በአገሪቱ በምሥረታቸው መጀመሪያዎቹ የሆኑት የግል ባንኮች፥ አዋሽ፣ ዳሸንና አቢሲኒያ ባንኮች በያዝነው ዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማስመዝገባቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ። አዋሽ ባንክ 3.3 ቢሊዮን ያልተጣራ፥ ኦዲት ያልተደረገና የተበላሹ ብድሮች ያልተቀነሱበት ትርፍ በማስመዝገብ ከግል ባንኮች መሪነቱን ለሦስተኛ ዓመት ያስጠበቀ ሲሆን፤ ዳሸንና አቢሲኒያ በተመሳሳይ 1.4 እና 1.2 ቢሊዮን ብር በማትረፍ ኹለተኛና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የምሥረታ የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን ለማክበር በዝግጅት ላይ ያለው አዋሽ ባንክ ያስመዘገበው የዘንድሮ ትርፍ ከአምናው የ1.96 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አንጻር የ70 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፤ ከተመሰረተ 24 ዓመታትን ያስቆጠረውና የመጀመሪያዎቹን 21 ዓመታት ከግል ባንኮች ከፍተኛውን ትርፍ በማስመዝገብ መሪ የነበረው ዳሽን ባንክ ደግሞ አምና ካተረፈው የ1.14 ቢሊዮን ብር ትርፍ አንጻር የዘንድሮው የ23 በመቶ ጭማሪ አለው። በተመሳሳይ የአቢሲኒያ ባንክ ትርፍ ከአምናው የ766 ሚሊዮን ብር አንጻር የ57 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።
በሌላ በኩል የተመሰረተበትን ዐሥረኛ ዓመት በማክበር ላይ የሚገኘው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ አንድ ቢሊዮን ኻያ ሚሊዮን ብር ያልተጣራና ኦዲት ያልተደረገ ትርፍ ማግኘቱን አዲስ ማለዳ ከባንኩ ከፍተኛ ኀላፊዎች ያገኘችው መረጃ ያመለክታል። ንብ ኢንተርናሽናል ባንክም ለአንድ ቢሊዮን የቀረበ ትርፍ በማግኘት ዘንድሮ ከፍተኛ ትርፍ ካስገኙ የግል ባንኮች ተርታ ተሰልፏል።
የባንኮቹ የሒሳብ ሪፖርት በውጪ ኦዲተሮች ሲመረመር አሁን ከተጠቀሰው የባንኮቹ ትርፍ አንጻር የተወሰነ ለውጥ ሊኖረው እንደሚችል ቢጠበቅም ልዩነቶቹ ግን ከፍተኛ እንደማይሆን የባለፉት ዓመታት የወጡት የባንኮቹ ሪፖርቶች ያሳያሉ። ለትርፍ መጨመር ምክንያቶች ባንኮቹ ከወለድ፥ ከውጪ ምንዛሬ ኮሚሽንና የተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኙት ገቢ መጨመር እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት ከተለያዩ አገልግሎቶች የሚያገኑት ገቢ ላይ ከፍተኛ ህዳግ በመጨመር ገቢያቸውን ሲያሳድጉ ቆይተዋል።
የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በጣም አትራፊ የሆነ የአገልግሎት ዘርፍ ሲሆን፤ መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ዝግ ማድረጉና በብሔራዊ ባንክ በኩል ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር ማደረጉ ለትርፋማነታቸው ዐቢይ ምክንያት ተደርጎ ይገለፃል።
ዘርፉ ባለፉት ሦስት ዓመታት እያሳየ የመጣው ዕድገት ከመቼውም ጊዜ የበለጠና አገሪቱ ከምትገኝበት የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የተቀዛቀዘ የንግድና ኢንቨስትመንት አንጻር አስገራሚ እንደሆነ ለዘርፉ ቅርበት ያላቸው ባለሙያዎች ይናገራሉ። ይሁን እንጂ የአገሪቱ ሁኔታ ግጭት እያየለበት የመጣ በመሆኑና በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽኖ በመበራከቱ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተበዳሪዎች ብድራቸውን ለመመስ እንዲቸገሩ አድርጓቸዋል። ይህም የብሔራዊ ባንክ የሥራ ኀላፊዎች እያስጨነቀ የመጣ ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል። በዚህ ጉዳይ ላይም የባንኩ ኀላፋች ከባንኮቹ ፕሬዝዳንቶች ጋር በቅርቡ መምከራቸው ይታወቃል። በመሆኑም አብዛኞቹ ባንኮች ዘንድሮ ትርፋቸውን ሲያሰሉ የተበላሹ ብድሮች ባይመለሱ የሚፈጠርን ሪስክ ለመቀነስ የሚይዙት መጠባበቂያ (provision) ከፍ እንዲል አድርጓል።
የአዋሽ እና የኦሮሚያ ባንክ ፕሬዘዳንቶች ፀሐይ ሽፈራውና አቤ ሳኖ በተመሳሳይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የባኮቻቸው ትርፍ ገና ኦዲት ስላልተደረገ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸገሩ ተናግረው የኦዲት ሥራው ካለቀ በኋላ ግን ሙሉ መረጃውን ለሕዝብ እንደሚደርሱ ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011



