የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሹመት ቅሬታን አስተናገደ

0
706

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባላት ሆነው እንዲሾሙ የተመረጡት አራት አባላት ሹመት ታዳጊ ክልሎችን ያገለለ ነው በሚል ቅሬታ አስተናገደ። በተለይም በቀደመው ጊዜ የታዳጊ ክልል ተወካዮች ይካተቱ እንደነበር እና አሁን ግን ምንም ተወካይ ባለመኖሩ ተቃውሟቸውን የምክር ቤቱ አባላት አሰምተዋል።

በተለይም አሕመድ መሐመድ የተባሉ የምክር ቤቱ አባል ለውጥ መጥቷል በተባለበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ዓይነት አግላይ ነገር መደረጉ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። አያይዘውም ከብሔር ተዋፅኦ ማነስ በተጨማሪም የቦርዱን ሚዛናዊና ፍትሐዊነት እንደሚጠራጠሩም አልሸሸጉም።

ከሕዝብ እንደራሴዎች ለቀረበው የተቃውሞ ሐሳብ በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ መስፍን ቸርነት ምላሽ ሲሰጡ “መንግሥት ያለ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ እና ይሁንታ እነዚህን አባላት ለሹመት አላጨም” በማለት በፍትሐዊነትና ሚዛናዊነት በኩል ለተነሳው ጥያቄ ግን የሚመለከተው አካል አምኖባቸው እና ሚዛናዊነታቸው ተረጋግጦ ለሹመት የቀረቡ ናቸው ሲሉ ምላሻቸውን አስቀምጠዋል።

የምርጫ ቦርዱ አባላት ሆነው እንዲሾሙ በእጩነት የቀረቡት አባላት ብዙወርቅ ከተተ፣ ውብሸት አየለ፣ ጌታሁን ካሣ፣ አበራ ደረፋ ሲሆኑ ከእጩዎቹ መካከል ውብሸት አየለ በምክትል ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ ቆዩ መሆናቸው ታውቆ ለብቻቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ ፈፅመዋል።

ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባልነት በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ከ200 በላይ ግለሰቦች ተጠቁመው እንደነበር የመንግሥት ረዳት ተጠሪው ለምክር ቤት ያስታወቁ ሲሆን በሦስት የማጣሪያ ምዕራፎች እንዲያልፉ እንደተደረገም ጨምረው ገልፀዋል። ቀረቡትን ጥቆማዎችም ሰባት አባላት ያሉትና ቀደም ሲል ወደ ሥራ የገባ መልማይ ኮሚቴ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መልማይ ኮሚቴ ግለሰቦችን መመልመል ሥራ ሰርቷል። በሦስት የማጣሪያ ምዕራፎች አልፈው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ሹመታቸው እንዲፀድቅ የታሰቡት እጩ አባላት በአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ውስጥ በኀላፊነት እና በአማካሪነት ሥሩ እንደሆነ የግል ማኅደራቸው ያትታል።

ብዙወርቅ ከተተ በቀድሞው በአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ውስጥ ባልደረባ የነበሩ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውስጥ ያገለገሉ እና በአክሽን ኤድ ዓለም ዐቀፍ ድርጅት በለንደን፣ በሩዋንዳና በኢትዮጵያ ቢሮዎች ውስጥ በኀላፊነት ያገለገሉ ናቸው።
ውብሸት አየለ በከፍተኛ ፍርድ ቤት የረጅም ዓመት የዳኝነት ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፤ በአገራችን የመጀመሪያ ሆነውን የግልግልና ዳኝነት ማዕከል መሥራችና ዋና ፀሐፊ ሆነው የሰሩ እንዲሁም የእርማት ጊዜያቸውን የጨረሱ ወጣት ጥፋተኞችን ማገገሚያ ማዕከልን በማቋቋም አስተዳዳሪ በመሆን አገልግለዋል።

ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ዐቃቤ ሕግነት፣ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ በመምህርነት እንዲሁም በተለያዩ የተባበሩት መንግሥታት ቢሮዎች በአማካሪነት አገልግለዋል። ጌታሁን በእንግሊዝ የዕርዳታ ድርጅት እና በሌሎች መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ኢምባሲዎች በአማካሪነት ሰርተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ቤት ከኻያ ዓመታት በላይ የማስተማር ልምድ ያላቸው ደግሞ አበራ ደገፉ ነገዎ ናቸው። አበራ ደገፉ በ2009 ከዩኒቨርስቲው የሚሰጠውን “የላቀ የማስተማር አበርክቶ” ሽልማት ተሸላሚ ምሁር ሲሆኑ፤ በዘመን ባንክ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች አስተዳደር ጉባዔ እና በኦሮሚያ የሕግ ጆርናል ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል።

በመጨረሻም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አባልነት የቀረቡት አራት እጩዎች በ17 ተቃውሞ፣ በ1 ድምፀ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here