- ቦርዱ እቅዱን ዳግመኛ ሊፈትሽ እንደሚችል አስታውቋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ካቀረበው 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር የበጀት ጥያቄ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮኑ ብቻ ይሁንታ ማግኘቱ ተገለፀ። ቦርዱ በውጪ አገር አጥኚዎች ባስጠናው ጥናት መሰረት 4 ቢሊዮን ብር ጠይቆ የነበረ ሲሆን በቋሚ ኮሚቴው አስተያየት መሰረት ወደ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማድረጉ ይታወቃል።
በቦርዱ ተከልሶ በቀረበው በጀት ላይ ተመስርቶ የመጨረሻ ውሳኔውን የሰጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከቀረበለት ጥያቄ ላይ አንድ ቢሊዮኑን በመቀነስ ወደ ሚቀጥለው የመንግሥት አካል ማሳለፉም ታውቋል።
የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከእቅዳቸው ላይ አንድ ቢሊዮን ብር መቀነሱ አዲስ የፋይናንስ እቅድ ለማካሔድ እንደሚያስገድዳቸው ተናግረው፣ ቦርዱ ቀጣይ ሥራም ወደ ክለሳው ማምራት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።
ቦርዱ በቅርቡ አጠቃላይ የሥራ ሒደቱን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይም፣ እያካሔዳቸው ባሉ ሥራዎች ዜጎች በቦርዱ እንዲሁም በአጠቃላይ የምርጫ ሒደቱ ላይ ያለውን ተዓማኒነት ለመጨመር መታቀዱን የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረው ነበር።
ጭማሪ ላሳየው የበጀት ጥያቄም የመራጭ ሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የምርጫ ጣቢያዎች መጨመር፣ በአንድ የምርጫ ጣቢያ አንድ የነበረውን ኮሮጆ ኹለት ለማድረግ፣ በግልጽ በሚያሳዩ ኮሮጆዎች መቀየር፣ የድምጽ መስጫ ወረቀት የደኅንነት መለያ ቁጥርና የተወዳዳሪ ምስልን የያዘ እንዲሆን መታሰቡ ለጭማሬው ምክንያቶች ናቸው ተብሏል። ከዚህ ባለፈ ገለልተኛ ምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመልና ለማሰልጠን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ በመሆኑ በጀቱ ከፍ እንዲል የተደረገበትን ምክንያት ሶሊያና ያስረዳሉ።
የምርጫ በጀቱ ሲዘጋጅ የመራጮች ቁጥር 53 ነጥብ 9 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ የተገመተ ሲሆን፣ ከዚያ ውስጥ 45 ነጥብ 3 ሚሊዮኑ ለመራጭነት ይመዘገባል ተብሎ መታሰቡንም ነው ሶሊያና የገለጹት። በጀቱ በአንድ ምርጫ ጣቢያ በአማካይ አንድ ሺሕ 500 መራጭ እንደሚመዘገብና 41 ሺሕ 600 ምርጫ ጣቢያዎችንም ታሳቢ ያደረገ ነው።
ከቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ቦርዱ ለቀረቡለት ጥቄዎች በሰጠው ምላሽ አገሪቱ ምርጫን ለማድረግ ከጸጥታ እና ከተለዩ ከቦርዱ ውጪ በሆኑ ምክንያቶች ላይ እንደማይመለከተው ነገር ግን አጠቃላይ ሁኔታዎችን ገምግሞ የሚቀርብ ዓለም ዐቀፍ ባለሙያዎች ተቀጥረው ጥናት እየተካሔደ መሆኑ ተጠቅሷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘም በየአካባቢው ያለው ግጭት ደረጃና በምርጫው ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በጥናቱ ታይቶና ውጤቱን መሰረት በማድረግ በምርጫው ላይ ውሳኔ ይሰጣል ነው የተባለው።
በአሁኑ ወቅት 24 አገር ዐቀፍና 42 ክልላዊ ፓርቲዎች በአጠቃላይ 66 ፓርቲዎች ሰርተፊኬት ማግኘታቸው የገለጸው ቦርዱ ለቀጣዩ አገራዊ ምርጫ ከጠየቀው በጀት ውስጥ 900 ሚሊየን ብሩን ከተለያየቱ ዓለም ዐቀፍ አጋር አገራት ለማሰባሰብ የታቀደ ሲሆን፣ ቀሪው በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ይሆናል ብሎ እቅድ ይዟል።
ቦርዱ የሕግ ማዕቀፎችን ማሻሻል፣ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይት መድረክ ማዘጋጀትና ለፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ ማድረግ እና ከሲቪክ ማኅበራት ጋር አብሮ መሥራት ዋና ዋና ሥራዎቼ ናቸው ማለቱም ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011



