የምሥራቅ ጎጃም ገበሬዎች በጤፍ ላይ የ400 ብር ቅናሽ አደረጉ

0
924
  • የገበሬ ማኅበራቱ በቆሎ በኩንታል 800 ብር በማከፋፈል ላይ ናቸው

በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ሦስት ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየኖች ነጭ ጤፍ በኩንታል እስከ 400 ብር በመቀነስ የገበያ ንረቱን ለማረጋጋት እየሠሩ መሆኑ ታወቀ። ሌሎች ወረዳዎችም ይህንን አርዓያ በመከተል የገበያ ማረጋጋት ሥራውን እየሠሩ መሆኑን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ገበያው እስኪረጋጋ ድረስም ለመንግሥት ሠራተኞችና ለሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት በቋሚነት የሚታደል ይሆናል።

በዚህም መሠረት ነጭ ጤፍ ከሚሸጥበት ዋጋ ጎዛምን 400 ብር፣ ሞጣ 200 ብር፣ ጊዮን 150 ብር ገበያ በመቀነስ ለማቅረብ መወሰናቸውን የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ጋሻዬ ጌታሁን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በጎዛምን የሚገኘው ዩኒየን ግን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተባለው ዋጋ እህል ማቅረብ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የጎዛምን ሁለገብ የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ዩኒየን ከነጭ ጤፍ በተጨማሪ ሌሎችንም የምርት ዓይነቶች ያቀርባል ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ዩኒየኑ ነጭ ጤፍ በኩንታል በ2 ሺሕ 400 ብር፣ ሰርገኛ ጤፍ በ2 ሺሕ 300 ብር፣ ቀይ ጤፍ በ2 ሺሕ ብር፣ በቆሎ በ800 ብር፣ 1ኛ ደረጃ የዳቦ ዱቄት በ1 ሺሕ 800 ብር እያቀረበ ይገኛል።

ዩኒየኑ አሁን እያደለው ያለውን ጤፍ እርካሽ በነበረበት ወቅት ገዝቶ ያከማቸው መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ጋሻዬ፣ የክልሉ መንግሥት ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ክትትል አድርጎ እርምጃ እስኪወስድ ድረስ ገበያ የማረጋጋት ሥራው እንደሚቀጥልና ከዞን እስከ ክልል፣ ብሎም እስከፌደራል ድረስ ገበያ የማረጋጋት ሥራው እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።

የዞኑ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ማስፋፊያ ጽሕፈት ቤት የግብይት ቡድን መሪ ሙሉሰው አዲስ፣ በሰው ሰራሽ የዋጋ ንረቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎችና የመንግሥት ሠራተኞች እንዳይጎዱ በማሰብ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ የሰብል ምርት ለማቅረብ እንደተዘጋጁ ገልጸዋል።

በደብረ ማርቆስ በቆሎ በአንድ ሺሕ ብር እንደሚሸጥ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ሙሉሰው፣ የዞኑ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ከዩኒየኑ በቆሎ በስምንት መቶ ብር በመግዛት ለሸማቹ ማኅበረሰብ በአንድ ሺሕ ብር ማቅረቡን አውስተዋል። የዳቦ ዱቄትም በስፋት እየተከፋፈለ መሆኑን አክለው ገልጸዋል።

አንዳንድ በመንግሥት የማይታወቁ ስግብግብ ነጋዴዎች በምግብ እህሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሕዝቡን ለችግር እየዳረጉት መሆኑን ያነሱት ሙሉሰው፣ እነዚህ ግለሰቦች ተይዘው ለሕግ እስኪቀርቡና ዋጋውም እስኪረጋጋ ድረስ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here