ኦፌኮና ኦነግ አባላቶቻችን በኦሮሚያ ክልል እየታፈሱብን ነው አሉ

0
619
  • ኦፌኮ የአባሎቹ ቤት መበርበሩንም አስታውቋል

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት በተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር እየዋሉ መሆናቸውን እና በጦር ካምፕ ውስጥ እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል። በነቀምት፣ በጊምቢ፣ በገሊላ ወረዳ ሊሙና በጉጂ ዞን በርካታ የኦፌኮ አመራሮች “ኦነግ ናችሁ” በሚል ሰበብ እየታሰሩ እንደሆነ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ ቲቪ ተናግረዋል። በምዕራብ ጉጂ የሚገኘው የኦፌኮ ጽሕፈት ቤት፣ በአካባቢው ባሉ ኮማንድ ፖስት አመራሮች መበርበሩንና በጽሕፈት ቤቱ የነበረውን አባላቸውን ደብድበው ራቁቱን ጥለውት መሔዳቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

“አብዛኛውን የኦሮሚያ ዞኖች በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥር ናቸው። በነቀምትና በሌሎች አካባቢዎች ኦነግ ናችሁ በሚል ሰበብ ኮማንድ ፖስቱ በርካታ ሰዎችን እያፈሰና እያሰረ ሲሆን፣ ሕዝቡም በሥጋት እየኖረ ነው” ሲሉ ሙላቱ ገለጸዋል።

ኮማንድ ፖስቱ በፍተሻ ሰበብ በኦፌኮ አባላቶች ቤት እየገቡ የግለሰቦችን ሶፋ በመበጣጠስና በመበታተን ከጥቅም ውጪ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ በርና ዕቃ በመሰባበር ሕዝቡን እያሸበሩት መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ሙላቱ፣ በአካባቢው መከላከያውም፣ ኮማንድ ፖስቱም፣ አስተዳደሩም ስለሚያስርና ስለሚፈታ አንዳንድ ሰዎች በማን እጅ መያዛቸውና መታሰራቸው እንኳን እንደማይታወቅ አስረድተዋል።

የኦነግ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ቶሌራ አደባ በበኩላቸው አባሎቻቸው በምሥራቅ ሐረርጌ፣ ጅማ፣ ኢሊባቦርና ወለጋ እየታሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ድርጊቱን በመቃወምና፣ የሚፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ ለኦሮሚያ ክልልና ለፌደራል መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ቢያስታውቁም፣ እናጣራለን፤ ይስተካከላል ከሚል ምላሽ ባለፈ አንድም ማስተካከያ አለመደረጉን አስታውቀዋል።

“ምናልባት ከኦነግ ጋር በጋራ ለመሥራት ከማሰባችሁ ጋር የተያያዘ ይሆን?” በሚል ለሙላቱ ላቀረብንላቸው ጥያቄም ምላሽ ሲሰጡ፣ ለአገር ጥቅም ነው እንሥራ ያልነው፤ መንግሥትን እናግዝ፣ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን ጥረት እናድርግ አልን እንጂ ሰላም እናደፍርስ አላልንም ሲሉ መልሰዋል።

ኦፌኮ እና ኦነግ ውሕደት በመፍጠር ፓርቲያቸውን ለማጠናከር እንደሚሠሩ ለአዲስ ማለዳ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ሌሎች የኦሮሞ ፓርቲዎችም የውሕደቱ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ ተናግረው ነበር። በወቅቱ ድርጅቶቹ፣ እውነተኛ ፌዴራላዊ ስርዓትን ለማረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነትን ለማስፈንና የራስን መብት በራስ መወሰን ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማታቸውን አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here