የጊዜ ገደቡ ክርክር ያስነሳው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለአንድ ዓመት ተራዘመ

የሱማሌ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሐመድን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለአንድ ዓመት የተራዘመው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በአንድ ዓመት ብቻ መራዘሙን እንደማይስማሙበት ገለፁ።

በኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መሰረት በየዐሥር ዓመቱ እንዲካሔድ የተደነገገው አገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ወደ 2012 እንዲተላለፍ የቀረበው ሐሳብ አገሪቱ ያለችበትን የፖለቲካ ትኩሳት ይበልጥ የሚያወሳስበው ስለሚሆን ላልተወሰነ ጊዜ ይራዘም የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል።

አያይዘውም “ራሳችንን ለመሸወድ ካልሆነ አሁን ላይ መረጋጋቶች እየታዩ ሳይሆን ከፍተኛ ሽግግር እየተደረገ ነው ያለው” የሚሉት ርዕሰ መስተዳደሩ በሚቀጥለው ዓመት ይደረጋል የተባለው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ነገሮች በአጭር ጊዜ መልክ ይዘው ይከናወናል የሚል ሐሳብ እንደሌላቸው ጠቁመዋል። የሕገ መንግሥቱ ጉዳይን በሚመለከትም ሙስጠፌ “ሕገ መንግሥት ከአገር ሕልውና አይበልጥም” በማለት ቆጠራው ላልተወሰነ ጊዜ በሚል መራዘም ይኖርበታል ሲሉ ተከራክረዋል።

የሙስጠፌን ሐሳብ የሚደግፉትና መራዘሙ በቀነ ገደብ መቀመጡን የሚቃወሙት የምክር ቤት አባል አወል መሐመድ በበኩላቸው ደግሞ “ከስድስት እስከ ስምንት መቶ አባውራ በአንድ አዳራሽ ውስጥ እየኖረ ባለበት ሁኔታ የማን ቤት ነው የምንቆጥረው›› ሲሉ ጠይቀዋል። በሚቀጥለው ዓመት ነገሮች ተረጋግተው ኹለት ታላላቅ አገራዊ ኩነቶችን ማካሔድ ለማሰብ የሚከብድ ትልቅ ኀላፊነት እንደሆነና ላልተወሰነ ጊዜ ቢራዘም የበለጠ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም “የመንግስት አስፈፃሚነት በተዳከመበት ጊዜ ኮሚሽኑ አሁንም የማራዘሚያ ጊዜ ይጠይቃል የሚል ሐሳብ አለን” የሚሉት ደግሞ ሩፋኤል መላኩ ናቸው።

ከኹለቱም ምክር ቤት አባላት የተነሱትን ተቃውሞዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። የሰላም ሚኒስቴር እስከ ሰኔ 30/2011 ድረስ በመላ አገሪቱ ያሉትን ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንደሚመልሳቸው ቃል የገባ በመሆኑ ለሚቀጥለው ዓመት የሕዝብና ቤት ቆጠራውን ማካሔድ ተመራጭ እና የሚፈለገውን ውጤት ለማግኘትም እንደሚረዳ ተናግረዋል። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታየ ምናለም ቆጠራው ወደ ሚቀጥለው ዓመት መራዘሙን ደግፈው “ፉክክር በሚመስልበት አመለካከታችን ትክክለኛውን ቁጥር ማግኘት የማይቻል ነው” ሲሉ ያስቀምጣሉ።

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 (3) ላይ የተደነገገው እና በየዐሥር ዓመቱ የሕዝብና ቤት ቆጠራ እንዲካሔድ የተደነገገ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም በ1997 ከአገራዊ ምርጫ ጋር ጊዜው በመገጣጠሙ መራዘሙ ይታወቃል። ከፍተኛ የሰው ኀይልና በጀት በመጠየቁ ወደ 1999 እንዲሸጋገር ተደርጎ በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 103 (5) ላይ ማሻሻያ ተደርጎበት ከአቅም በላይ በሆኑ በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሊራዘም ይችላል በሚል ተደንግጓል።

በመጨረሻም አራተኛውን የሕዝብና ቤት ቆጠራ ለኹለተኛ ጊዜ ለማራዘም በተሻሻለው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 103 መሰረት የቀረበው ውሳኔ ሐሳብ በ30 ተቃውሞ እና በ3 ድምጸ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

ሰኔ 3/2011 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤት አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሦስተኛ የጋራ ስብሰባ ባካሔዱበት ወቅት ጥልቅ ክርክርን ስተናገደው ቆጠራ ለአንድ ዓመት ተራዝሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here