በመተከል ዞን አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ስድስት ሰዎች ተገደሉ

0
875
  • በጃዊ ታስረው የነበሩ አመራሮች ተለቀዋል ተባለ

በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ቆታ ቀበሌ አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት የስድስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አራት ሰዎች መቁሰላቸው ታወቀ።

በፀጥታ ስጋት ምክንያት ባለፈው እሁድ፣ ግንቦት 25/2011 ምሽት 12 ሰዓት ተኩል አካባቢ ንብረታቸውን ይዘው ከአካባቢው ለመውጣት በመኪና በማጓጓዝ ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። ግጭቱን ለማረጋጋት በቤኔሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ አየነው በላይ ለአማራ መገናኛ ብዙኀን እንደገለፁት፣ ንብረታቸውን ጭነው እየተጓዙ በነበሩ ወገኖች ላይ ለዘረፋ የተሠማሩ አካላት ጥቃት ፈፅመዋል።

በማግስቱ አስከሬን ወደ ቤተሰብ ለመውሰድ በሚደረግ እንቅስቃሴ በነዋሪዎችና ማንቡክ በሚገኙ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መካከል ግጭት ተፈጥሮ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን የተናገሩት አሰማኸኝ፤ ሦስት ነዋሪዎች እና ስድስት የመከላከያ አባላት ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ባለፉት ጊዜያት በተካሔዱ ውይይቶች በማንዱራ እና ዳንጉር ወረዳዎች ሰላም እየሰፈነ፣ ተፈናቃዮችም ወደቀያቸው መመለስ እየጀመሩ እያለ የፀጥታ ስጋት ማገርሸቱ አሳዛኝ ነው ብለዋል አየነው።

በግጭቱ የተጠረጠሩትን በቁጥጥር ሥር የማዋል ተግባርም ሲከናወን ቆይቶ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ የማረጋጋት ሥራ 8 አመራሮች እና ሌሎች 69 ግለሰቦች ተጠርጥረው መያዛቸውን የሰላም ሚኒስቴር አሳውቆ ነበር። ቀሪ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል እየተሠራ እንደሆነ ሚኒስቴሩ መግለፁም ይታወሳል።

በተመሳሳይ፣ በአማራ ክልል በአዊ ዞን ጃዊ ወረዳ ተፈጥሮ በነበውን አሰቃቂ ጥቃት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን ተከትሎ፣ የፌደራል የጸጥታ አካላትና የተፈፀመውን ወንጀል ለመመርመር እንዲሁም፣ የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን ዘርን መሰረት ያረገ ጅምላ ጭፍጨፋ መሆኑን ለማረጋገጥ ወደ ቦታው ተጉዞ በቁጥጥር ሥር ያዋላቸውን ሰዎች በማጣራት መልቀቁ ታወቀ።
አመራሮቹን የለቀቀው ‹የአማራ ክልል መንግሥት ነው› በሚል የተሰራጨው ወሬ ስህተት መሆኑን እና የክልሉ መንግሥት እንዲህ ዓይነት አስነዋሪ ተግባር እንደማይፈጽም የክልሉ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አሰማኸኝ አስረስ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

ምርመራውን እያካሄዱ ያሉት የፌደራል የጸጥታ አካላት የታሠሩት ሰዎች ወንጀለኛ አለመሆናቸውን አጣርተው መልቀቃቸውን እና ቀጣይ ምርመራዎችንም በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስረታውቀዋል።

ከሳምንት በፊት የፌደራል የፀጥታ አካላት በገፍ አስረዋቸው የነበሩ አመራሮችን ጉዳያቸውን በፍጥነት አጣርቶ ነጻ የሆኑትን እንዲለቅ፤ ወንጀለኞችም ለሕግ እንዲቀርቡ ጥያቄ አቅርበው የነበረ በመሆኑና በዛም የተወሰኑ አለመግባባቶች እንደነበሩ ገልጸዋል። አሁን ግን በጋራ እየሠሩ መሆኑን አሰማህኝ ተናግረዋል።

ጉዳዩን ለመመርመር ወደ ስፍራው ያቀናውን ቡድን የክልሉ መንግሥት አባሯል በሚል ለሚነሱ አስተያየቶች አሰማኸኝ መልስ ሲሰጡ “የተባረረ አካል አለመኖሩንና በስፍራው ያለው የጸጥታ አካልም በሰላም ምርመራውን በማካሔድ ላይ ይገኛል” ብለዋል።

ወደ መተከል ዞን የምርመራ ቡድን ልኮ የነበረው የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን፣ ምርመራውን አጠናቆ መመለሱን የገለፁት የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ማርሴ በቅርቡ ኮሚሽኑ የጥናቱን ውጤት ይፋ እንደሚያደርም ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here