ኢዜማ “አሮጌ ሐሳብን በአዲስ ልብስ” ወይንስ “የወይን ጣዕሙ መቆየቱ”

0
1306

ጌታቸው መላኩ አንጋፋዎቹ ፖለቲከኞች በአዲሱ ትውልድ አቻዎቻቸው በአንድ ፓርቲ ውስጥ አብሮ በመሥራት ሒደት ሊያጋጥማቸው ስለሚችሉት ተግዳሮቶች የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲን እንደማሳያ በመጥቀስ ሐሣባቸውን አቅርበዋል።

 

ሰሞኑን አንድ ለውጥ ተኮር በተለይ ድርጅታዊ ለውጥ ተኮር ጉዳይ ላይ ሐሳቤን እንዳካፍ በአንድ ድርጅት ከፍተኛ አመራር ተጋብዤ ነበር። ግብዣው ሳይገርመኝ አይቀርም። “የእኔን ሐሳብ ለመጋራት የተጋበዝኩት ምን ትልቅ ነገር ሠርቼ ነው?” የሚል ሐሳብም ውስጤ ይብላላ ጀመር። ወደ አእምሮዬ ጓዳ በመዝለቅ የተለየ ነገር ፍለጋ ስባክንም ሰነበትኩ። ወደ መረጃዎቼና መጻሕፍቶቼ መደርደሪያ አልፌ ልዩ ነገር ፍለጋ ቀናትን አጥፍቼ ነበር፤ ያላስቀመጡትን ፍለጋ ማለት ይህ ነው!

ለማንኛውም ጠሪ አክባሪ ነውና ያለችኝን ለማካፈል ወስኜ ለማዘጋጀት ሳስብ ኹለት አጋጣሚዎች እንደ መልካም ትውስታዎች ፍንትው ብለው ተከሰቱልኝ። አንደኛው የማኅበራዊ ብዙኀን መገናኛ ላይ ያየሁት “በድርጅቶች አመራር መካከል የትውልድ ልዩነት ሲኖር መስተጋብሩ ምን ይመስላል? ልዩነቱ አሳሳቢስ ከሆነ ምን ማድረግ ይበጃል?” የሚል ጉዳይ ነበር። በዚህም የተለያዩ ታዋቂ የድርጅት ዘላቂ አመራር ባለሙያዎች ያወሱትን ጉዳይ ሳሰላስል ቆየሁ። በዚያ ላይም ተመርኩዤ ሐሳቤን በማደራጀት ላይ እንዳለሁ ኹለተኛው ትውስታ ከአእምሮዬ ጓዳ አለሁ አለኝ።

ይኼኛው ገጠመኝ ውጪ አገር በስደት ቆይተው የነዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቡድን መንበረ ሥልጣኑ በመቆጣጠሩ አገር ውስጥ ገብተው ከሚንቀሳቀሱትና በይፋ መክሰሙን ካወጀው አርኞች ግንቦት 7 እና አጋሮቹ ጋር የተያያዘው ነው። በርግጥ አገር ውስጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሥማቸው ይታወቅ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀደም ሲል መክሰማቸውን ማወጃቸው ቢታወቅም (ምንም እንኳን የአንዳንዶቹ የመክሰም ጉዳይ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አገጋጋሪነት ሆኖ መቀጠሉ እንዳለ ቢሆንም)። የከሰሙትን ፓርቲዎች ጨምሮ በፖለቲካ ተሳትፏቸውና በአመራርነታቸው የሚታወቁ ግለሰቦችን ጨምሮ አዲስ ፓርቲ አቋቁመዋል – የኢትዮጵያውያን ለማኅበራዊ ፍትሕ ኢዜማ ።

ይሁንና የታዘብኩት ነገር ቢኖር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ አሁንም ፊታውራሪዎቹ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት እና ከዚያም በላይ የምናውቃቸው ፊቶች ሆነው ማግኘቴ ነው። በሰለጠነው ዓለም የተለመደ እንዲያውም ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ይመስለኛል። እንደ ምሳሌ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ኦባማና ምክትላቸው ጆ ባይደን ጥምረት ይጠቀሳል። በነገራችን ላይ ጆ ባይደን አሁን ደግሞ ለፕሬዚደንትነት ለመወዳደር እየተዘጋጁ መሆኑ ይታወቃል። ይህንን ውሳኔያቸውን ተከትሎ በተለያዩ አካላት አይመጥኑም፣ በተለይ በፆታዊ መስተጋብራቸው ስርዓት ይጎድለዋል ያሉ ከሳሾች ቢነሱባቸውም እሳቸው ግን በሐሳባቸው እንደሚገፉበት አስረግጠዋል።

በእኛ አገር ግን ከባለፉት አርባ እስከ ስልሳ ዓመታት ውስጥ በፖለቲካ ትግል ሥም የምናውቃቸው ግለሰቦች አሁንም የአዲሱ ፖለቲካ ምኅዳር ዋነኛ ተዋናይ ሆነው መጥተዋል። ልምድ እጅግ ትልቅ አበርክቶ እንዳለው የማይስተባበል ቢሆንም ከላይ ያነሳሁት የትውልድና ዘመን ልዩነት እነዚህን ግለሰቦች ውጤታማ ያደርጋቸው ይሆን? የሚልም ስጋት ጭሮብኛል። ከላይ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስና ንፅፅር ለማድረግ በመሞከር እነዚህ ዘመናትን የተሻገሩ አንጋፋ ፖለቲከኞች በአዲሶቹ ፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ሊገጥማቸው የሚችለውን ተግዳሮቶች ለማመላከት ልሞክር።

የአመራር ተመክሮ
እንደኢዜማ ዓይነት አዳዲስ ፓርቲዎችን በነባር መሪዎች ጠርናፊነት ወደ ሜዳው ከገቡ ሊከሰቱ የሚችሉ ተግዳሮቶችን ከመልካም አጋጣሚዎቻቸው መሳ ለመሳ ለማንሳት ልሞክር። ተግዳሮታቸው የትየለሌ ናቸው ብለው የሚከራከሩ ብዙዎች አሮጌን ሐሳብ አዲስ ልብ አልብሶ ማምጣት ሲሉት፤ የነባር ፖለቲከኞችን ተሳትፎ የሚደግፉት አካላት ደግሞ “የወይን ጠዕሙ መቆየቱ” በማለት ይከራከራሉ። በዚሁና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ምርምር አድርገው አበርክቷቸውን ካጋሩን ባለሙያዎች ሥራ አንጻር ማየት ለግንዛቤም ለገንቢ ትችትም ይጠቅማል እላለሁ።

በመጀመሪ ደረጃ የትውልድ ልዩነት በሚንፀባረቅበት ተቋም ውስጥ የሚንፀባረቁጽ ችግሮች መነሻቸው የልምድና ተመክሮ ጉዳይ ነው። ቀዳሚው ትውልድ በአብዛኛው ኑባሬያዊና ተዋረድን የጠበቀ አመራርና አሠራር ለማስፈን እንደሚጥር የስትራቴጂ ሊቁ ፒተር ሴነጄ (ዶ/ር) ሲናገሩ፤ የኋለኛው ትውልድ ደግሞ በአመራር ፍልስፍናው ከፈጣንና ልዩነትን የሚፈጥሩ እርምጃዎች ላይ ያተኩራል። ይህም በፒተር ሴነጅ አገላለፅ (Traditional/Hierarchical leadership Vs. Dynamic and Breakthrough leadership) ይባላል።

እንደዚህ ምሁሩ አገላለፅ በጣም ጥቂት መሪዎች ዘመን ተሻጋር የሚባለውን ኹለቱን እሳቤዎች የማቀናጀትና የመጠቀም አቅም ሲኖራቸው ብዙ መሪዎች ግን ሲቸገሩ ይስተዋላል። በሆኑም በነባር አመራሮች የሚመሰረቱት አዳዲስ ፓርቲዎች የኹለቱን ዘመን ጠቀስ እሳቤና ልዩነቶች የማቻቻል አቅምና ችሎታቸው መፈተኛ የቤት ሥራዎቻቸው ይሆናሉ።

ኹለተኛው የቀዳሚው ትውልድ በአዲስ ትውልድ ፓርቲዎች ላይ የመሳተፍ ተግዳሮት የእሳቤ አድማስ (imagination) ላይ ያለውን ልዩነት በማንፀባረቅ ላይ ያተኮረ ነው። የእሳቤ አድማስ የነገሮችን ኹለንተናዊ ቁመና (ስፋት፣ ጥልቀት፣ አስቸኳይነት፣ ምስጢራዊነት፣ ጊዜ ተሻጋሪነትና) የመሳሰሉትን ነገሮች ያካተተ ነው። በመሆኑም ይህ የእሳቤ አድማስ ልዩነት የጉዳዮችን ትርጉም በግልፅ በትውልዱ መካከል ይፈጥራል። ይህም ለመግባባትና ልዩነትን ለማቻቻል የሚደረጉ ጥረቶች ጥግ ድረስ የመጓዝ ፈቃደኝነት ኖሮ መልካም መግባባት ቢኖርም፤ ሁል ጊዜ የሚሳካ ጉዳይ ሊሆን ስለማይችል ልዩነቶች ከባድ ሆነው በሚመጡበት ጊዜ ድርጅታዊ አቋም ሊፈተሽ ይችላል።

ለውጥን በበጎ የመመልከትና የመሻት ጉዳይ (adaptation to change)
ለውጥ የማይቀር ጉዳይ እንደሆነ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ የማትቀረውን ለውጥ መፍራት ወይም ለመከላከል መሞከርን ነባራዊ ተቃርኖ (Existing paradox) ይሉታል። ምሁራን የመሪዎችን ሥራ መፈተሻ መሰንክልም ይኸው ለውጥ እንደማይቀር እየታወቀ የሚፈተር መከላከል ነው። ምሁራን በለውጥ ጊዜ የሚተሉትን የመከላከል ተግባራትን የማክሸፊያ መንገዶች ብለው ካስቀመጧቸው ስልቶች መካከል የለውጥ አካላትንና ተዋንያንን የስሜት ደረጃ በመከታተል ኀለፊነትን መወጣት የሚለው ቀዳሚ ቦታ ይሰጠዋል። በመሆኑም ተዋንያንን የመምራት ጉዳይ እጅግ አስፈላጊና ስትራቴጂዊ ጉዳይ ይሆናል ማለት ነው። ይህም ለውጥን በበጎ ለመመልከት የመሻት ሁኔታን ይፈጥራል።

አሮጌ ሐሳብን በአዲስ ልብስ የመምጣቱ ፍርሃት
ከግማሽ ደርዘን በላይ ፓርቲዎች ከስመን ኢዜማ የሚባል አዲስ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ አቋቁመናል ካሉን ሳምንታት ተቆጥረዋል። በዚህም ጊዜ አንደ ሁል ጊዜው በርካቶች በተስፋ ጥቂቶች ደግሞ በጥርጣሬ ከዚያም ያነሱት ደግሞ በፍርሃት ጊዜ የሚያመጣውን እየጠበቁ ይገኛሉ። ተስፈኞቹ በአብዛኛው ትንታኔ ሳይኖራቸውና ሳያሻቸው “መልካሙን ነገር የሚያመጣው ፈጣሪ ነው” ብለው የሚያምኑ እንደሆነ ያደረኩት ጥቂት ግምገማ አሳይቶኛል። ቀሪዎቹ በአዲሱ ፓርቲ መሪዎች ልምድና ተመክሮ የሚተማመኑ ይመስላሉ። በጥርጣሬ ሁኔታውን የመከታተሉት ደግሞ የአገራችን ፖለቲካ ከልምድ ከሚገኝ ብስለት ይልቅ ደራሽ ስሜት የሚነዳው ሆኖ ስላገኙት መጠርጠርን መርጠው የሚጠባበቁ ይመስላሉ። እነዚህ አካላት ሁኔታዎች ባይሳኩ ማንንም ምክንያት አድርገው ማማረር የሚፈልጉ አይመስሉም። ይልቁንም በሒደት ሌላ አማራጭና ችግር መፍቻ ዘዴን የሚስቡ ይመስላሉ። “ፈሪዎቹ” የሰለባዎች ሥነ ልቦና ምርኮኛ የሆኑ ይመስላል። በእነዚህ ግለሰቦች ላይ ሐሳብ የመስጠት ማንም የሞራል የበላይነት ያለው አይመስለኝም። ይልቁን ጠባሳቸው ለሌሎች ትምህርት ሆኖ እንዲታይ መፈለግ አዝማሚያ ያሳያሉ።

በመጨረሻም የለውጡ ሒደት በግለሰብ አመራር ላይ ብቻ የሚንጠለጠል እንዳልሆነ ይታወቃል። ነገር ግን የመሪዎች ግንዛቤና አቋም ደግሞ ዓይነተኛ ጉዳይ ነው። በመሆኑም የአዲሱ ፓርቲ መሪ ነባር ታጋዮች ዘመናቸውን መዋጀት ዋነኛ ሥራቸው መሆኑ ይሰማኛል። መጽሐፉም ዘመኑን ዋጁ ይለናልና፣ ዕዩት መርምሩት አስፈላጊውን ጉዳይ ለዩና ሥሩበት ማለት የመስለኛል።
ልቡና ለመሪዎቻችን ዘመናቸውን እንዲዋጁ!!

ጌታቸው መላኩ (የሚዲና ተግባቦት አማካሪ)
[email protected]

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here