የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዲሶቹ ተሿሚዎች እነማን ናቸው?

0
743

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ በጸደቀው አዋጅ 1133/2011 መሰረት ሰኔ 7/2011 አራት ተጨማሪ የቦርድ አባላትን መሾሙ ይታወቃል። የቦርድ አባላቱ ምልመላ ሒደትን ለማስተባበር ሰባት አባላት ያሉት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ተግባር በመግባት ሥራውን ማከናወኑን ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለአዲስ ማለዳ በላከው ዝርዝር መረጃ አስታውቋል።

በዚህ መሰረትም መልማይ ኮሚቴው፣ ዕጩ የቦርድ አባላት መልማይ ኮሚቴ የውስጥ አሰራር መመሪያ በማውጣት የእጩ ቦርድ አባልነት ጥቆማ ከሃያ በላይ በሚሆኑ የመገናኛ አውታሮች ለሕዝብ እንዲገለፅ በማድረግ 200 ጥቆማዎች በስልክ፣ በኢ-ሜይል፣ በአካል እና ፋክስ አማካኝነት ተቀብሎ በሦስት የማጣሪያ ምዕራፎች እንዲያልፉ ተደርጓል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ በአዋጁ አንቀፅ 6 የተጠቀሱትን መሰረታዊ ተፈላጊ መስፈርቶች ማለትም ኢትዮጵያዊ ዜግነት፣ የትምህርት መስካቸው በአዋጁ የተጠቀሱት ስለመሆናቸው (በሕግ፣ ፖለቲካ ሳይንስ፣ ሕዝብ አስተዳደር፣ ስታትስቲክስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ከምርጫ ጋር ተያያዥ የሆኑ መስኮች)፣ በሥራ ዘርፉ ብዙ ተቋማት ውስጥ ስለመሥራታቸው፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ስላለመሆናቸው፣ እንዲሁም ፍቃደኝነታቸውን በማረጋገጥ ከቀረቡት እጩዎች መካከል 20 የሚሆኑት ወደ ኹለተኛው ማጣሪያ እንዲያልፉ ሆኗል።

በኹለተኛው ማጣሪያ ደግሞ የተጠቋሚዎች የትምህርት ዝግጅት እና የሙያ ስብጥር፣ በዘርፈ ብዙ መድረኮችና ተቋማት ስለማገልገላቸው እንዲሁም፣ በተነፃፃሪነት ገለልተኛ በሆኑ ተቋማት ውስጥ ስለመሥራታቸው፣ በተቻለ አቅም የብሔር፣ የፆታ ስብጥርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ከ20 ዕጩዎች ውስጥ፣ 10 ዕጩዎች ለሦስተኛው የማጣሪያ ምዕራፍ ተሻግረዋል።

በመጨረሻው ምዕራፍ፣ የመልካም ሥነ ምግባር እና ስብዕናቸው፣ ኀላፊነት የመሸከም ብቃታቸው፣ ሐሳብን የመግለፅ ችሎታቸው፣ ለምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ለውጥ ያላቸው ራዕይ እና አገራዊ ምልከታን እንዲሁም፣ የቡድን ሥራ ልምዳቸውን መሠረት በማድረግ ላለው አራት ክፍት ቦታ ለእያንዳንዱ ኹለት ኹለት፣ በጠቅላላው ስምንት ዕጩዎችን ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይይ በማቅረብና ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንዲሾሙ ተደርጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልማይ ኮሚቴው አጠቃላይ አካሔድ እና ስለደረሰበት ደረጃ በኮሚቴው የቀረቡትን የመጨረሻ 8 ዕጩዎች በተመለከተ ከ20 በላይ የፓርቲዎች አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል። የመልማይ ኮሚቴውን የመጨረሻ ዕጩዎች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተሰጠውን ግብዓት መሰረት በማድረግ ብዙወርቅ ከተተ፣ ውብሸት አየለ፣ ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር) እና አበራ ደገፋ (ዶ/ር) በዕጩነት ተለይተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው እንዲሾሙ ተደርጓል። እነዚህ አዳዲስ ተሿሚዎች ለመሆኑ እነማን ናቸው?

1. ብዙወርቅ ከተተ
ትምህርት ዝግጅት
በ1952 በአዲስ አበባ የተወለዱት ብዙወርቅ ከተተ፣ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በግሪክ አገር፤ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ደሞ በኩባ ሃቫና ዩኒቨርሲቲ የውጪ ቋንቋዎች ትምህርት ክፍል በሥነ ቋንቋ ኹለተኛ ደረጃ ዲግሪ ሲያገኙ፣ ከአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተመርቀዋል።
የሥራ ልምድ
ብዙወርቅ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ፣ ወደ አገራቸው በመመለስ በበርካታ ተቋማት ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ በተለያዩ አገራት የውጪ ባለሞያ ሆነው በመሥራትም ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ባለሞያ ናቸው። ካገለገሉባቸው መሥሪያ ቤቶች መካከል የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ አክሽን ኤይድ ኢንተርናሽናል (በለንደን፣ በኢትዮጵያ፣ በሩዋንዳ በአገር ዓቀፍ ዳይሬክተርነት) ሴፈር ወርልድ የምሥራቅ አፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ በመሆን ሰርተዋል።

አደጋ መከላከልና መልሶ ማልማት ላይ የሚሠራው የጀርመን አማካሪ ድርጅት ውስጥም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፕሮጄክት አስተባባሪ ሆነው የሠሩት ብዙወርቅ፣ ከ1999 ጀምሮ በአየርላንድ የልማት ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የመልካም አስተዳር ፕሮግራም ኀላፊ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
በተጨማሪ ብዙወርቅ በማኅበረሰባዊ ተሳትፎ በማድረግ “ዜጋ ለእድገት” የተሰኘ በመልካም አስተዳደር፣ በአቅም ግንባታ እና ሲቪክ ተሳትፎን በማበረታታት ላይ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት መሥራችና የቦርድ ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ኅብረት መሥራችና የቦርድ አመራር በመሆን አገልግለዋል።
ብዙወርቅ የአማርኛ፣ የእንግሊዘኛ፣ የፈረንሳይኛ እና የስፓኒሽ ቋንቋዎችን ይናገራሉ።

2. ውብሸት አየለ ጌጤ
የትምህርት ዝግጅት
ውብሸት አየለ በ1947 በአዲስ አበባ ከተማ የተወለዱ ሲሆን፣ በ1980 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል።
የሥራ ልምድ
ውብሸት ከፍተኛ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በሕግ ባለሞያነትና በከፍተኛ አማካሪነት አገልግለዋል። በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በዳኝነት ሰርተዋል። ከዳኝነታቸው በተጨማሪ የራሳቸውን የሕግ አማካሪ ቢሮ በመክፈት የሕግ አማካሪና ጠበቃ ሆነው ሠርተዋል። በፍትሕ ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የጠበቆች አስተዳደር የሥነ ምግባር ጉባኤ የኮሚቴ አባል በመሆን አስተዋፅዖ ሲያበረክቱ ቆይተዋል።

ውብሸት በአገሪቱ የመጀመሪያው የሆነውን የግል የዳኝነት ማዕከል በመመስረት እዛም በዋና ጸሐፊነት ሰርተዋል፤ ከዚያም በተጨማሪ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነውን የመታረሚያ ጊዜያቸውን የጨረሱ ወጣት ጥፋተኞች ማገገሚያ ማዕከልን በማቋቋም አስተዳዳሪ ሆነው አገልግለዋል።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ራሱን እንደ አዲስ ማዋቀር ከጀመረበት ካለፉት ወራት አንስቶ ደግሞ ቦርዱን በማማከር፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ውይይት በማስተባበር፤ እንዲሁም ሌሎቹን የቦርድ እንቅስቃሴዎች ላይ በሞያቸው ከፍተኛ ተሳትፎ ያደረጉ ግለሰብ ናቸው። ውብሸት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር በሚገኘው የፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ምክር ቤት ሰብሳቢ በመሆንም እያገልገሉ ይገኛሉ።

ውብሸት ከሞያቸው በተጨማሪ፣ የሲቪክ ማኅበራትና ማኅበረሰባዊ ተሳትፎአቸው ከፍተኛ ሲሆን፣ የዓለማየሁ ኀይሌ ፋውንዴሽን፣ የፓን አፍሪካ የሕግ ባለሞያዎች ኅብረት፣ አትዮ ፓረንትስ ትምህርት ቤት እና የተለያዩ ማኅበራት መሥራችና አስተባባሪ ናቸው። ውብሸት የአማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው።

3. ጌታሁን ካሳ (ዶ/ር)
የትምህርት ዝግጅት
ጌታሁን ካሳ አተይ (ዶ/ር) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1986 አግኝተዋል። ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከክዊንስ ዩኒቨርሲቲ ኢንግላንድ በ1994፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በ2010 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሙያቸውን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ወስደዋል።
የሥራ ልምድ
ጌታሁን ካሳ ከ1986 ጀምሮ በተለያዩ የኀላፊነት ቦታዎች በሞያቸው አገልግለዋል። ከእነዚህም መካከል በትግራይ ክልል ዐቃቤ ሕግነት፣ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተለያዩ ቢሮዎች በአማካሪነት፣ በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ የተለያዩ ኢምባሲዎች እና የመንግሥት ተቋማት ሰርተዋል። በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ኮሚሽንም ዋና ዳይሬክተር በመሆንም አገልግለዋል። ከሕግ ባለሞያነታቸው፣ አማካሪነታቸው እና መምህርነታቸው በተጨማሪ በአሁኑ ሰዓት በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሥር የሚገኘው የሕግ እና የፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ውስጥ አባል ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ጌታሁን የተለያዩ የምርምር ጽሁፎችን በአገር ውስጥና በዓለም ዐቀፍ የኅትመት ውጤቶች ላይ ያሳተሙ የሕግ ባለሞያ ሲሆኑ፣ በምርምር ሥራዎቻቸውና ጽሁፎቻቸው በአብዛኛው በሰብኣዊ መብቶች፣ በምርጫና የምርጫ ግጭት አፈታት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተግባርና ኀላፊነት ላይ ያተኮሩ ናቸው።
ጌታሁን ትግርኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን ሙሉ ለሙሉ የሚችሉ ሲሆን፣ የተለያዩ የሞያ ማኅበራት አባልና የተለያዩ ወቅታዊ የትምህርታዊ ኅትመት ሥራዎች (Academic Journals) አርታኢም ናቸው።

4. አበራ ደገፋ (ዶ/ር)
የትምህርት ዝግጅት
አበራ ደገፉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ የመጀመሪያና ኹለተኛ ዲግሪያቸዉን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሕግ እንዲሁም፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በተመሳሳይ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ወርክ እና ሶሻል ዴቨሎፕመንት አግኝተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኔዘርላንድስ ከሚገኘዉ ኢንስቲትዩት ፎር ሶሻል ስተዲስ ማዕረግ የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ አላቸዉ። አበራ በኮፐንሃገን እና በፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ ባሉ የሰብኣዊ መብት ማዕከላት የምርምር እና የትምህርት ቆይታም አድርገዋል። ከዚያም በተጨማሪ በተለያዩ የአውሮፓና የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት የተዘጋጁ የተለያዩ የሥራ ላይ ሥልጠናዎችን ወስደዋል።
የሥራ ልምድ
አበራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከመደበኛ የመምህርነት ሥራቸዉ ባሻገር በተለያዩ ከፍተኛ የኀላፊነት ቦታዎች ላይ በሙያቸው በማገልገል ላይ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በዘመን ባንክ፤ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠበቆች አስተዳደር ጉባዔ እና በኦሮሚያ የሕግ ጆርናል የቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል።
በርካታ የምርምር ጽሁፎችን በተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም ዐቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተምም ችለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም ተማሪዎችን በማስተማር ሥራ ላይ የሚገኙት አበራ በ2009 ከዩኒቨርሲቲው የሚሰጠዉን “የላቀ የማስተማር አበርክቶት” ተሸላሚ ናቸው። አበራ የአፋን ኦሮሞ፣ አማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋዎችን ሙሉ ለሙሉ መናገር ይችላሉ።

_____________________________________

ከላይ ከቀረቡት ዕጩዎች መካከል ውብሸት አየለ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመረጡ ሲሆን፣ የተወካዮች ምክር ቤት አስቀድሞ የሾማቸው የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ በምርጫ ቦርዱ መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2011 አንቀጽ 28 መሰረት በሰብሳቢነታቸው እንደሚቀጥሉ በፓርላማው ውሳኔ ተመልክቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here