በአዲስ አበባ 5ሺሕ ሕገወጥ ቤቶች እንደሚፈርሱ ተረጋገጠ

0
1006

በአዲስ አበባ ከተማ በዐሥሩም ክፍለ ከተሞች በጠቅላላው 5 ሺሕ የሚደርሱ ሕገ ወጥ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ የማጣራት ሥራዎችን ጨርሶ በመጪዎቹ ሳምንታት ወደ ተግባር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት አስታወቀ። ከሕገ ወጥ ግንባታው በስተጀርባ በስውር ተሳትፈዋል የተባሉ ባለሀብቶች፣ የፖለቲካ ሹመኞች፣ እንዲሁም በክፍለ ከተማና ቀበሌዎች የሚሠሩ ሐሰተኛ የይዞታ ካርታ እየሠሩ የሚሸጡ ግለሰቦችን ከተማ አስተዳደሩ ግብረ ኃይል አቋቁሞ የመለየት ሥራውን እየሠራ ሲሆን የተለዩ ግለሰቦችም መኖራቸውን ጠቁሟል።

የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ለአዲስ ማለዳ በሰጠው ማብራሪያ፥ በርካታ ባለሀብቶች ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን በመፈፀም እና አነስተኛ ቤቶችን በጭቃ እና በላስቲክ በመገንባት አቅመ ደካሞችን እና ሕፃናትን እንዲኖሩበት በማድረግ እና መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንዳይወስድ እንቅፋት መፍጠራቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ሥሙ “ሰፈራ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ነዋሪዎች መኖሪያ ቤታቸው በሕገ ወጥ መንገድ መገንባቱንና በቅርብ ቀናት እንደሚፈርስባቸው እንደተነገራቸው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁ ሲሆን፥ ለሚወሰደው እርምጃም በጽሁፍ ማሳወቂያ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል። ይህን በሚመለከት አዲስ ማለዳ ከከንቲባው ጽሕፈት ቤት ያገኘችው ምላሽ እንደሚያመለክተው፤ እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ አቅራቢዎች መኖሪያቸው እንደሚፈርስ በምን እርግጠኛ እንደሆኑ መረጃ እንደሌለው እና የሚፈርሱት ቤቶች ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ በግንባር ከነዋሪዎች ጋር ያሉበት ድረስ በመሔድ ተወያይቶ መግባባት ላይ የደረሰባቸውን ቤቶች እንደሆነ ጠቁሟል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የማጣራት ሥራዎች በተከናወኑበት ወቅትም ሕገ ወጥ ናቸው በተባሉት ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትን ነዋሪዎች ግብረ ኀይሉ ያነጋገረ ሲሆን፤ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በቀጥታ ገንብተው ገቡ ሳይሆኑ ባለሀብቶችና ሹመኞች ገንብተው ለመሬት መያዣነት ያስቀመጧቸው ሰዎች መሆናቸውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።

ከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ እንደገለፀውም “የፈለገውን ያህል ሕገ ወጥ ቢሆኑም ተለዋጭ ቦታዎችን ሳንሰጣቸው ሕፃናትንና አቅመ ደካሞችን ሜዳ ላይ አንበትንም” ሲል አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ቀጥሎም ሕገወጥ ናቸው የተባሉትን ቤቶች መንግሥት ሕጋዊ እምርጃ በሚወስድበት ወቅት የፖለቲካ መጠቀሚያ በማድረግ የራሳቸውን ድብቅ አጀንዳ እና ጥቅም ለማስተጋባት የሚሠሩ ግለሰቦች እንዳሉም ጠቁሟል። በመጨረሻም ኅብረተሰቡ ከጀርባ ሆነው ውዥንብር ከሚፈጥሩ ግለሰቦች በመጠንቀቅ ከመንግሥት ጎን እንደቆምም አሳስቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here