ለልማት ተነሺዎች የማኅበራዊ ትስስርና ሥነ ልቦና ካሳ ሊከፈል ነው

0
415
  • ለገጠር መሬት አማካኝ ገቢ 10 ዓመት ተባዝቶ የሚሰጠው ካሳ ከፍተኛ ገቢ በ15 ተባዝቶ እንዲሰጥ በረቂቁ ላይ ቀርቧል

በከተሞችና በገጠር ኢትዮጵያ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚፈናቀሉ ዜጎች ከመኖሪያ ይዞታቸው በሚፈናቀሉበት ወቅት ከነበሩበት አካባቢ ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወሩ ለሚደርስባቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ካሳ እንዲከፈላችው አዲስ የረቀቀው የካሳ አዋጅ ቀረበ። ረቂቁ እንደ እድር፣ ማኅበርና የመመሳሰሉ ማኅበራዊ ትስስሮች በሚቋረጡበት ወቅት በተነሺዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የሚደርስባቸው በመሆኑ ይህንንም ጉዳት ለመቀነስ ረቂቁ በገንዘብ ካሳ መስጠትን እንደመፍትሔ አስቀምጧል።

በሕገ መንግሥቱ መሰረት አዲስ የረቀቀው አዋጅ በከተማ እንዲሁም በገጠር መሬት አስተዳደር ላይ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን በወል ለሚፈናቀሉ ዜጎችም ተጨማሪ መብቶችን ረቂቁ ሰጥቷል። ከ100 በላይ ሆነው ለሚፈናቀሉ ነዋሪዎች እንደግለሰብ ከሚሰጣቸው ካሳ እንዲሁም መብቶች በተጨማሪ በወል የማቋቋም ግዴታንም ያስቀምጣል።

ተነሺዎችን ማቋቋም ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ ክልሎች ለመልሶ ማቋቋም የሚሆን ፈንድ ማቋቋም እንዳለባቸውም አዋጁ ያስቀምጣል። ይህም በአንድ ማዕከል የሚተዳደር የካሳና መልሶ ማቋቋምያ ስርአት በመዘርጋት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች እና በክልሎች የተበታተነውን አሰራር ይሰበስባል በሚል እሳቤ መሆኑን ረቂቁ ያሳያል። ይህ ፈንድ በአዋጅ ወይም ደንብ የሚቋቋም ሆኖ የገንዘብ ምንጭ ክልሎች ከበጀት ድርሻቸው የሚያዋጡት ወይም ከዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ከሚገኝ ብድር እንዲሁም ደግሞ የገንዘብ ድጋፍ ሊሆን ይችላል።

የገጠር ባለይዞታ ምትክ ተመጣጣኝ መሬት ሲሰጠው መሬቱን አልምቶ ምርት እስኪሰጠው ድረስ ላለው ጊዜ የሚቋቋምበት ድጋፍ መሬቱን ከመልቀቁ በፊት ያሉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ ሲያገኝ ከነበረው ገቢ ከፍተኛው ተወስዶ የአንድ ዓመት ክፍያ ያገኛል።

ነገር ግን ምትክ መሬት ማግኘት ካልተቻለ ከፍተኛ ዋጋው በ15 ተባዝቶ የሚሰጥ ሲሆን በቀድሞው አሰራር ግን አማካኝ ገቢ ተወስዶ በዐሥር የሚባዛ ነበር።

በመሬት በማስለቀቅ ሒደት ውስጥ ለተነሺዎች በቂ የመልቀቂያ ጊዜን ከመስጠት አንፃር በቀድሞ አዋጅ በማስለቀቅያ ትዕዛዙ መሰረት ከነበረበት በአንድ ወር በማሻሻል ወደ 4 ወር እንዲያድግ ተደርጓል። ሆኖም ያለ በቂ ምክንያት ይዞታውን ለማስረከብ ፈቃደኛ ያልሆነን ግልሰብ እንዲሁም በሕገ ወጥ መንገድ ቦታ ለመያዝ ንብረት ያሰፈረን አካል የ30 ቀን ገደብ ጠብቆ ቦታውን ለመረከብ የሚችልበት አግባብ እና የፖሊሲ ኀይልን ትብብር መጠየቅ እንደሚችልም ተደንግጓል።

አሁን በሥራ ላይ ያለው የካሳ አዋጅ በሥራ ላይ ከዋለ 13 ዓመታትን ቢያስቆጥርም ወቅታዊነት የሚጎድለው ሆኖ በመገኘቱ ለክለሳው ምክንያት ተደርጎ ተቀምጧል።

የወረዳ ወይም የከተማ አስተዳደር መሬት የማስለቀቅ ሥልጣን ቢኖረውም የንብረትና መፈናቅያ ካሳ ለመሸፈን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ያለባቸው ከመሆኑ አንፃር መሬት እንዲለቀቅለት የሚፈልግ አካል ተገቢውን ካሳና ማቋቋምያ ድጋፍ ወጪ ገቢ ማድረግ እንደሚጠቀምበት እና ተነሺዎቹም ክፍያው ካልተፈፀመ የከተማ ወይም የከተማ አስተዳደሩ የማያስለቅቅ መሆኑን ተደንግጓል።

ለተነሺው የካሳ ግምት በፁሁፍ እንዲያውቅ ከተደረገበት ቀን ጀምሮ በ3 ወር ጊዜ ውስጥ ተገቢውን ካሳ ካልተከፈለው በመሬቱ ላይ ከቋሚ ተክልና ግንባታ በስተቀር ሌሎችን ሥራዎች እንዲሁም በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ማንኛውም ሥራ መሥራት ይቻላል።

ከዚህ ቀደም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር አዋጁን በማስፈፀም ሥልጣን የነበረው ቢሆንም አንዳንድ የአዋጅ ድንጋጌዎችን ወቅታዊነት የሚጎድላቸው በመሆናቸው በጥናት መለየቱን ተከትሎ በቀጣይ ይህንን አዋጅ ለማስፈፀም በከተሞች የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም በገጠር የግብርና ሚኒስቴር እንደሆኑ ተለይተዋል።

ለሕዝብ ጥቅም ቦታ በሚለቀቅበት ጊዜ የበርካታ ዜጎች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች ኑሮ የሚነካ መሆኑን አዋጁ አስቀምጧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here