ማክሰኞ፣ ሰኔ 18/2011 ጠዋት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ አራዳ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ከአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ በተፈጸመው ጥቃት ፖሊስ ጥርጥሬአቸዋለሁ ያላቸውን ሰባት ግለሰቦች አቀረበ። በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የከቀረቡት ተጠርጣሪዎች መካከል ኹለቱ የበረራ ጋዜጣ እና የአስራት ሚዲያ ባልደረቦች መሆናቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
አንዳኛ ተጠርጣሪ በሪሁን አዳነ የዕንቁ መጽሔት አዘጋጅ፣ የውይይት መጽሄት ዋና አዘጋጅና የነበረ ሲሆን በቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ድረስ የአስራት ሚዲያ መስራች አባልና የበረራ ጋዜጣም ባልደረባ ሆኖ ሲገለግል ነበር። መርከቡ ኃይሌ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ጌዴዮን ወንድወሰን፣ ማስተዋል አረጋና ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሲሆኑ ሃየሎም ብርሃኔ የጦር መሣሪያ ይዞ እጅ ከፍንች ተይዞ ተገኝቷል ተብሏል። ጌታቸው አምባቸውም የበረራ ጋዜጣ ባልደራበ እና የአስራት ሚዲያ የፋይናንስ አማካሪ ሆኖ በማገልገል ላይ የነበረ ሲሆን ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ፣ በአማራ ክልል ተፈፀመ በተባለው “መፈንቅለ መንግሥት” እና በአዲስ አበባው ግድያ እጁ አለበት ብሎ ጠርጥሮታል። በተለያየ ደረጃ ባላቸው ተሳትፎ በወንጀሉ ላይ ለመጠርጠር በቂ ምክንያት እንዳለው ገልፆ፤ ሕገ መንግሥታዊ ስርዓቱን ለመናድ ሞክረዋል ሲል ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ የሆኑት ሄኖክ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት መርከቡ ኃይሌና ስንታየሁ ቸኮል የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አመራሮች ሲሆኑ፣ ጌዴዮን ወንድወሰንም የባላደራ ምክር ቤቱ አባል ነው። ሄኖክ እንዳስታወቁት፣ ግለሰቦቹ በፀረ ሽብር አዋጅ መሰረት የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ አደረጉት የተባለው ነገር ተለይቶ በዝርዝር የቀረበ ሳይሆን፣ በደፈናው “በመፈንቅለ መንግሥቱ” ጠርጥሬያቸዋለሁ የሚል መግለጫ ብቻ ለፍርድ ቤቱ ማቅረቡን ተናግረዋል።
“ተጠርጣሪዎቹ ያጠፉት ጥፋት ምን እንደሆነ ሳይነገር የ28 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም፤ ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ይዞ ስላልመጣ፣ የተከበረው ፍርድ ቤት መዝገቡን ይይልን፤ እነዚህን ሰዎች ለመያዝ ምንም የሚያስጠረጥር ምክንያት የለም” ሲሉ ሄኖክ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል።
ማስረጃ ሊያሸሹ ስለሚችሉ በማረፊያ ቤት ቆይተው ምርመራው እንዲቀጥል ፖሊስ በጠየቀው መሰረት፣ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ፖሊስ አደረጉት የሚባለውን ነገር በዝርዝር ለየብቻ እንዲያቀርብ፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ ባለመቅረቡም፤ የምርመራ መዝገብ ይዞ እንዲቀርብ በማለት ለሐምሌ 17 ቀጠሮ ትዕዛዝ መስጠቱንም ጠበቃው አክለው ተናግረዋል።
ፖሊስ የተወሰኑት ተጠርጣሪዎች በሥልክ እየተነጋገሩ ከጉዳዩ ጋር የተገናኘ ነገር ይፈፅሙ ነበር የሚል ጉዳይ ማንሳቱን ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ሄኖክ፣ ፖሊስ ባሕር ዳር የሔዱትም ያልሔዱትም ተሳትፎ አድርገዋል ማለቱን አስታውቀዋል።
ስድስተኛው ተጠርጣሪ የሆነው ሐየሎም፣ ጄኔራል ሰዓረና ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ የአስክሬን ሽኝት ፕሮግራም ላይ “የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ባሉበት ጥቃት ለማድረስ መሣሪያ ይዘው ተገኝተዋል” በሚል መያዙን ፖሊስ ሲያስረዳ፣ ግለሰቡም የጥበቃ ሥራ ስለሚሠራ መሳሪያ እንደያዘ ለፍርድ ቤቱ ማስረዳቱን ሔኖክ ተናግሯል።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጠው እስክንድር ነጋ፣ የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት አባላት በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች ከተፈጸሙት ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት ግንኙነት ሊኖራቸው እንደማይችል አስታውቆ፣ በተለይ ስንታየሁ ቸኮል ከእሱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳለው በመናገር፣ የምክር ቤቱን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በየዕለቱ እየተገናኙ እንደሚወያዩና በኹለቱ መካከል የተደበቀ ሚስጢር አለመኖሩን ተናግሯል።
በፖሊስ የሚፈለጉ ሌሎች የአዲስ አበባ ባለ አደራ ምክር ቤት አባላት መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ኤልያስ ገብሩ፣ ከባሕር ዳር ከተመለሱ በኋላ በቦሌ ክፍለ ከተማ የመታወቂያ ጉዳይ ላይ በሚዲያዎች ላይ አስተያየት ሲሰጡ የነበሩት ሰናይት ታደገን ጨምሮ ሌሎች አባላቶች በፖሊስ ሲፈለጉ እንደነበር ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011



