የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረግ ሽኩቻ

0
1533

የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት የውጪ ምንዛሬ እጥረት መታመም ከጀመረ ዋል አደር ብሏል። አንዴ ከፍ ሌላ ጊዜ ዝቅ ሲል የነበረው የዶላር አቅርቦት፣ ላለፉት ተከታታይ ወራት አቅረቦት የበለጠ እየከፋ መምጣቱን የትይዩ ገበያን የምንዛሬ ምጣኔ ብቻ በማየት ማወቅ ይቻላል። ሳምሶን ብርሃኔና አሸናፊ እንዳለ ገበያውን በመቃኘት፣ ተዋናዮቹን በማናገር እንዲሁም የመስኩን ምሁራን በማስተቸት ‘የውጪ ምንዛሬ ሽኩቻ’ ገፊ ምክንያቶችን ከመጠቆም እና ከማስተንትን ባሻገር የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦችንም አካተው የሐተታ ዘማለዳ ጉዳይ አድርገውታል።

ሙስጠፋ መሐመድ ሰሊጥ መነገድ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። ለባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለራሱ ድርጅትና ሌሎች ወደ ውጪ አጋር ላኪዎችን በመወከል ተገበያይቷል። በዚህ ወቅት እርሱም ሆነ የሚወክላቸው ድርጅቶች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰሊጥ ወደ ውጪ በመላክ ለአገራቸው ቀላል የማይባል አሰተዋፅዖ አድርገዋል።

በቅርቡ ግን ያጋጠመው የቀድሞ የንግድ እንቅስቃሴውን የሚፈታተን ነው። በአገሪቱ ያለው የውጪ ምንዛሬ ተከትሎ ከፍተኛ የሰሊጥ ዋጋ ንረት በምርት ገበያው ተከስቷል። ይባስ ብሎም በታሪክ ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ሁኔታ ዋጋው ከእጥፍ በላይ ከመጨመሩ በላይ 7 ሺሕ 277 በኩንታል ሲደርስ ነበር ሙስጠፋ ጉዳዩ ከቁጥጥር ውጪ መሆኑን ያወቀው።

መቼም ሰሊጥ በአገር ውሰጥ ተፈላጊነቱ እምብዛም በመሆኑ ታዲያ ይህን ምን ጉዳት አለው ተብሎ ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ጉዳዩ ቀላል እንዳልሆነ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የውጪ ምንዛሬ ለማግኘት የሚደረገውን ሽኩቻ ለተረዳ ለማንኛውም ሰው ቀላል ነው።

በተለይም ባለፉት ሦስት ወራት መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የዶላርና ሌሎች ዋና ዋና መገበያያዎች ክምችት ጥሩና በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ቢልም ከፍተኛ የዉጪ ምንዛሬ እጥረት ተከስቷል። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የሚገኙ ነጋዴዎች የግብርና ምርቶች በኪሳራ ወደ ውጪ በመላክ በሚያገኙት የውጪ ምንዛሬ ዕቃ በማስመጣት ተግባር ላይ ተጠምደዋል።

በኩንታል እስከ 60 በመቶ እየከሰርን ነው ወደ ውጪ እየላክን ያለነው ይላል ሙስጠፋ በተለይም የምወክላቸው ነጋዴዎች በምንም ዋጋ ቢሆን ሰሊጡን አግኝተው በኪሳራ ወደ ውጪ በመላክ የዶላር ፍላጎታቸውን ማሳካት ነው የሚፈልጉት ሲል ያስረዳል።

በርግጥ የዶላር እጥረት በኢትዮጵያ ሲያጋጥም ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ችግሩ ለዐሥርት ዓመታት የቆየ እና ሥር የሰደደ መሆኑ የአደባባይ ሐቅ ነው።

በተለይ ላለፉት ሰባት ዓመታት የውጪ ንግዱ እና ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ምርት አለመመጣጠንን ተከትሎ እየሰፋ ያለው የንግድ ጉድለት ችግሩን አባብሶታል። በተጨማሪም አገሪቷ አጠቃላይ ምርት ከተፈጠረው ፍላጎት ጋር አለመመጣጠኑ ለውጪ ንግድ በር መክፈቱ እጥረቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።

አንዳንዶች በኢትዮጵያ የኮንትሮባንድ ንግድ፣ የትይዩ ገበያ፣ የሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር መስፋፋትና የጨለማው ምጣኔ ሀብት ዕድገትን በመግለጽ በኢትዮጵያ ያለው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ሰዋዊ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ችግሩን ፍላጎትንና አቅርቦት ለማመጣጠን የሚሆን ፖሊሲ አለመኖሩን እንደ ምክንያት ያነሳሉ።

በትይዩ (ጥቁር) ገበያው ውጪ ምንዛሬ ለመሰብሰብ የሚደረገው ሽኩቻ
አለሙ ጌታሁን (ለደኅንነቱ ሲባል ሥሙ የተቀየረ) በኢትዮጵያ ሆቴል ጀርባ ከሚገኙት ሱቆች መካከል የአንዱ ባለቤት ነው። ለሥሙ ሱቅ ይኑረው እንጂ አንድም ቀን ልብስ ለመሸጥ ጓግቶ አያውቅም።

የንግድ ፈቃድ ከንግድ ቢሮ ያገኘው ልብስ ለመሸጥ ቢሆንም አልፎ አልፎ በተባራሪ ካልሆነ አንድም ቀን ይህንን አድርጎ አያውቅም።

እንደሌሎቹ በአካባቢው የሚገኙ የሱቅ ባለቤቶች እነርሱም ውጪ ምንዛሬ በመሸጥ ላይ ነው ሕይወቱን መሰረት ያደረገው። ታዲያ ምንም እንኳን ይህንን ሕገወጥ ተግባር ሲፈጽም የጥቁር ገበያ እንዲቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ብሔራዊ ባንክ በ500 ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ሱቁ ውስጥ ቢሆንም ለዓመታት አቁም ያለው ማንም አልነበረም።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን በመጡ ወራት ወሰጥ በተወሰደ ድንገታዊ አስተዳደራዊ እርምጃ ለጊዜውም ቢሆን ሱቁን ለመዝጋት ተገዶ ነበር።

ብዙዎቹ ጓደኞቹም በመታሰራቸው የተነሳ ለጥቂት ቀናትም ቢሆን በአዲስ አበባ ዋነኛ የትይዩ ገበያው በሆነው ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢ እንቅስቃሴ አልነበረም ነበር።

ከተወሰደው አሰተዳደራዊ እርምጃ በተጨማሪ በጥቂት ሰዎች መንግሥት የዶላር ምንዛሬ ሊቀንስ ነው ተብሎ በመወራቱ የትይዩ ገበያ ተቀዛቅዞ ነበር። በዚህም የተነሳ ዶላር በትይዩ ገበያው እስከ 27 ብር ሲሸጥና ከዋናው የውጪ ምንዛሬ ገበያ ጋር ያለውም ልዩነት እስከ 20 ሳንቲም ደርሶ ነበር። ይህ ግን ሊቆይ አልቻለም።

አሁን መንግሥት አስተዳደራዊ እርምጃ ከወሰደ 10 ወራት አልፎታል። የውጪ ምንዛሬ በታሪክ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። በአሁኑ ወቅት ዶላር ከ41 ብር 50 ሳንቲም በላይ በጥቁር ገበያ እየተሸጠ ሲሆን ይህ በባንኮቹ ውስጥ ካለው ግብይት ጋር ሲነጻጸር ከ11 ብር በላይ ጭማሪ አለው።

የምጣኔ ሀብት ባለሞያዎች ይህ ዓይነቱ ልዩነት በአገሪቱ ያለው የውጪ ምንዛሬ እጥረት ከቁጥጥር ውጪ መድረሱን የሚያሳይ ነው ይላሉ። ከእነዚህም መካከል የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቴዎድሮስ መኮንን (ዶ/ር) አንዱ ናቸው። ቴዎድሮስ በአንድ አገር ላይ በዋናው የውጪ ምንዛሬ መገበያያ ዋጋ እና በትይዩ ገበያው መካከል ከ2 በመቶ በላይ ልዩነት ካለ በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ውስጥ ትልቅ ችግር አለ እንደማለት ነው ይላሉ። ነገር ግን አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ልዩነቱ ከ35 በመቶ በላይ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የትይዩ የውጪ ምንዛሬ ግብይቶች በመርካቶ፣ ካዛንችስ፣ ኢትዮጵያ ሆቴልና ጋንዲ ሆሰፒታል አካባቢ በግልጽ ይካሔዳሉ። በአዲስ አበባ በትይዩ ገበያ ዋነኛ ተዋናዮ በትናንሽ ሱቆች ባሻገር የባንክ ቅርንጫፍ ኀላፊዎችና ገንዘብ ከፋዮች ናቸው።

አነስተኛ የሆኑ ትይዩ ገበያውን ዋጋ መሰረት ያደረጉ ውጭ ምንዛሬዎች በባንክ ቅርንጫፎች ደረጃ በሚገኙ ገንዘብ ከፋዮች በሕገወጥ መልኩ እንደሚፈፅም አዲስ ማለዳ በአንዳንድ ባንኮች ያደረገቻቸው ምልከታ ያሳያል።

ይህን ሽያጭና ግዢን ያካተተ ሲሆን ይህንን ተግባር ለመፈፀም በባንክ ሠራተኞች መካከል የውጭ ምንዛሬ መስኮት ላይ ለመሰየም ሽኩቻ እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል። አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኛ፤ የውጭ ምንዛሬ መስኮት ላይ የሚቀመጡ ሠራተኞች ከሌላው በተለየ መልኩ የተሻለ ኑሮ እና ገንዘብ ያላቸው ሲሆን አንዳንዴም በቀን እስከ 50 ሺሕ ብር በላይ እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ከፍተኛ የሆኑ ትይዩ ገበያን ዋጋ መሰረት ያደረጉ የውጭ ምንዛሬዎች በባንክ ኀላፊዎች እና በውጭ ምንዛሬ ዳይሬክተሮች የሚፈፀም ሲሆን ግብይቱ በአብዛኛው በትላልቅ ሆቴሎች እንደሚካሔድ በተለያዩ ባንኮች የሚሠሩ በጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይገልፃሉ። የውጭ ምንዛሪው ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለማንቀሳቀስ ቪትዝ መኪና በብዛት ተግባር ላይ እንደሚውል አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃም ያመለክታል።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ የባንክ ከፍተኛ ሥራ ኀላፊዎች የውጭ ምንዛሬ ፈላጊዎች ቅድሚያ በመስጠት በብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠው መሸጫ ዋጋ ከፍ በማድረግ ትርፍ ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉ በዘርፉ ላይ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች ያነሳሉ። አንድ ዶላር በብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠለት ዋጋ ላይ ስምንት ብር ድረስ ጭማሪ ተደርጎበት በባንኮች ውስጥ ግብይት እንደሚፈፀም አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነጋዴዎች ይገልፃሉ።

ይህ ዓይነቱ በትይዩ ገበያው የሚታየው የውጭ ምንዛሬ ትንቅንቅ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያነሳሉ። አይ ኤም ኤፍ የሚባለው በዓለም ዐቀፍ የገንዘብ ተቋም የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የትይዩ ገበያ በአንድ አገር የሚሰፋው የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱና ፍላጎቱ መካከል ከፍተኛ ልዩነት ሲኖር ነው።

በትይዩ ገበያው የሚቀርበው ዋጋ ከፍተኛ መሆን ለማደጉ ሌላ ምክንያት ነው። አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የወጋገን ባንክ ከፍተኛ ሥራ ኀላፊ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ለማንም ሰው ቢሆን በዓመት በቁጠባ ወለድ 7 በመቶ ገቢ እያደገ፤ የውጭ ምንዛሬ ከብር ጋር ያለው ልዩነት ከዋጋ ግሽበት በላይ በሚጨምርበት አገር ትይዩ ገበያው አዋጭ ነው። ይህ ማለት ገንዘብ በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ በዶላር ለውጦ ማስቀመጥ ይሻላል ማለት ነው።

በሌላ በኩል በአገሪቷ ያለው የንግድ ጉድለት ከ14 ቢሊዮን ዶላር በላይ በመሆኑ ይህንን ክፍተት ለሟሟላት አለመቻሉ አንዱ የትይዩ ገበያው መሥፋት ምክንያት ነው።

በተለይም የውጭ ምንዛሬ ተመን በመንግሥት የሚወሰን ከሆነ የትይዩ ገበያ የመስፋፋቱ ዕድል ሰፊ ሊሆን እንደሚችል መገመት አዳጋች እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

ዳንኤል ደበሌ የተባሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሐሙስ፣ ግንቦት 29/2011 በተዘጋጀ ውይይት ላይ እንደገለፁት ለ40 ዓመታት በሥራ ላይ የዋለው የውጭ ምንዛሬ ስርዓት ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት ነው። የውጭ ምንዛሬ ስርዓቱ ነፃና ገበያ መር ካልሆነ ችግሩ አይፈታም የሚሉት ዳንኤል መንግሥት ለጉዳዩ ነገ ዛሬ ሳይል ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል እጥረቱን የፖሊሲ ለውጦችን በማምጣት ማስተካከል እንጂ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ እንደማይቻል የፋይናንስ ባለሙያው አቡዱልመናን ሙሐመድ ያነሳሉ።

ለአብነትም እንደ የትይዩ ገበያው ህጋዊ ማድረግን እንደ መፍትሔ እንዱልመናን አንስተዋል።

የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ተኬ አለሙ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ። ‹‹ሕገወጡን የዶላር ገበያ ሕጋዊ ማድረግ እና በነፃ ገበያ እንዲነገድ ማድረግ እጥረቱን ለመፍታት መፍትሔ ነው›› ይላሉ ተኬ ከስድስት ወራት በፊት በኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው ባወጡት ፅሁፋቸው። በተለይም ትይዩ ገበያ ህጋዊ ሲሆን ለቁጥጥር እንዲመች በማድረግ ታክስ እንዲከፍሉ ማስገደድ ይችላሉ ብለዋል።

ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። ትይዩ ገበያውን ሕጋዊ ማድረግ ለዋጋ ግሽበት አገሪቷን ያጋልጣል የሚሉት ዓለማየሁ ይህ ዓይነቱ እርምጃ ቢወሰድ ባንኮች የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ከመግባታቸው በላይ እጥረቱን ለመፍታት መፍትሔ አይሆንም ይላሉ።

በሌላ በኩል አሁን በሥራ ላይ ያለው በእውቀት የሚመራ የዶላር ገበያ ስርዓት (managed floating) መቀየር እንደ መፍትሔ ይነሳል። እንደ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቴዎድሮስ ገለፃ የውጭ ምንዛሬ ገበያ ጣሪያና ወለል በማስቀመጥ በፍላጎትና አቅርቦት እንዲመራ መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ።

የግብርና ምርቶችን በርካሽ በመሸጥ የሚደረግ ሌላ ሽኩቻ
የግብርና ምርቶች የአጠቃላይ የአገሪቷን የውጪ ንግድ ከ70 በመቶ በላይ ይሸፍናል። ይህንን ያህል አስተዋጽዖ ቢያበረክትም በሚያመጣው የውጭ ምንዛሬ አንፃር ሚናው እምብዛም ነው። ከግብርና ምርቶች ከፍተኛው ድርሻ የሚይዘው ቡና ሲሆን ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎችና ጥራጥሬዎች ይከተላሉ።

እነዚህን የግብርና ምርቶች ወደ ውጪ በመላክ የተሰማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ነጋዴዎች ያሉ ሲሆን ለአገሪቷ ከሚያመጡት የውጭ ምንዛሬ ይልቅ የሚያመጡት ጉዳት እንደሚበዛ በተደጋጋሚ ይነሳል። በሰሞኑ የተከሰተው የኪሳራ ሽያጭ ለዚህ እንደማሳያ ይነሳል። በዚህ የተነሳ በአገሪቷ ባለው ውጭ ምንዛሬ እጥረት ተከትሎ በተከሰተ ያልተገባ ፉክክር የተነሳ የኢትዮጵያ ግብርና ምርቶች ከዓለም ገበያ አንፃር በከፍተኛ ሁኔታ ዋጋ መቀነስ አሳይተዋል።

ለአብነትም ውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሲባል ላኪዎች ከቶን እስከ 300 ዶላር ሲከስሩ የሰሊጥ ነጋዴዎች በቶን እስከ 700 ዶላር እየከሰሩ ይሸጣሉ። በተለይም በዓለም ዐቀፍ ገበያ ከተከሰተው የግብርና ምርቶች ዋጋ መቀነስ ጋር ተዳምሮ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል። ለምሳሌ በ15 ዓመታት ውስጥ አነስተኛው ዓለም ዐቀፍ የቡና ዋጋ በባለፈው ወር የተመዘገበ ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ አገራት ምርት መጨመር ጋር ተያይዞ ሰሊጥም ሊረክስ ችሏል።

ግንቦት 29/2011 የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር ባደረገው ውይይት ከቡናና ሰሊጥ ባሻገር የቁም እንስሳቶችና ሌሎች የቅባት እህሎች በአገር ውስጥ ገበያ የተጋነነ ዋጋ እየተሸጡ ነገር ግን ወደ ውጪ በኪሳራ እንደሚላኩ ተገልጾ ነበር። “ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ነው” ሲሉ ሚኒስቴሩ ተናግረው ነበር።

አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የቡና ነጋዴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከውጪ ዕቃ ለማስመጣት ዶላር ለማግኘት ሲባል በዘርፉ ላይ እንደተሰማሩ ይገልፃሉ። ላኪዎች በውጪ ንግድ ያገኙትን 30 በመቶ የውጭ ምንዛሬ ዕቃ ለማስመጣት መጠቀም እንደሚችሉ የሚያትተውን የብሔራዊ ባንክ ሕግን ለመጠቀም ወደ ዘርፉ እንደገቡ ነጋዴው ይናገራሉ።

በዚህ ተግባር የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ በመጠቀም በከተማው ውስጥ የሌሉ ምርቶችን በማስመጣት ተግባር እንደተሰማሩ ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል። በተጨማሪ በሌሎች ዘርፉ ላይ (በመኪና እና መለዋወጫዎች ማስመጣት) ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ካለው ውጪ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ግብርናና ምርቶች መላክ እንደተሰማሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ይህ ዓይነቱ ተግባር በሙያው ለብዙ ዓመታት የቆዩት ነጋዴዎች ከገበያ ውጭ እንዳያደርግ ተሰግቷል። በቅርቡ በላይነህ ክንዴ አስመጪና ላኪ በምርት ገበያ የሚያደርገውን የሰሊጥ ንግድ ለጊዜው ማቆሙን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል። ይህን የተመለከቱት ሰሊጥ ነጋዴው ሙስጠፋ የአገሪቷ የወጪ ንግድ ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ችግር ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ያመለክታሉ። “ከውጭ ገዢዎች ጋር ለመደራደር ያለንን አቅም አሳይቶናል” ይላሉ ሙስጠፋ።

ይህንን ችግር መንግሥት ሊፈታ አለመቻሉን የንግድ ኢንዱስትሪ ሚኒስትሯ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር አምነዋል። ለዚህም መንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ችግሮችን እንደ ምክንያት አነስተዋል። ይሁን እንጂ ከማስተካከያዎች በኋላ እርምጃ እንደሚወስዱ ሚኒስትሯ አስጠነቅቀዋል።

እርሳቸው ይሁን ይበሉ እንጂ፤ ባለሙያዎች እንደሚገልፁት ጉዳዩ ሥር ነቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ ያስፈልገዋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ቴውድሮስ በበኩላቸው ወደ ውጪ ምርት የሚልኩ ነጋዴዎች አለመበረታት መደረግ ካለባቸው ለውጦች መካከል መሆን አለበት ይላሉ።

የተለያዩ ሕጎችን በማውጣት አስመጪዎች ወደ ሌላ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ ማድረግ መንግሥት ይኖርበታል ሲሉ ቴውድሮስ ይገልፃሉ። በተጨማሪም የተለያዩ ምርቶችን ወደ ውጪ የሚልኩ ነጋዴዎችን የሰበሰቡትን የውጭ ምንዛሬ እንዲጠቀሙ የ30 በመቶ ገደብ ሊነሳላቸው አልያም ድርሻቸው ላይ ከፍተኛ ማስተካከያ ሊደረግ ይገባል ሲሉም ቴዎድሮስ ሐሳባቸውን አክለዋል።
በሌላ በኩል፤ አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ቦርድ አባል በበኩላቸው እንድ ቡና፣ ሲሊጥና አተር የመሳሰሉ የግብርና ምርት አቅራቢዎች ምርት ዋጋ ይጨምራል ብሎ በማሰብ ከፍተኛ ምርት ማከማቸታቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ችግሩን አባብሶታል ይላሉ።

ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር
በኢትዮጵያ ድንበርን አቋርጠው በአየር ወይም በየብስ የውጭ ምንዛሬ ይዘው ሊወጡ ሲል የሚያዙ ሰዎችን መስማት የተለመደ ነገር ከሆነ ሰንበትበት ብሏል። በጫማ፣ በቦርሳ፣ በሰፊ ልብስ ውስጥ በመሾጎጥ እና በመኪናዎች ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ከፍሎች ውስጥ በመደበቅ የውጭ ምንዛሬ ይዘው ሊወጡ ሲል የተያዙ ሰዎችን ታሪክ መስማት የተለመደ ነገር ሆኗል። የሚያዙት የውጭ ምንዛሬዎች ግን የሚፈፀመውን የሕገውጥ ምንዛሬ ዝውውር አንድ በመቶ እንኳን አይሆንም ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከውጭ ምንዛሬ ሕገወጥ ዝውውር ጋር የተያያዙ ከ300 በላይ ጉዳዮች በፍርድ ቤቱ የታየ ሲሆን ዐሥሩ ሲፈረድባቸው 99 የሚሆኑት ጉዳዮች አሁንም እየታዩ ነው። ጉዳዮች እያንዳንዳቸው ከ50 ሚሊዮን ብር እስከ 300 ሚሊዮን ብር የሚጠጉ የሕገወጥ የውጪ ምንዛሬ ዝውውር ያካትታሉ።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከኢትዮጵያ በዓመት ከአራት ቢሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ይወጣል። ይህ ከአገሪቷ የወጪ ንግድ ጋር ሲነፃፀር ከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ከፍ ያለ ነው። የአገሪቷን በጀት አንድ ሦስተኛ ያክላል።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚገልፁት በአገሪቷ የእጅ በእጅ ገንዘብ መር ግብይት መኖሩ ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር መናር አንድ ምክንያት ነው። በተለይም በኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከ100 ሚሊየን ሕዝብ 25 በመቶ እንኳን ባለመሆናቸው የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠርና የዶላር ዋጋ ጭማሪ ከዋጋ ግሽበት ከፍ ያለ መሆኑ የሕገወጥ ዝውውር እንዲስፋፋ ምክንያት ሆኗል።

በሌላ በኩል፤ ነጋዴዎችና ባለሀብቶች በአገሪቷ ገንዘብ የመግዛት አቅም ላይ ያላቸው ዓመኔታ አነስተኛ መሆኑ የሚያገኙትን ገቢ ወደ ወጪ ምንዛሬ በመቀየር ወደ ውጪ አገራት አውጥተው ለሌላ ተግባር እንዲያውሉት ወይም በሌሎች አገራት ባንክ እንዲያስቀምጡት ምክንያት ነው። አንዳንዴም በአገር ውስጥ የሚፈፀሙ ግዢዎች ክፍያቸው በውጭ አገራት ውስጥ መፈፀሙ ሌላው የሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር መስፋት ምክንያት ነው።

ነገር ግን ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በላይ ዋነኛው የኮንትሮባንድ ንግድ መስፋፋት ነው። የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኮንትሮባንድ ንግድ ከ55 በመቶ እስከ 80 በመቶ ያለውን የሕገወጥ ንግድ ዝውውር ይሸፍናል። አሁን ላይ የተከሰተው ከዚህ የተለየ አይደለም።

በአገሪቷ ካለው እጥረት ጋር ተያይዞ ነጋዴዎች የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሬ ሙሉ ለሙሉ ለመሰብሰብ ሲሉ በድንበር በኩል ከአንዳንድ ባለሥልጣናት ጋር በመመሳጠር ወደ ውጪ እንደሚልኩ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተለይም በሕጋዊ መንገድ ከሚልኩት ላኪዎች ከውጪ ንግድ ሽያጭ የሚያገኙትን 30 በመቶ ብቻ ለተለያዩ ግዢዎች እንዲጠቀሙ መፈቀዱ ፊታቸውን ወደ ኮንትሮባንድ እንዲያዞሩ እንደገፋፋቸው በተደጋጋሚ ይገልፃሉ። ለአብነትም፤ የሰሊጥ ነጋዴዎች ምርቶች ከገበሬ ቀጥታ በመግዛት ወደ ሱዳን እንደሚሸጡ የዘርፉ ተዋናዮች ይገልፃሉ። በሺዎች የሚቆጠሩ ከብቶችም በየቀኑ በሕገወጥ መንገድ በአገሪቷ አራቱም አቅጣጫ ይወጣሉ።

የውጭ ምንዛሬ እጥረቱን መፍታት ይቻላል?
የውጭ ምንዛሬ እጥረትን እንደ መፍታት ለመንግሥት የሚከብድ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እጥረቱ ሲከሰት አዲስ ባይሆንም ለባለፉት ኹለት ዓመታት የታየው ችግር ግን በዓይነቱ ገዘፍ ያለ ነበር። በተለይም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣን ሊወርዱ አካባቢ እጥረቱ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ነበር። በወቅቱም የነበረው የውጭ ምንዛሬ ክምችት የአገሪቷን የአንድ ወር ከውጭ የሚገቡ የሸቀጦች ፍላጎት የሚያሳካ አልነበረም።

ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወራት በኋላ ግን ችግሩ ለጊዜውም ቢሆን ሊፈታ ችሎ ነበር። በወቅቱ ከዩናይትድ ኢምሬትስ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ዓለም ባንክ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ መገኘት ተችሎ ነበር። በተጨማሪ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ሥልጣን ከተቆናጠጡ በኋላ በዓመት ውስጥ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከሐዋላ ተሰብስቧል። እነዚህ መሻሻሎች የአገሪቷ የውጭ ምንዛሬ መጠባበቂያ ክምችት የ2 ነጥብ 6 ወራት የገቢ ሸቀጦችንና ወጪ ለመሸፈን እንዲችል አድርጎታል።

ብሔራዊ ባንክ ከኹለት ወራት በፊት በስምንት ወራት ውስጥ ከ13 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ቢያገኝም መጠኑ ከመድኀኒትና ነዳጅ ከመሸፈን እንደማያለፍ የባንኩ ገዢ ይናገር ደሴ ገልፀው ነበር። ይህንን ንግግራቸውን ከሳምንት በኋላ ቢያስተባብሉም የውጭ ምንዛሬ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። በርግጥ፤ በብሔራዊ ባንክ ይሁንታ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የግል ባንኮች ከጥቂት ሳምንታት በፊት 100 ሚሊዮን ዶላር ለውጭ ምንዛሬ ጠያቂዎች ቢያከፋፍሉም ችግሩ እልባት የሚያገኝ አይመስልም።

ይባስ ብሎ፤ ወደ ውጪ ለሚሔዱ ሰዎች ለአንዳንድ ወጪዎች መሸፈኛ ይሸጥ የነበረው የውጭ ምንዛሬ (እስከ 200 ዶላር) ማግኘት አዳጋች እየሆነ መጥቷል። ታዲያ እጥረቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍታት ከባድ ነው የሚሉት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ሸቀጦችን መቀነስ ላይ መሠራት እንዳለበት ይመክራሉ። ዓለማየሁ በተለይም በአገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ምርቶች በመለየት ለገቢ ንግድ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ያስፈልጋል ይላሉ። በዚህ ሐሳብ ቴውድሮስም ይስማማሉ። ቴዎድሮስ “መንግሥት ወጪ ንግድ ከማበረታታት ባሻገር ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ምርት መቀነስ ላይ ትኩረቱን ሊያደርግ ይገባል” ይላሉ።

በተጨማሪም በአገሪቷ የተፈጠረው ፍላጎት ሊያሳካ የሚችል አቅርቦት መፍጠር ላይ መንግሥት ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ባለሙያዎች ያነሳሉ። በተለይም በየዓመቱ የሚፈጠረውን ፍላጉት ለማሳካት የሚችል ፖሊሲ ሊቀረፅ እንደሚገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በሌላ በኩል የዓለም ባንክ በግንቦት 2011 ባወጣው ጥናቱ ነፃ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ (floating exchange rate regime) የገበያ ስርዓት እንዲተገበር እና ብር ከሌሎች የውጭ ምንዛሬ አንፃር ያለውን የዋጋ ልዩነትን መቀነስ ላይ መንግሥት ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባ ገልፆ ነበር። የምጣኔ ሀብት መምህሩና ባለሙያው ዓለማየሁ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። “ይህን ምክር መንግሥት ከተቀበለ አገሪቷ በቀላሉ መውጣት የማትችልበት ቀውስ ትገባለች” ይላሉ። ይህም በበርካታ አገሮች የተከሰተ መሆኑ ይታወቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here