የ‘ፕራይቬታይዜሽኑ’ ድርድር ጉዳይ ‘ዐሥር ጊዜ ለካ፥ አንድ ጊዜ ቁረጥ’!

0
272

በኢትዮጵያ ውስጥ ከመጣው የፖለቲካ ለውጥ ጋር ተያይዞ፥ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት በምጣኔ ሀብት በኩል ሊወስዳቸው ካሰባቸው እርምጃዎች መካከል አንዱ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታነት እንዲዘዋወሩ ማድረግ ይገኝበታል። ለዚህ እርምጃ ከተለዩት የልማት ድርጅቶች መካከል ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ መብራት ኀይል፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት እና የስኳር ፋብሪካዎች የሚገኙበት ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍልን የሚወክሉ ሃያ አንድ አባላት ያሉት የአማካሪ ቡድን በማቋቋምና በማስጠናት ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።

እነዚህን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታነት የማዘዋወር የፖሊሲ አቅጣጫ ውሳኔ ዓላማዎች የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ዕድገት ማስቀጠልና የምጣኔ ሀብት ትራንስፎርሜሽን ማፋጠን፣ የልማት ፋይናንስ አቅርቦት፣ የግሉ ዘርፍን ልማትና ተሳትፎ ማሳደግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ተወዳዳሪና ምርታማነት ማሳደግ እና የመንግሥት ድርጅቶችን የፋይናንስ አቅም ማጠናከር እንዳለባቸው በቅርቡ በጸደቀው የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ላይ በግልጽ ተቀምጧል።

በርግጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ባለሀብትነት መቀየሩ ላይ የምጣኔ ሀብት ምሁራን በመርኅ ደረጃ በአጠቃላይ ስምምነት ቢኖራቸውም፥ በተለይ ወደ ዝርዝር ጉዳዮች በሚገቡበትና አፈፃፀሙን በተመለከተ የትኞቹ ድርጅቶች ይሸጡ በሚሉት ላይ ግን ስምምነት እንደሌላቸው አዲስ ማለዳ ለመታዘብ ችላለች።

በዓለም ላይ በመንግሥት ሥር የነበሩ የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል የማዘዋወር ውሳኔ በተለይ የሶቪየት ኅብረት መፈራረስን ተከትሎ የቀዝቃዛቀው ጦርነት በማብቃቱ በ1980ዎቹና 90ዎቹ በርካታ የምሥራቅ አውሮፓ አገሮች፣ ራሺያ እንዲሁም የአፍሪካ አገራት ማካሔዳቸው ይታወቃል። ይሁንና የአገራቱ ተመክሮ የተፈለገውን ወይም የተጠበቀውን ያክል አመርቂ እንዳልሆነ እንዲያውም አገራቱን ለምጣኔ ሀብታዊ ኪሳራ መዳረጉን የሚከራከሩ በርካታ ምሁራን አሉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰደ ባለው የፖሊሲ አቅጣጫ ለውጥ ላይም እንዲሁ የአገራችን የምጣኔ ሀብት ምሁራን በኹለት ጎራ ተከፍለው በጉዳዩ ዙሪያ የመከራከሪያ ነጥቦቻቸውን እየሰነዘሩ እንዳሉ ይታወቃል።

አንዳንዶቹ የምጣኔ ሀብት ምሁራን የመንግሥት ሥልጣን የያዙትን የዘርፉን ባለሙያዎች ጨምሮ እነዚህን የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ወደ ግል ማዘዋወር ለአገር ይጠቅማል በማለት ድጋፋቸውን በማስረጃ ያስደግፋሉ፤ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰትን እንዲጨምር በማድረግ ድርጅቶቹ እንዲስፋፉ ያደርጋል፣ የቴክኖሎጂ እውቀት ሽግግር እንዲኖር ያስችላል፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራል የሚሉ የመከራከሪያ ጭብጦችን በማንሳት። በተጨማሪም ከመንግሥት ይዞታነት ወደ ግል የሚደረገው ዝውውር ሌሎች የምጣኔ ሀብት ዘርፎች ከማነቃቃቱም ባሻገር መንግሥት በምጣኔ ሀብት ያለውን ጣልቃ ገብነት እንደሚቀንስ ያምናሉ።

በሌላ ወገን ያሉ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን በበኩላቸው የመንግሥትን የልማት ድርጅቶች ወደ ግል ባለቤትነት ማዞር አገር ይጎዳል ይላሉ። በተለይ ከአንፃራዊ ጥቅም አንፃር (comparative advantage) በአገር ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል መከራከሪያም ያቀርባሉ። በመከራከሪያ ነጥባቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደምሳሌ በመውሰድ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ያስረዳሉ። አየር መንገዱ ላለፉት 70 ዓመታት በጥሩ ሥም፣ በአትራፊነትና ከፍታውን ጠብቆ በመሔድ ስኬታማ ድርጅት በመሆኑ በከፊል ወደ ግል ይዞታነት እንዲዞር ማድረግ ከአንጻራዊ ጥቅም አንፃር ለኢትዮጵያ አይበጅም ሲሉ ያስረዳሉ። የአየር መንገዱ አንድ የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚና አሁን ኩባንያውን በመምራት ላይ የሚገኙትም ይህንን ሐሳብ እንደሚጋሩትና ውሳኔ ከመደረሱ በፊት በደንብ ሊጤን እንደሚገባ በተለያዩ መንገዶች መግለፃቸው ይታወቃል።

አዲስ ማለዳ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ወደ ግል ይዞታነት የሚደረጉ ዝውውሮች በግልጽ የሚያመጡት ጥቅምና ጉዳት እንዲሁም ትርፍና ኪሳራ በጥንቃቄ ሊጠና ይገባል ትላለች። መንግሥት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ በምሁራን መካከል የሚካሔድ ተከታታይ ውይይቶችንና ክርክሮችን ማዘጋጅት ይጠበቅበታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያዋቀሩት አማካሪ ቡድንም ሥራውን በከፍተኛ ትጋትና ጥንቃቄ በመሥራት፣ የዘርፉን ምሁራን በማነጋገር እና የአገራትን ተሞክሮ ግምት ውስጥ ያስገባ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል በማለት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

እንደአዲስ ማለዳ ያሉ መገናኛ ብዙኀንም መከራረሪያ መድረኮችን የማመቻቸትና መንግሥትም ሆነ ሕዝብ በጉዳዩ ዙሪያ ግልጽ መረጃ እንዲኖራቸው፤ እንዲሁም በመጨረሻም መንግሥት ለሚወስደው ውሳኔ ፋይዳ ያላቸው ግብዓት እንዲያገኝ ለማድረግ እገዛ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ውሳኔው ከባድ፣ ውጤቱም ብዙ መዘዝ የሚያስከትል በመሆኑ የድርጅቶቹ ከመንግሥት ወደ ግል ይዞታነት መቀየር ጥልቀት ያለው ጥናትና ድርድር ብልህ ውሳኔ ያሻዋል በማለት አዲስ ማለዳ አበክራ ታሳስባለች። ብሒሉስ ‘ዐሥር ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ!’ አይደል የሚለው!

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here