ባልተገኘንበት ሜዳ

0
582

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የአንድነት፣ የሰላምና የፍቅር የምትባል አገራችን፤ እንግዳ ተቀባይ፣ ሰው አክባሪና ትኹት የምንባል እኛ ሁላችን ሕዝቦቿ፤ ያለሌላ የውጭ ጠላት ጣልቃ ገብነት፤ እርስ በእርስ እየተናቆርን ነው። ፍቅራችን ለባዳ፤ አክብሮታችን ለእንግዳ ነው እንጂ ለእኛ አልሆነንም። ደግሞም በተማረው ብሶ ወንድም በወንድሙ ላይ መሣሪያና ዱላ አንስቷል፤ ብቻ ምን አለፋችሁ ተጨካክነናል።

ኋላ መከራና ሐዘኑ ግን ለእናቶች ነው። ስደትና እንግልት የሚከፋው ለእነርሱ ነው። የወለዱት ልጅ በገዛ ወንድሙ የተገደለባቸውም፤ የምተባቸውም ሕመማቸው እኩል ነው። “የገደለ ባልሽ, የሞተው ወንድምሽ” ዓይነት ሆኗል። ወንድማማቾች እርስ በእርስ ይገዳደላሉ የእናቶችም ልብ ይሰብራሉ።

በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በሚነሱ ብጥብጦች ተሳትፎ የሚያደርጉት ወንዶች ናቸው። ሰው ከተገደለበት ሜዳ፣ አገር ከጠፋበት አውድማ ሴቶች አልነበሩም። ፈርተው ነው? በፍፁም አይደለም! አገራችን ስለክብሯና ሉዓላዊነቷ ባደረገቻቸው ትግሎች ሁሉ ሴቶች ነበሩ። እናት አርበኞችን፣ ብርቱ ተሟጋች ፖለቲከኞችንም አይተናል።

እናስ የፖለቲካው ትኩሳት ሳይደርስባቸው ቀርቶ ነው ድንጋይ ያልያዙት? በፍፁም አይደለም! አስቀድሞ ነገር ለብልቦ የሚፈጀው ማንን ሆነና። ይሁንና ከስሜታዊነት ርቆ ለማሰብና ለማገናዘብ ትዕግስት ስላላቸው፣ ስላለን ነው። እኩል እንድንኖር በተፈጠርንባት ምድር ላይ፤ ሕግ አውጪውም አፍራሹም፤ አስከባሪውም ረባሹም ወንድ ነው። ይህ በዓለማችን አራቱም አቅጣጫ ያለ እውነት ነው።

በነገራችን ላይ አክቲቪስቶች፣ በሐሳብ ተሟጋቾች፣ ተቃዋሚና ተቆጪ ሴቶች እንዳሉን ግልፅ ነው። እኩልነት በዚህ አይገለጥም እንጂ ከመነቋቆሪያው ሜዳ የሚገኙ ሴቶችም አሉ። በአብዛኛው ግን እውነታው ያ ስለሆነ ነው። እናትን አደባባይ አባትን ተቆጪ አድርጎ በቀረፀ ማኅበረሰብ ውስጥ፤ እርግጥም ሴቶችን በክፋትና ጥፋት ውስጥ በብዛት ማግኘት አይታሰብም። እንደውም ዓለም ይህን ጊዜ በሴቶች ብትመራ ይህ እየሆነ ያለው ሁሉ አይኖርም ነበር።

የት እንደሰማሁት እርግጠኛ ባልሆንም፤ አንድ ሰው “ዓለም በሴት ብትመራ ምን ትመስል ነበር?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ ጭቅጭቅ ይበዛ ይሆናል እንጂ ጦርነት ግን አይታሰብም አለ አሉ። እንደ ቀዝቃዛው ጦርነት ያለጥይት፣ ያለድንጋይና ያለመገዳደል ተከራክሮ፣ ተጨቃጭቆና ተሟግቶ መርታት ይቻላል።

“ሴት የላከው …” ይባል የለ!? ሴት የላከችው ሞትን እስከማይፈራ ከታዘዘ የወገኑንና የወንድሙን ሕይወትና ሰውነት ለማክበርም አይቸገርምና፤ የሥልጣን ወንበሮች ላይ እስክንቀመጥ በየቤታችን ባለሥልጣን እንሁን። በጥፋቱ ሜዳ አለመገኘታችን ነፃ አያደርገንም። ወንድሞች፣ ባሎችና ልጆቻችን ናቸው የተሠማሩትና ከደሙ ንፁሕ አይደለንም። ተባብረንና ተራምደን ለሰላም እስክንሔድ ድረስ … ወንዶቹን ለሰላም እንላካቸው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here