“ኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል ማዛወር በጣም ትልቅ ስህተት ነው።” ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ

0
1293

ዓለማየሁ ገዳ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ናቸው። የሦስተኛ ዲግሪ (የዶክትሬት) ተማሪችን ማክሮኢኮኖሚክስ የትምህርት ዓይነቶች ከማስተማራቸውም በተጨማሪ በሚሠሩት የምርምር ሥራቸው ያማክሯቸዋል። በኬኒያ – ናይሮቢ በሴንትራል ባንክ ኤንድ ትሬዠረሪ፣ በካምፓላ – ኡጋንዳ ኢፒአርሲ/ማካራሬ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በምሥራቃዊ ደቡብ አፍሪካ አገራት ባሉ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ከማስተማሩ ጎን ለጎን ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ እንዲሁም በውጪ አገራት ያደረጉ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን በማማከርም ይታወቃሉ።

ዓለማየሁ የምርምር ሥራዎቻቸው ታዋቂ በሆኑ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፤ ለማጣቀሻነት የሚረዱ መጻሕፍቶቻቸው በዓለም ዐቀፍ ገበያ ውስጥ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት እግር በእግር በመከታተል ምርምር ያካሒዳሉ፣ በሰፊው ይጽፋሉ። በአዲስ ማለዳ ጋዜጣ እህት በሆነችው ‘ኢትዮጵያን ቢዝነስ ሪቪው’ መጽሔት ላይ በርከት ያሉ መሰረታዊና ወቅታዊ በሆኑ አገራዊ የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ዙሪያ ጽፈዋል፤ በአዲስ ማለዳ ጋዜጣም ላይ እንዲሁ አበርክቶ አላቸው።
ብዙዎች ሥመጥር የምጣኔ ሀብት ባለሙያ መሆናቸውን የሚመሰክሩላቸው ዓለማየሁ በሥራ ከተጣበበ ጊዜያቸው የተወሰነውን ደቂቃዎች በመውሰድ የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ በወቅታዊና መሰረታዊ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ማለዳ፡ የመንግሥት ተቋማትን ወደ ግል የማዘዋወሩ ሁኔታ ወደ ጫፍ እየደረሰ ይመስላል። በአጠቃላይ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወሩን (‘ፕራይቬታይዜሽን’) እንቅስቃሴ እንዴት ያይቷል?

ፕራይቬታይዝሽን የሚደረገው ለኹለት ነገር ነው። አንደኛው ጥሩና ቀልጣፋ አሰራር እንዲያመጣ ነው። ኹለተኛው ለሸማቹ በትንሽ ዋጋ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው። ይህን ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ገበያ ውስጥ ውድድር መኖርና ውድድሩን የሚመራ ተቋም ያስፈልጋሉ። ይህ ከተደረገ በኋላ ደግሞ ለተወዳዳሪዎች ዕድሉን መስጠት ያስፈልጋል። ይህ ጥሩ ውጤት ካላመጣ ወደ ግል ንብረትነት ሲዘዋወር ጥሩ ነው።

እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ አንድ ድርጅት ቢሸጥ ከመንግሥት ጠቅላይነት (ሞኖፖል) ወደ ግል ነው የሚሔደው። የግል ድርጅት ደግሞ የሚያገኘውን ትርፍ የት እንደሚያደርግው መጠየቅ አይቻልም፤ ምክንያቱም መብቱ ነው። ለምሳሌ፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ግል ማዛወር በጣም ትልቅ ስህተት ነው። ምክንያቱም በምንም መስፈርት አየር መንገድ ተወዳዳሪ ሆኖ እያለ ይሸጥ ሊባል አይችልም።

እኔ ባደረኩት ጥናት ዋና ዋና ከሚባሉ ሰባት የአሜሪካ አየር መንገዶች የትርፋቸው ህዳግ 4.5 በመቶ ነው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትርፍ ግን ከ9 እስከ 13 በመቶ ነው ይሆናል። ከተጓዦች ለአገሪቷ የሚያስገኘው ዶላር ቀላል አይደለም። የድርጅቱ የቀድሞና የወቅቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚና አቶ ግርማ ዋቄ እና አቶ ተወልደ [ገብረማሪያም] በብዙ መግለጫዎች ላይ እንደነገሩን መሸጥ ምንም የቴክኖሎጂ ለውጥ ለድርጅቱ አያመጣም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አየር መንገዱ በቴክኖሎጂም ሆነ በሰው ኀይሉ ከሌሎች የተሻለና ዓለም ያለበት ደረጃ ላይ ነው ያለው። እንደዚህ ዓይነት ድርጅት እንዴት ይሸጣል።

ከኢኮኖሚ አዋጭነት አንፃርም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመሸጥ ምንም ዓይነት ምክንያት የለም። በጅምላ ከሌሎቹ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጋር ለመሸጥ ከተሞከረም እንዲቀር መጣር አለብን። የጅምላ ውሳኔ አይበጀንም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሸጥ ባይኖርብንም ኢትዮ ቴሌኮም ግን ምናልባት በከፊል መሸጡ ላይከፋ ይችላል። ይህም ግን አሁን ላይ ከተገበረ ችግር ያመጣል። ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግሥት በዚህ ዓመት ከመንግሥት ድርጅቶች 45 ሚሊዮን ዶላር በላይ በትርፍ መልክ አግኝቷል። ሆኖም 60 በመቶ የመጣው ከቴሌኮም ነው። የቀረው 30 በመቶ ደግሞ ከንግድ ባንክ ነው። ስለዚህ ለመንግስት እነዚህን መሸጥ ማለት የራሱን አቅም መሸክ ማለት ነው ።

ከዚህ ቀደም ባጠናሁት ጥናት የቴሌኮም ትርፍ ህዳግ 60 በመቶ ነው። ስለዚህ የገዛው ሰው በሚቀጥለው ዓመት 60 በመቶ ያተርፋል ማለት ነው። በኢትዮጵያ ሕግ ማንም ዓለም ዐቀፍ ድርጅት ያተረፈውን ትርፍ ወደ ውጪ ማውጣት ይችላል። ብሔራዊ ባንክ ዶላሩን ቀይሩልኝ ቢል ከየት መጥቶ ሊሰጥ ነው።

አዎ! ቴሌኮም ደካማና ከጎረቤቶች አገራት አንፃር ብዙ ይቀረናል። ስለዚህ አሁን ማድረግ ያለብን አሁን ያለውን አስተዳደር አጠናክሮ ዓለም ዐቀፍ ልምድ ላላቸው ትንሽ ድርሻ ቢሸጥላቸው አይከፋም። ለአፍሪካ አገራት የቴሌኮም ድርጅት ቢሸጥ ያዋጣል። ሲሸጥ ግን ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው ድርሻ የመንግሥት መሆን አለበት። ከዚያ ተቋሙ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለሌሎች ተፎካካሪ ደርጅቶች ዘርፉ ክፍት መሆን ይኖርበታል። ይህም ዋጋ እንዲወርድና ዘርፉ ጠንካራ እንዲሁም ለተጠቃሚዎች ጥሩ አገልግሎት ለማቅረብ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ይህ ሳይሆን ግን ዝም ብሎ መሸጥ ኀላፊነት የጎደለው ነገር ይመስለኛል።

ሌላው ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሥልጣን ከያዙ በኋላ መንግሥት ምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለው መሪ ደርሻ ሲቀንስ ይታያል። ይህ ትክክል ነው ብለው ያምናሉ?

ትክክለኛ አይደለም፣ እድገት ለማምጣት ከተፈለገ በእኔ ግምት ልማታዊ መንግሥት መቀጠል አለበት። ችግሩ ምንድነው በእውቀት ላይ የተመሰረተ ልማታዊ መንግሥት አልነበረም ኢትዮጵያ ስትከተል የነበረው። ኹለተኛው ደግሞ ዲሞክራቲክ ልማታዊ መንግሥት አልነበረም። ይሁን እንጂ ያለ ልማታዊ መንግሥት ያደገ አገር አታይም።
አሜሪካን ብንወስድ የመጀመሪያዎቹ 100 ዓመታት ልማታዊ መንግሥት ትከተል ነበር። የምሥራቅ እስያን ታሪክ ማንም የሚያውቀው ነው። እናም ጠንካራ የሆነና ምጣኔ ሀብቱ ላይ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መንግሥት መኖር አለበት።

ምንም ጥያቄ የሌለው ነገር መንግሥትም ከግል ዘርፉ ጋር መሥራት አለበት እንጂ ብቻውን መሥራት የለበትም። ለምሳሌ ዳን ቴክኖሎጂ የተባለው ድርጅት በነበረኝ ቆይታ እንደተረዳሁት የግል ዘርፉ ከፍተኛ ጫና ሲደርስበት ነበር። እኔ መንግሥትን ብሆን ይህን ዓይነቱን ድርጅት ጠንካራ እንዲሆን አድርጌ በአፍሪካ ደረጃ ተፎካካሪ እንዲሆን አደርገው ነበር።

በሌላ በኩል የመንግሥት እና የግል የምንለው ነገር አቁመን ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን እንተካ ወይስ የውጪ ንግድን ማበርታት ላይ እናተኩር የሚለው ላይ ነው መነጋገር ያለብን። አሁን የተማርነው ምንድነው እስያውያን ኹለቱንም አጣጥመው ነው የመጡት እንጂ አንዱን አላረጉም። አንዳንዴ ረጂዎች ኹለቱን አጣጥሞ (ማለትም የግልና የመንግሥት ዘርፉን) ለመሔድ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ። ግን የመንግሥት የመሪነት ጥበብህ የሚታወቀው ይህን ተቋቅሞ ኹለቱንም አጣጥሞ መሔድ ሲችል ነው።

የመንግሥት ሚና ከፍተኛ በነበረበት ወቅት ላይ ብዙ ክፍተቶች ታይተዋል። አንደኛ ሙስና በጣም ጨምሯል። ኹለተኛ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እንዲዘገዩና መንግሥት ለከፍተኛ ኪሳራ አጋልጧል። መንግሥት ሳይቀር ንግድ ውስጥ ከዚህ ቀደም እስከመግባት ደርሶ ከስሮ ወጥቷል። ከዚህ አንፃር እንዴት የታክስ ከፋዮች ገንዘብ እየባከነ እንዴት ልማታዊ መንግሥት ይቀጥል ይላሉ?

ይሻሻል እንጂ ልማታዊ መንግሥት በነበረበት ይቀጥል ብዬ አላምንም። ለምንድነው ይህ ዓይነት ችግሮች የተፈጠሩት የሚሉትን መረዳት ያስፈልጋል። በርግጥ የሁሉም ልማታዊ መንግሥት ችግራቸው ለከፍተኛ ብክነትና ለሙስና ክፍተት መፍጠራቸው ነው።

በኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂም ሆነ ዲሞክራሲያዊ አልበረም፤ ከግል ዘርፉም ጋር በግልፅ አይነጋገርም። የእኛ የመንግሥት አወቃቀር በብሔር ላይ መሰረት ማድረጉ ሌላ ችግር ነው። በዚህም የተነሳ መንግሥት የራሱ ደጋፊዎች አድርጎ የሚቆጥራቸው የእርሱ ብሔር ተከታይ ይሆንና ለሌላ ችግር ያጋልጣል። በሌላ በኩል፤ ተጠያቂነት አለመኖሩ መንግሥት ለራሱ ፓርቲዎችና አጋሮቹ እንዲያደላ ምክንያት ይሆናል። ፓርቲዎቹ የራሳቸው ድርጅት (‘ኢንዶውመንት’) ያላቸው መሆኑ ደግሞ የበለጠ ችግሩን አባብሶታል።

ለዓመታት አልፈታ ያለው ነገር የውጪ ምንዛሬ ጉዳይ ነው። ለጥቂት ጊዜያት በተለይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ ከመጡ በኋላ በተገኙ እርዳታዎች መሻሻል ቢያሳይም አሁን መልሶ ችግሩ ተባብሷል።

የንግድ ሚዛን መዛባት ጊዜያዊ ሳይሆን ለብዙ ዓመታት የቆየ ነው። ችግሩ መዋቅራዊ የሆነ ነው። ይህ የንግድ መዛባት መዋቅራዊ ነው። ዋናው ምክንያቱ ወደ ውጪ የሚላከው በተጠበቀው እድገት ሊያድግ አለመቻሉ ነው። ከውጭ የምናስገባው ደግሞ ከአቅማችን በላይ ነው። በአማካይ ከ18 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ስናስገባ የምንልከው ግን ሦስት ቢሊዮን ዶላር አይሞላም። እስራኤል እዚህ ችግር ላይ ነበረች። ችግሩ መዋቅራዊ በመሆነ እስራኤል ከውጭ የምታስገባውን የምትቀንስበትን ስሌት ሠራች። ይህንንም አገር ውስጥ በማምረት መተካት አሳካች። ከዚያ የውጪ ንግድን አጠናከረች። እኛም ይህን ካላደረግን በአጭር ጊዜ መፍትሔ ማግኘት አይቻልም።

ሌላው ለውጭ ምንዛሬው ችግር ተደርጎ የሚነሳው የትይዩ ገበያው ማንሰራራት ነው። መንግሥት ትይዩ ገበያው ለማዳከም ጥቂት ሕገወጥ ሻጮችን ሲያስርና አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወስድ እንጂ የፖሊሲ ለውጥ ሲያደርግ አልታየም። ለአብነትም አሁን ዶላር በጥቁር ገበያ ከ42 ብር በላይ ይሸጣል።

ትይዩ ገበያ ላይ ከዚህ ቀደም ያልኩት ነው የሆነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት የትይዩ መገበያያዎችን ሲዘጋ 38 እስከ 40 ይገባል ብዬ ነበር። ይህን ለመገመት ነብይነት አይጠይቅም። በኢኮኖሚ ፖሊሲ ትንተና ላይ ተነስቼ ስላልኩት ነው ትክክል የሆንኩት። እነዚህን ሰዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ ሲወሰድ ተጋላጭነታቸው ይጨምራል። ትርፍ ካላገኙበት እንዲህ ዓይነቱ ሕገወጥ ግብይት ውስጥ አይገቡም።

እነዚህ ሰዎች በሕጋዊው መንገድ ያልተሟላ ፍላጎትን ነው የሚያረኩት። ስለዚህ ይህ ፍላጎት ለምን መጣ የሚለው ማወቅ ያስፈልጋል። ለመድኀኒት ግዢ ነው ወይስ ዕቃዎች አምጥቶ ትርፍ ለማግኘት በሚደረግ ፉክክር የተፈጠረ ነው የሚለው መለየት አለበት።

ሌላው ደግሞ የትይዩ ገበያ መስፋፋት ፓለቲካ እንድምታ ሊኖረው ይችላል። ፖለቲካዊ ችግር ሲያጋጥሙ ሰዎች ያላቸውን ገንዘብ ይዘው መውጣት ይፈልጋሉ። የሰረቁ ሰዎችም ብራቸውን በዶላር ማውጣት ይፈልጋሉ። ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚ አለመተማመን ያዩ ሰዎች ከብር ይልቅ በዶላር እንያዝ ይላሉ። እነዚህን ፍላጎቶች የአስተዳደር እርምጃው መገደብ ይቻላል ወይ? አይችልም። ነገር ግን ለችግሮቹ መፍትሔው እንደመፈለግ ይልቅ ቀላሉን መንገድ ነው መንግሥት እየተከተለ የሚገኘው። በማፈንና በማሰር የትይዩ ገበያውን ማጥፋት አይቻልም።

ዓለም ባንክ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፓርት እጥረቱን ለመፍታት የውጭ ምንዛሬ ተፎካካሪና በገበያ መደረግ ይኖርበታል ብሎ ነበር። እዚህ ላይ ምን አስተያየት አሎት?
ይህ በፍፁም የሚሆን አይደለም። ይህ ከተተገበረ ዶላር በትይዩ ገበያው 60 ብር ይገባል። ሰዎች ገንዘባቸውን በዶላር እንዲቀይሩ ይገፋፋና የባንኮችን ጤናማ የፋይናንስ ደኅንነት ያናጋል።

ለዚህ ደግሞ ሱዳንን ማየት ይቻላል። ሱዳን 28 ፓውንድ 1 ዶላር ነበር በአንድ ሰከንድ ወደ 48 አደገ። ከዚያም ሕገወጥ ገበያ ላይ 52 ገባ። በዚህ የተነሳ የዳቦ ዋጋ በአራት እጥፍ አደገ። እናም አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ገበያ መር ነፃ የወጭ ገበያ ከተተገበረች ሱዳን የደረሰው ቀውስ ነው የሚያመጣው። ይህን የሚመክር ጠላት እንጂ ወዳጅ ነው ብዬ አላምንም።

መንግሥት ብዙን ጊዜ ወጪ ላኪዎች ማበረታት ላይ ብቻ ትኩረት ያደርጋል። ለምሳሌ ለዓመታት እንደ ዘይትና ስንዴ ያሉ ምርቶች አገር ውስጥ ማምረት እየተቻለ ከውጭ ሲገቡ ነበር። በሌላ በኩል ከመቶ ሚልዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማምጣት ላልቻለው የጨርቃጨርቅ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ተስጥቷል።

አይሠጥም! ይሔ መንግሥት የወደድኩለት አንድ ነገር ይህን ማመኑ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲመጡ የወደድኩላቸው አንድ ነገር እርሻ ላይ እና መስኖ ላይ አተኩራለው አሉ፤ ያ ቁልፍ ነገር ነው። የበፊቱ ኢሕአዲግ የተሳሳተው አንዱ ነገር ወደ ኢንዱስትሪ ሲሔድ የምግብ አቅርቦት መሳካቱን ከግምት ውስጥ አላስገባም ነበር።

ይህም የማይክሮ ኢኮኖሚክ ችግር አምጥቷል። ለምን የምግብ ዋጋ ግሽበት ላይ ያለው ድርሻ ወደ 60 በመቶ ስለሆነ ነው። የኢንዱስትሪና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ያለው ሠራተኛ እጁ ላይ ያለውን ሊገዛ ሲል የምግብ ዋጋ ይጨምራል። የምግብ ዋጋ ሲጨምር ኹለት ነገር ያመጣል፦ የዋጋ ግሽበትና የምጣኔ ሀብት መዛባት ያመጣል። ይህ ደግሞ የአገሪቷ ገንዘብ ከውጭ አገራት መገበያያ አንፃር እንዲወርድ ያደርጋል። ዓለም ዐቀፍ ገበያ ላይ ተፎካካሪ አገሪቷ መሆን አትችልም ማለት ነው። የበፊቱ ኢሕአዴግ የተሳሳተው የምግብ አቅርቦትን መዘንጋቱ ነው። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከመጡ ግን ስንዴና ዘይት ለማምረት ታስቧል። ይህ በሌሎች ምርቶች ላይ መበረታታት አለበት።

በሌላ በኩል መንግሥት የአገር ውስጥ ባለሀብት ከማበረታታት ይልቅ የውጭ ባለሀብቶች ቅድሚያ ይሰጣል ተብሎ ይታማል። በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ?
በእኔ ግምት መንግሥት ይህን አላደረገም። ለምን ቢባል የመንግሥት ዋና ችግሩ የውጭ ምንዛሬ ነው። ስለዚህ በምን መልክ የውጭ ምንዛሬ ላግኝ ስትል ከአገር ውስጥ ኢንቨስተር ይልቅ የሚገኘው ከውጭ ባለሀብቶች ነው። ኹለተኛ የእኛ የግል ዘርፍ በእኔ ግምት በጣም ደካማ ነው። የእኛ አገር መንግሥት ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ ድርሻ አለው ይባላል እንጂ እንደውም በእኔ ግምት የግሉ ነው ትልቅ ድርሻ ያለው፤ ችግሩ ግን የግል ዘርፍ ደካማ ነው።

ከፋፍለን ስናየው የግሉ ዘርፍ ግብርናና ግብርና ያልሆነ ብለን ማየት እንችላለን። እርሻ 80 በመቶ የአገሪቷን የሥራ ኀይል ይይዛል። 80 በመቶ የግብርናው ዘርፍ አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደሮችን ይይዛል። ግብርና ያልሆነው ዘርፍ ደግሞ በኹለት ሲከፈል ኢንዱስትሪና ኢንዱስትሪ ያልሆነ ቢባል የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ከ90 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው የግሉ ዘርፍ ነው።

ሌላው ጉዳይ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ነው። በስድስት ዓመታት ውስጥ ትልቁ የዋጋ ግሽበት ባለፈው ወር ላይ በ20 ነጥብ 9 በመቶ ታይቷል። አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱም 16 ነጥብ 5 በመቶ ድርሷል። ይህስ ምን ያሳያል?

አዎ! በጣም ችግር ነው። ኹለት ነገር የሚያሳይ ይመስለኛል። አንደኛው ትንሽ ግልጽነት አሁን ተጀምሮ ይሆናል። ሪፖርቱ ላይ ሁሌም የሚታየው አጠራጣሪና ከነባራዊው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር ትንሽ ነው። በግል ሕይወቴ የተገነዘብኩት ሁሉም የምግብ ዓይነቶቸ ቢያንስ 50 እና በ60 በመቶ ጨምሯል ባለፉት ኹለት ዓመታት ጨምሯል፤ ነገር ግን ሪፖርት በመንግሥት የተደረገው ከዚህ ተቃራኒ ነው።

ኹለተኛው ባለፈው አንድ ዓመት ከባድ የምጣኔ ሀብቱ ላይ መቀዛቀዝ ተከስቷል። ባንኮች ብዙ አያበድሩም። ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች ለመግዛት ሲባል የግብርና ምርቶች በርካሽ እየተቸበቸቡ ነው። ሥራ እጥነት ተባብሶ ቀጥሏል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን ከፍተኛ የብድር ጫና፣ ሥራ አጥነትና የጥቁር ገበያ መስፋፋት እንዲሁም የምጣኔ ሀብት መቀዛቀዝ ይታያል። ታዲያ አገሪቷ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናት ማለት ነው።

ከባድ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ መሆናችን ምንም ጥያቄ የለውም። መንግሥት መጀመሪያ ችግሩን ማመን አለበት። ይሔን ለሕዝብ ካስረዳ በኋላ ብቻውን ስለማይችለው ባለሙያዎችን ከውጭም ከውስጥ ሰብስብ አድርጎ ማነጋገር ያስፈልጋል። የምግብ አቅርቦትን እንዴት ልጨምር፣ የክፍለ ኢኮኖሚ ማነቆ ምንድነው፣ ኢንዱስትሪው ለምንድነው የማያድገውና አማራጭ ፋይናንስ እንዴት ይገኛል የሚለውን ተነጋግሮ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል። ከዚያም እንዴት ምጣኔ ሀብቱ መመራት እንዳለበት ቢያንስ የአምስት ዓመት ፍኖታ ካርታ መሥራት አለበት።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምጣኔ ሀብታችን በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ብለው ነበር። ለአብነትም የኢኮኖሚው ዕድገት 9 በመቶ እንደሚሆንና በአገሪቷ ታይቶ በማይታወቅ ወደ 23 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች ብለው ነበር። ይህንን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እንዴት ያዩታል?

ይህ ቁጥር የተጋነነ ወይም ስህተት ሊሆን ይችላል። አገሪቷ ከብድር፣ ከዕርዳታ፣ ከውጪ ንግድና ከሐዋላ እንዲሁም ከሌሎች ምንጮች የምታገኘው ቢደመር ይህን ያህል ሊሆን አይችልም። አገሪቷ 23 ቢሊዮን ዶላር አግኝታለች ማለት የወጪ ንግድ ሙሉ ለሙሉ ሸፍና ትርፍ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ አግኝታለች እንደ ማለት ነው። ይህንን ደግሞ ለማመን ያስችግራል።

የኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት በየዓመቱ 9 እና 10 በመቶ አሳይቷል ተብሎ በመንግሥት ይነገራል። መሬት ላይ ወርዶ የምናየው እና በሪፖርት የሚወጣው ነገር ይለያያል። የምጣኔ ሀብት ዕድገት ትክክለኛውን ነገር ያሳያል ማለት ይቻላል?

በመንግሥት የሚነገረው ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት የተጋነነ ነው። ባደረኩት ጥናት መንግሥት እውነተኛውን የዕድገት መጠን እንደማይነገረን ነው መረዳት የቻልኩት። የአገሪቷ ዕድገት ምንጩ ምንድነው ብዬ አጠናሁት። ከኢንቨስትመንት ወይም ከካፒታል አኩሙሌሽን (የመዋዕለ ነዋይ ወይም ካፒታል ክምችት) ወይም ቴክኖሎጂን መሰረት በማድረግ ነው። የካፒታል ድርሻ ከአራት በመቶ አይበልጥም። ቴክኖሎጂ አስተዋፅዖ ከአንድ በመቶ አይበልጥም። በጣም በቴክኖሎጂ ያደጉት አገራት ኹለት በመቶ ነው የሚያድጉት። የግብርና ዘርፉም ዕድገቱ አነስተኛ ነው። መዋዕለ ነዋይ ቢያድግም ለምጣኔ ሀብት ያለው ድርሻ አነስተኛ ነው። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቢበዛ ምጣኔ ሀብቱ 6 ወይም 7 ቢሆን ነው ዕድገቱ። ይሔም ቢሆን ያለማጋነን በጣም ጥሩ የሚባል ነው። የአፍሪካ አገራት አማካይ ዕድገት እንኳን አምስት በመቶ አይደርስም።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here