሉ።

በመሆኑም ወረርሽኙ በተከሰተባቸው ወረዳዎች ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድን በቦታዎቹ ተሰማርቶ ለዚህ አገልግሎት ብቻ ተብሎ በተቋቋሙ ጊዜያዊ የሕክምና ማዕከላት ምላሽ እየሠጠ ይገኛል።

በመጨረሻም በአጎራባች አገራት ማለትም ሶማሊያና ኬኒያ የተከሰተው የኮሌራ በሽታ ወደ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ሊዛመት ስለሚችል አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገም ነው ተብሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here