ጉዞ ዘ ማለዳ ወደ ምሥራቅ ኢትዮጵያ

0
1250

አዲስ ማለዳ አሁንም ጉዞዋን ቀጥላለች! የጉዞዋን መልኅቅ የተጣለችው ምሥራቃዊቷ የታሪክ ማኅደር እና የአንድ ሺሕ ዓመት እመቤት ወደ ሆነችው ሐረር ከተማ ላይ ነው። 74 አሚሮች የነገሡባት፣ በምሥራቅ አፍሪካ ገናና የእስላማዊ መንግሥት መናገሻ፣ 519 ኪሎ ሜትር ከአዲስ አበባ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ የምትርቀው ጥንታዊቷ እና ዛሬም በውበት የጎብኝዎቿን ልብ የምታጠፋው የፀሐይ መውጫዋ ፈርጥ ሐረር!

ግንቦት 29/2011 ከአዲስ አበባ በተለምዶ ሜክሲኮ ከተባለው ሥፍራ የተጀመረው ጉዞ ወደ ሐረር በሦስት መኪናዎች ተከፋፍሎ በርካታ ጋዜጠኞችን ያሳተፈ ነበር ። በዕለቱ ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ አዲስ አበባ በወጉ ሳትነቃ ነበር ጉዟችንን የጀመርነው። ሰዓት አክብሮ በቀጠሮ መገናኘት ችግር ሁላችንም ላይ ይስተዋላልና፣ አዲስ ማለዳ የነበረችበት መኪና ቀድሞ ተነስቶ ጉዞ ቢጀምርም ቀሪ ኹለቱ መኪኖች ተጓዦቻቸው በጊዜ ባለመገኘታቸው ቆመን እንድንጠብቃቸው የሥልክ ጥሪ ለአሽከርካሪያችን በመደረጉ ልንቆም ተገደድን።

ከአዲስ አበባ – ወለንጪቲ
የሆነው ሆኖ ጉዞው ተጀምሯል አዲስ- አዳማ የፍጥነት መንገድ ከወትሮው በተለየ የተሸርካሪ ፍሰት ጨምሮበታል በአራት ረድፍ የተከፋፈለው መንገድ ከዐሥር እና ዐሥራ አምስት ሜትር ባልዘለለ ርቀት ውስጥ ደርዘን መኪኖችን ማየት ግርታን የሚፈጥር ነው። የማለዳዋ ፀሐይ ጉዟችን ወደ ምሥራቅ መሆኑን ያወቀች ይመስል ገና ከጥዋቱ ነው አቀባበሏን ያሳመረችው። በጉዞ አስተባባሪያችን በተነገረን መሰረት አዳራችን ሐረር ከተማ መሆኑ ተረጋግጧል፤ ማረፊያችንም እዛው ቀድሞ እንደተያዘልን ተበስሮናል።

አዲስ አበባን በእንቅልፍ ልቧ ተሰናብተናት የወጣነው ተጓዦች ፍጥነት መንገዱን ተከትለን አዳማን በስተምዕራብ እያየን የፍጥነት መንገዱን መጨረሻ ደርሰን ወደ ምሥራቅ በመታጠፍ መንደርደር ጀምረናል። እውነት ለመናገር እኛ የተሳፈርንበት መኪና አሽከርካሪ ያሽከረክራል ከሚባል እንዲያው ይራመዳል ቢባል ይቀላል። ዝግ ማለቱን እና ጥንቃቄ ማድረጉን ብወድለትም ገና የሚጠብቀንን ረጅም ጉዞ ሳስበው ግን ልቤ መዛል ጀምሯል። ኹላችንም ማልደን ነበርና ለጉዞ የተቀጠርነው እህል በአፋችን አልዞረም በዚህም ምክንያት የረሃብ ስሜት እየተሰማን በመሆኑ ረፈድፈድ ሲል ከአዳማ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ወለንጪቲ ከተማ ለቁርስ ቆምን። ወለንጪቲ ድንበር ተሻጋሪ የከባድ መኪና ሹፌሮች የፈጠሯት ትንሽ ከተማ ናት። ይሁን እንጂ ረሃባችንን ለማስታገስ በገባንበት ምግብ ቤት አዲስ አበባ እግር እስኪነቃ ቢኬድ የማይገኝ የፍየል ጥብስ በሚገርም ዋጋ አስተናግዳናለች።

እነሆ አሁን መንገደኞች ከረሃብ በአንድ ጊዜ ጥጋብን እያዳመጥን ጉዟችንን ቀጥለናል።

ከወለንጪቲ – አሰበ ተፈሪ/ጭሮ
የሚቀጥለው መቆሚያችን የት እንደሆነ ባናውቅም በከባባድ መኪኖች የተሞላውንና ጠባቡን ከአዳማ ጅቡቲ የሚዘልቀውን መንገድ ተያይዘነዋል። የመንገዱን ነገር ለመግለፅ ረጅም ዝርዝር ስለሚያስፈልገው ለጊዜው እንተወውና ጠባብ መሆኑንና በተለምዶ “አይሱዙ” የሚባሉ ቀላል የጭነት መኪኖች መንገዱን ያላማከለ እና አደገኛ አነዳዳቸውን ነብስና ሥጋችን እየተላቀቀ ነበር ስንታዘብ የነበረው። ከአዳማ የጀመረው የሙቀት መጠን ጉዟችን ወደ ፊት በረዘመ ቁጥር ይበልጡኑ እየጋለ መሔድ ጀምሯል። የመኪናውን መስኮት ከፍተን የምናገኘው ሞቃት አየር መስኮት ለመክፈታችን እንድንጠራጠር የሚያደርግ ኀይል ነበረው። በነገራችን ላይ የሙቀቱ መጠን የጨመረ ቢሆንም በመኪና መንገዱ ግራና ቀኝ ግን ልብን የሚሰልብ ልምላሜን ሲመለከቱ ከሚሰማዎት ሙቀት ጋር ለማስታረቅ ከተፈጥሮ እና ከአዕምሮዎት ጋር ከፍተኛ ግብግብ እንደሚገጥሙ አይጠራጠሩ። ሰሞኑን በአካባቢው መዝነብ በመጀመሩ ሜዳዎች፣ ጋራዎች፣ ሸንተረሮ ከፍተኛ ልምላሜ ተላብሰዋል።

ከወለንጪቲ እረፍት በኋላም ምንም ዓይነት ፍጥነት መሻሻል ያልታየበት ሹፌራችን ከአዲስ አበባ ኹለት መቶ ኪሎ ሜትር ወደ ምትርቀው የፍራፍሬ ዓለም መተሐራ አድርሶናል። በነገራችን ላይ ወደ መተሐራ ጉዟችን ላይ ግርምትን ያጫረብን ትዕይንት ቢኖር፤ ከቀዘቀዘ እሳተ ጎመራ አረፋ የተፈጠሩ እጅግ የጠቆሩ እና ከመጠናቸው እጅግ በተለየ ሁኔታ ክብደታቸው ቀላል የሆኑ ድንጋዮችን ተመልክተናል። ሌላው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስን የሆነውን የኮንክሪት አስፓልት የመተሐራ የውሃ ምንጭ በሆነው በሰቃ ሐይቅ ዳርቻ ላይ ረግጠነው አለፍን።

በቀደመው ጊዜ መተሐራን አቋርጦ የሚያልፈው አስፓልት ይህ እንዳልሆነና የድሮው መንገድ በሰቃ ሐይቅ ውስጥ ሰጥሞ ደብዛው እንደጠፋ አካባቢውን የሚያውቁ የጉዞ አጋሮቻችን ሹክ ብለውናል። መተሐራ ለእኛ ጭንቅ የሆነብንን ሙቀት ገና ለመቀበል እያኮበኮበች እንደሆነች ከነዋሪዎቿ እንቅስቃሴ ታዝበናል። አሁን መተሐራን ለቀን ወደ ቀጣዩ መዳረሻችን አዋሽ 7 ኪሎ ጉዞ ጀምረናል። በዚህ አካባቢ ሽፍታ ይይዘርፈኛል ቀማኛ ይነጥቀኛል ብለው ሳይሳቀቁ የአካባቢው ነዋሪዎች ከመንገድ ድካም ሲሰማቸው ሞቃቱ አሸዋ ላይ ድንጋይ ተንተርሰው የግራር ዛፍ ሥር ሸለብ እስኪያደርጋቸው አረፍ ይላሉ። ዝርፊያ እዚህ አካባቢ እጅግ የተወገዘ እና ፀያፍ ነው።

እነሆ አሁን አዋሽ ብሔራዊ ፓርክን አቋርጠን ከቀድሞው ፍጥነታችን ቀንሰን እያዘገምን ነው። ለምን መሰላችሁ ገና ፓርኩን ስንጀምር የዱር እንስሳት መንገዱን ሊያቋርጡ ስለሚችሉ በዝግታ ያሽከርክሩ ዓይነት ይዘት ያለው ማስታወቂያ ማንበባችንን ተከትሎ ነው። የሙቀቱን ነገር ለማሰብ የሚከብድ ልዩ ትንግርት ነው። አዋሽ ፓርክን ወጥተን አሁን በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር ጉምሩክ ኮሚሽን የአዋሽ 7 ፍተሻ ጣቢያ የሚገኝበት እና በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አዋሽ 7 ኪሎ ከተማ ደርሰን ለመኪኖች ነዳጅ ለመቅዳት ቆምን።

ለሰዓታት ተቀምጠን በመጓዛችን ሰውነታችንን ለማፍታታት ከመኪናው ወረድን። የተቀበለን ሙቀትና እጅግ የሚያቃጥል ፀሐይ የከሰል ምድጃ አጠገብ የተቀመጥን ያህል የሚጋረፍ ነበር። ጥላ ፍለጋ ተመልሰን መኪናችን ውስጥ ብነገባም መኪናውም የአካባቢውን ሙቀት ሲቀበል ቆይቶ ኖሮ ከሰውነታችን ላብ እንደ ውሃ ይወርድ ጀመር። ከዐሥር ደቂቃ በኋላ ጉዟችን ቀጠለ። በነገራችን ላይ አዋሽ 7 ፍተሻ ጣቢያ ላይ መሔጃችን አስፓልት አዲስ ሊባል በሚችል ደረጃ በደህና ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን መመለሻችን ግን እጅግ ተጎሳቁሏል። እዚህ ላይ ግን መታሰብ ያለበት ጉዳይ መንገዱ ከጭነት ብዛት መበላሸቱ ወይም የመንገዱ ጤንነት ሳይሆን የትኛውም የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ሳንጠይቅ አንድ ነገር እንረዳለን። ይህም በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከወጪ ንግዱ ይልቅ የገቢ ንግዱ በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ነው። አሁን የምጣኔ ሐብቱን ትንታኔ ለጊዜው ይቆየን።

አዋሽን ተመልሰን እስክናገኝሽ ከሙቀትሽ ጋር ቸር ይግጠመን ብለን ጉዞ ወደ ፊት። አዋሽ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ማሰልጠኛ እንዳለው አይተን ለሰልጣኞቹ ትልቅ ክብር ሰጥተናቸዋል። እውነትም እንደወርቅ በእሳት የተፈተኑ የሕዝብ ልጆች።
ቀጠልን ደግሞ ጥቃቅን ገጠር መንደሮችን ግራና ቀኝ እያለፍን መኤሶን አልፈን ጉዞ ወደ አሰበ ተፈሪ ወይም ጭሮ አድርገናል።

ከአዲስ አዳማ የፍጥነት መንገድ ጀምሮ የታዘብነው እና የውብ ተፈጥሮው እና መልክዓ ምድሩ ሐዘን የሆኑት ደግሞ በመንገዱ ግራና ቀኝ በአሳዛኝ ሁኔታ ተገልብጠው የሚታዩት ተሸከርካሪዎች ናቸው። ከአዋሽ መኤሶን አልፈን ወደ አሰበ ተፈሪ በምናደርገው ጉዞ ደግሞ የአደጋውና የተገለበጡ መኪኖች ቁጥር እየበዛ መጥቷል። አሰበ ተፈሪ ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ ደርሰን ለምሳ ቆመናል። ከመኤሶ ጀምሮ አንድ ቀልባችንን የያዘው ነገር ቢኖር ሴቶች በአካባቢው የሚዘወተረውን አለባበል ‘ድሪያ’ ወይም ‘ሽቲ’ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ዓርማ ያለበት መሆኑ ነው። ለምሳ በቆምንበት አሰበ ተፈሪ ሰላማዊ እና በብዙ የጫት ተረፈ ምርት የተከበቡ የአዕምሮ ሕመምተኞችንም እግረ መንገዳችን ታዝበናል። እንግዲህ ከዚህ በኋላ ያለው መንገድ ፈጣሪ አብሮን ይሁን እንጂ እጅግ ከባድ እና ጠመዝማዛ ነው።

ከአሰበ ተፈሪ – ጨለንቆ – ድሬዳዋ
ከአሰበ ተፈሪ እንደወጣን ጋራውን ሹሩባ የተሰራች ልጅ አገረድ ያስመሰለውን በመስመር የተተከለውን የጫት እርሻ በቅርብ ርቀት እየተመለከትን ነው። በዚህ አካባቢ በቆሎ እና ጫት መሳ ለመሳ ተተክለው መመልከት ግርምት የሚያጭር ነው። በአካባቢው ልምላሜ እየተመሰጥን ጠመዝማዛው መንገድ አንድ ጊዜ ወደ ላይ ሽቅብ አውጥቶ ሰማይን ሲያስቧጥጠን በል ሲለው ደግሞ ቁልቁል አምዘግዝጎ እንጦሮንጦስ እየከተተን ሲያስጉዘን እኛም በግርምት ላይ ግርምትን እየጨመርን በመሐል ደግሞ አሰቃቂ አደጋዎችን ስናይ እየተሸማቀቀቅን እየተጓዝን ነው። በዚህ መንገድ ላይ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ እንዲሁም በአገር ሀብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለሚያይ ልቡ በቁጭት ይደማል። በተለይ ደግሞ ከአሰበ ተፈሪ በኋላ ያለው መንገድ አሽከርካሪዎችም በአካባቢው በስፋት የሚገኘውን ጫት እየቃሙ ስለሚያሽከረክሩ አደጋው ከመልከዓ ምድሩ ጋር ተዳምሮ ቁጥሩ ከፍ ይላል።

አሁንም ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ከመንገድ ግራና ቀኝ እንደ ክቡር ዘበኛ በግርማ ሞገስ ቀጥ ብለው የሚታየት ዛፎች አካባቢው ደጋ መሆኑን እያሳበቁ ነው። የሒርናን ዳገት አዝግመን ወጥተናል ታዲያ በዚህ መሐል አንድ ድምፅ ከመኪናው ጎማ ተሰማ መኪናው ውስጥ ያለው በሙሉ ደንግጦ ምንነቱን ለማየት መኪናው በአግባቡ እስኪቆም እንኳን መታገስ አልቻለም። የመኪናችን ጎማ ፈንድቷል ስለሆነም ቆመን መቀየር ይገባናል። ከሌሎች መኪኖች ሹፌሮች ጋር በመተጋገዝ በደቂቃዎች ጎማው ተቀይሮ ጎዞው ቀጠለ። ለወትሮውም በኤሊ ፍጥነት የሚሔደው መኪናችን የመንገዱን ዳገታማነት ምክንያት አድርጎ ጭራሽኑ መቆም ቀርቶታል። ይሆነው ሆኖ አሁን ወደ ታሪካዊቷ ጨለንቆ ከተማ እየተዳረስን ነው በመንገድ ታዲያ የዛሬ ኹለት ዓመትን አሳዛኝ ትውስታን ለመንገር የቆሙ ኹለት በሕዝባዊ አመፅ ተቃጥለው አፅማቸው የቀረ የሰላም ባስ ንብረት የሆኑ አውቶብሶችን አይተናል።

በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ዘመን ሐረርን ለማስገበር በተደረገ ውጊያ ጨለንቆ ላይ ከባድ ፍልሚያ መደረጉንና እልቂት መድረሱን ለመዘከር የቆመ መታሰቢያ በዚች ትንሽ ከተማ በሰፊ ቦታ ላይ ተንጣሏል። አሁን ፀሐይም ወደ ማደሪያዋ ገብታ ተሸሽጋለች፣ ጊዜውም ለዓይን ያዝ ማድረግ ጀምሯል ጉዟችን ግን እንደቀጠለ ነው። ከአዲስ አበባ ስንነሳ በጉዞ አስተባባሪያችን የተነገረን በሐረር ከተማ የተያዘልን ማረፊያ እውነት እንዳለሆነ እና ሐረር ከመሸ ብንገባ አልጋ እንደማናገኝ ስለታመነበት የሐረሩ ጉዞ ለዛሬ ድሬዳዋ ላይ እንዲገታ ተወሰነ። እናም ደንገጎ ላይ ወደ ግራ ታጥፈን ቁልቁል የበርሃ ቴምር ወደ ሆነችው ድሬዳዋ ሸመጠጥን። አሁን ከምሽቱ 2 ሰዓት ሆኗል ድሬዳዋ ለመግባት የደንገጎ ተራራን ቁልቁል እየተጠማዘዝን መውረድ ብቻ ነው ሚጠበቅብን። ቁልቁል በወረድን ቁጥር ታዲያ አፉን ወደ ከፈተ ፍም እሳት የምንገባ ያህል ሙቀቱ በማታ እንኳን ኀያል ነው። ድሬዳዋ ደርሰን አዳራችንን ካደረግን በኋላ ለቀጣዩ ቀን ጉዞ ማልደን በመነሳት መኪናችንን ተሳፈርን።

ከድሬ ዳዋ – ሐረር
ቁልቁል እንደወረድን እንቅልፍ ጋር ጥል ያለበት የሚመስለውን የድሬ ዳዋን ሕዝብ ተሰናብተን ሽቅብ ወጥተን ጉዞ ወደ ሐረር። በጫት ምርቷ ጎረቤት አገር ብቻ ሳይሆን ባሕር ተሸግሮ ሥሟ የሚታወቀው አወዳይ ከተማ ሰዓታችንን በተደጋጋሚ ለማየት የሚያስገድድ የሰዎች እንቅስቃሴ እና ሽርጉድን አስቀድማ ተቀበለችን። በእርግጥ ሰዓቱ ለ12 ሰዓት 20 ደቂቃዎች ይቀሩት ነበር አወዳይ ግን በሌላው አካባቢ ረፋድ ላይ የማይታየውን ጥድፊያ እያከናወነችው ነው።

ሳይሰናበተን አሻራውን ብቻ ጥሎ ያሸለበውን ሐሮማያ ሐይቅን በምናብ ሰላምታ እያቀረብን እና ሐረር ከተማን እየናፈቅን ነጎድን። አሁን ከኹለት ቀናት ጉዞ በኋላ ታሪካዊቷ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የባሕልና የሳይንስ ድርጅት በመቻቻልና በአብሮነት የተሸለመችውን ሐረር ከተማ ረገጥን።

“ለአገሩ እንግዳ ነኝ ለሰውም ባይተዋር” አይነት ጨዋታ ሐረሮች ጋር ቦታ የለውም። “አቦ ሐዘን ውጣ ወለ በል ጭንቀት” ነው ጭዋታው። የፌደራል ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ 11ኛ ዓመታዊ ክብረ በዓሉን ለማክበር ነበርና ጉዞውን ያዘጋጀው ከተማዋ በኤጀንሲው ዓርማ አሸብርቃ ነው የተቀበለችን። የፌደራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ በክብረ በዓሉ ላይ በመላው አገሪቱ አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡ የህብረት ስራ ማኅበራትን በደማቅ ስነ ስረዓት የሸለመበት፣ ኤጀንሲውንና በኤጀንሲው አማካኝነት የሚሰሩ ስራዎችን ደግሞ በራሳቸው ተነሳሽነት የዜና ሽፋን ሲሰሩ ለነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የምስክር ወረቀት የሰጠበት ታሪካዊ መርሃ-ግብር ተከናውኖ ቆይታችን በፍቅርና በአስገራሚ ኹነቶች የተሞላ ነበር።

ስለ ታሪካዊነቷ ብዙ ተብሏል እስኪ ስለ ነዋሪው ደግሞ ትንሽ እንጨዋወት። በሐረር ከተማ የኔ ቢጤ እና የአዕምሮ ሕመምተኛ እስከ ቀን እኩሌታ ነው ሚለምኑትና ሚታመሙት ልክ ፀሐይ በአናት ላይ ስትሆን ኹሉም ጫቱን ይዞ ጥጉን ይይዛል። ጭቅጭቅና ቂም የማያውቁት ሐረሮች ከዘመናት በፊት ከአዲስ አበባ የተሸኙት የፔጆ ምርት መኪኖች ዋነኛ የትራንስፖርት መገልገያቸው ናቸው። እስኪ በአስቂኝ ገጠመኝ እንሰነባበት።

ሐረር ከተማ ገብተን አልጋ ፍለጋ መዞር ግድ ብሎን ነበር። ታዲያ በዚህ ወቅት አንድ ቦታ ደርሰን አልጋ እንዳላቸው ፈገግታ አስቀድመን ጠየቅን ምላሹ ግን አስደንጋጭ ነበር “የሙስሊም ወይስ የክርስቲያን?” የሚል ነበር ምንመልሰው ነገር አጥተን ደቂቃዎችን እርስ በእርስ በመተያየት አሳልፈን እየሳቅን ተያይዘን ወጣን።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here