- ከ1000 በላይ ቤቶች በሕገወጥ መንገድ ተሰርተዋል
- ባለቤቱ ፈረንሳዊ የሆነ አንድ ሎጅ በመቃጠሉ ባለሀብቱ የ25 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቋል
በሐረሪ ክልል ሐኪም ወረዳ፣ አማሬሳ ቀበሌ የሚኖረው ሞሐመድ አሚር የሐረርን ሕዝብ እንኳን በዘርና በሃይማኖት እርስ በእርሱ ሊናከስ የዱር እንስሳ ከሆነው እና በሌላ ቦታ ሰው ከሚበለው ጅብ ጋር ሳይቀር ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ ነበር ሲል ያወሳል። የተለያዩ ማንነቶች ሳይጣረሱ በፍቅር የኖሩባት የነበችው ሐረር ዛሬ ይህ ውበቷ ወደ ታሪክነት እንዳይቀየር ሥጋቱን በመግለፅ ወገን ወገኑን መዝረፍና ማጥቃት ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፤ አሁኑ መጠነኛ መረጋጋት ቢኖርም፣ የሕዝቡ ሥነ ልቦና አሁንም ሥጋት ያጠላበት መሆኑን ያስረዳል።
ሞሐመድ ለንግግሩ መነሻ የሆነው መጋቢት 2011 የሐረር ከተማ በብብቷ የያዘችውን ቆሻሻ የምታስወግድበት አጥታ በምጥ የተያዘችበት ኹነት መጀመሪያው ነው። በወቅቱም ሽታው ከተማዋን በክሎ፤ ቆሻሻውን ለማስወገድ የቆሻሻ ገንዳ ጭነው ለመጣል የሚሔዱ መኪኖች ከነሸክማቸው ይዘው ወደ ከተማዋ ሲመለሱ ድርጊቱ ከከተማ መስተዳድሩ በላይ እንደነበር የሚያስታውሰው ሞሐመድ ሐረር ቆሻሻዋን ታቅፋ ለአንድ ወር መቆየቷን ያወጋል።
የቆሻሻ መጣያ ሥፍራውን የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዳይጠቀም በመከልከሉና ካሳ በመጠየቁ ምክንያት፣ ለአንድ ወር ያህል በከተማዋ ቆሻሻ መጣያ ጠፍቶ ከተማዋ ሽታ እንደነበር የክልሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኀላፊ አብዱላኪም ዮኒስ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ከሐረር ከተማ 7 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ጄኒላ ወረዳ ልዩ ሥሙ ‘ላንድ ፊል’ በሚባል ሥፍራ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሰኔ 2000 ላይ ለ10 ዓመት የሚሆን ካሳ ተከፍሏቸው፣ 13 ካሬ ሜትር በሚሆን ቦታ ላይ ቆሻሻ እንዲጣል ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር የቢሮ ኀላፊው አብዱላኪም ይናገራሉ። ከ10 ዓመት በኋላ ግን በአካባቢው የሚጣለው ቆሻሻ እየሸተተ በመምጣቱና አካባቢውንም በመበከሉ ነዋሪዎቹ አዲስ የጉዳት ካሳ ጥያቄ ማንሳታቸውን ያወሳሉ።
እንደ አብዱላኪም ገለጻ፣ በአርሶ አደሮቹ ማሳ ላይ ቆሻሻ እንዲጣል ሲወሰን፣ ለማኅበረሰቡ ቃል የተገባው፣ ይመረታል የተባለው ማዳበሪያም ሆነ ሌላው ነገር ምርት ላይ ውሎ ባለመታየቱ፤ የአካባቢው ማኅበረሰብ “በቂ ካሳ አልተከፈለንም፣ የሐረርን ቆሻሻ አንሸከምም፣ የጉዳት ካሳም እንፈልጋለን” የሚሉ ጥያቄዎች ተፈጥረዋል ይላሉ።
ችግሩ እየከፋ በመምጣቱም በመጀመሪያው ዙር 16 ሚሊዮን ብር ሲከፈል፣ ከወራት በኋላ በኹለተኛ ዙር፣ ራቅ ብሎ የሚኖረው ገበሬ “እኔም ቆሻሻው ሸቶኛል ስለዚህ የጉዳት ካሳ እፈልጋለሁ” በማለቱ ተጨማሪ 20 ሚሊዮን ብር ካሳ ተከፍሎ ቆሻሻው እንዲደፋ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛው የካሳ ክፍያ መሆኑንም አብዱላኪም አክለው ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ሞሐመድ በአብዱላኪም ሐሳብ አይስማማም፤ አንድ ቡድን ባሻው ሰዓት ተነስቶ ብር ሲጠይቅ ገንዘብ የሚሰጠው ከሆነ፣ ሌሎች ተመሳሳይ ቡድኖችም ተነስተው እንዲያምጹ በር መክፈት ነው ይላል። ከዚህ ግርግር ጀርባ የባለ ሥልጣናት እጅ መኖሩን በማመላከት።
የባለሥልጣናት እጅ አለበት የሚለውን ወሬ ማስረጃ የሌለው አሉባልታ ነው የሚሉት አብዱላኪም፣ ይሄ ሁሉ መዘዝ ባለፉት 27 ዓመታት መሬት የመንግሥት ነው፤ ሕዝብ ምን አገባው በሚል የተወሰደው እርምጃ ያመጣው ጦስ እንደሆነ ይናገራሉ። ብዙ ነገሮች ይከናወኑ የነበሩት በሕዝቡ ፈቃድ ስላልነበረ፣ በዚህ አርሶ አደሩ ቂም ይዞ እንደነበርም ያወሳሉ።
እንደ አብዱላኪም ገለጻ፣ በአካባቢው እየተበራከተ የመጣው ሥራ አጥ ወጣት እንዲህ ዓይነት ክፍተቶችን እንደ አጋጣሚ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።
“በሐረሪ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች የተስተዋሉ ነገሮች ናቸው። ስለዚህ ችግሩን ለመፍታት ካሳ መክፈላችን አማራጭ የሌለው ነገር ነበር” ሲሉም አክለዋል።
ከለውጡ በኋላ በሐረሪ ክልል እየታየ ያለው እንቅስቃሴ ለብዙዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች ሥጋት መሆኑን የሚናገሩት የሶፊ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ለማ ተከተል፣ በርካታ መሬት መወረሩን፣ ሰዎች ከመኖሪያቸው እንዲወጡ መደረጉንና ቀማኛነት በከተማዋ መንሰራፋቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ፣ ቋሚ የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በሐኪም ጋራ በ20 ካሬ ሜትር ላይ በእርከን ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ወጣቶች፣ ማታ ተክለው የሔዱትን ችግኝ፣ በማግስቱ ጧት እንደማያገኙት ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የጄኒላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ገዛኸኝ በቀለ፣ በዚህ የተነሳ ከ80 በላይ የሆኑ ሠራተኞች ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸው እንደነበር ይናገራሉ።
ማንነታቸው በግልጽ የማይታወቁ ወጣቶቹ በፈለጋቸው ሰዓት እየተነሱ፣ በማን አለብኝነት ጥቃት እንደሚያደርሱ ያስታወቁት ገዛኸኝ፣ እነዚህ አካላት ከኅብረተሰቡ አይደለም ከክልሉም የጸጥታ ኀይል አቅም በላይ ናቸው ይላሉ።
አብዱላኪም ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት በሐረር ከተማ 650 ሔክታር መሬት ተዘርፏል ፤ ከ1000 በላይ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተገንብተዋል፤ ሃረማያ ዩኒቨርሲቲ ፍራፍሬ የሚያመርትበት ሴራት ፓርኪንግ ተዘርፏል፤ ቤተክርስቲያንና መስጂዶች ተደፍረዋል።
“የሚሰግድበትን መሲጂድ ደፍሮ ቤት የሠራ አለ፤ በርካታ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ተቀምተዋል፤ ገንዘብ ቆጥበው ኮንዶሚኒየም ቤት የሠሩ መምህራንና ሠራተኞች ለአንድ ዓመት ተኩል ከቤታቸው እንዲፈናቀሉ ተደርገው፣ በቤቱ ሌሎች ሰዎች ይኖሩበት ነበር። የክልሉ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከዓመት በኋላ ሕገወጦቹን በማስወጣት እንዲገቡ ተደርጓል” ሲሉም ያስረዳሉ።
የጸጥታ አካላቱም የወንጀሉ ተባባሪዎች እንደነበሩ የሚናገሩት አብዱላኪም፣ እነዚህ አካላት ሕዝቡን በዘር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ በመከፋፈል የጸጥታ ችግር በክልሉ እንዲፈጠር በማድረግ ትልቅ ቦታ ነበራቸው። በዚህም ሳቢያ በርካታ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ውለው ከተጣራ በኋላ ብዙዎቹ ከሥራ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። በወንጀሉ ቀጥተኛ ተሳታፊ የነበሩትም በሕግ እንዲጠየቁ ሆኗል።
የውሃ ችግር
ሐረሪ ውሃ የምታገኘው ከድሬዳዋ 75 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አዶሌ፣ አዎዳይንና ሃረማያን አቋርጦና አዳርሶ የተረፈውን ነው። ይሄንን የውሃ መስመር ሃረማያ ላይ በመዝጋት 10 ሚሊዮን ብር ወደ አካውንታችን ካላስገባችሁ በውሃ ጥም ታልቃላችሁ የሚሉ ኀይሎች መነሳታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያሳወቁት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የክልሉ ከፍተኛ አመራር፣ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር በተለያዩ ዘርፎች ላይ በተመሳሳይ ጥያቄ መቅረባቸው የወጣቱ ብቻ አድርጎ መመልከቱ ስህተት ነው ይላሉ፤ የሰላማዊውን ሕዝብ ያውም መሰረታዊ ነገሩን በመገደብ ከሚደራደር ሕገወጥ ኀይል ጋር መስማማት ሌላ ትርጉም የሚያሰጠው ነው በማለት።
እኚሁ ግለሰብ እንደሚሉት ከሆነ፣ የክልሉ መንግሥት ከቆሻሻ መጣያ ሥፍራው ጋር በተያያዘ፣ በሥፍራው ላሉ አርሶ አደሮች ካሳ መክፈሉ ብዙ ጥያቄ ባያስነሳም፣ ከአካባቢው ርቀው የሚገኙ ሰዎች “ሸቶናል” በሚል ላቀረቡት ጥያቄ ለመጀመሪያዎቹ ከሰጠው 16 ሚሊዮን ብር፣ 4 ሚሊዮን ብር ጨምሮ 20 ሚሊየን ብር የከፈለበት አግባብ ለከተማዋ ነዋሪ እንግዳ ነበር ብለዋል። ገንዘብ በቀላሉ የሚገኝ ከሆነ እኛስ በሚል ይመስላል ኤረር ላይ ከውሃ ጋር በተያያዘ ሌላ የካሳ ጥያቄ መጣ፤ ሲልም ስለቀጣዩ ክስተት ያወጋል።
የክልሉን የውሃ ችግር ለመቅረፍ ኤረር በሚባል አካባቢ አዲስ የውሃ ፕሮጀክት ተቋቁሞ፣ ተመርቆ ሥራውን በጀመረ በአምስተኛው ወር፣ በእርሻ ቦታቸው ላይ ጉድጓድ ተቆፍሮ ውሃ ሲወጣ ድርቀት አምጥቶብናል፣ እርሻችንን በመስኖ ውሃ ማጠጣት አልቻልንም፣ ካሳ አልተከፈለንም በሚሉ የአካባቢው ማኅበረሰብ ውሃው እንዲቋረጥ መደረጉንና፤ የመብራት መስመሩንም እንደበጣጠሱት የሚናገሩት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሐረሪ ከተማ ነዋሪዎች፣ የክልሉ መንግሥት ከእነዚህ ሕገወጥ ሰዎች ጋር ተደራድሮ 20 ሚሊዮን ብር መክፈሉን ይናገራሉ።
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አብዱላኪም በበኩላቸው፣ አርሶ አደሮቹ ለመስኖ የሚጠቀሙበት ውሃ እየደረቀ መምጣቱን በአካል ሔደው መመልከታቸውንና በአካባቢው ንጹሕ የመጠጥ ውሃና መብራት አለመኖሩን መታዘባቸውን ተናግረዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ “የውሃ፣ የመብራት ችግር አለብን፣ ፍቱልን” ብለው ቢጠይቁም ምላሽ የሚሰጣቸው የመንግሥት አካል አልነበረም ይላሉ። እነዚህ ሰዎች መብታቸውን ስለጠየቁ እንዴት ሕገ ወጥ ልንላቸው እንችላለን? ሲሉም ጠይቀዋል።
አብዱላኪም አክለው ውሃውን የዘጋው የአካባቢው አርሶ አደር ሳይሆን፣ ግርግሩን ተጠቅመው የሚንቀሳቀሱ አካላት መሆናቸውንም ይጠቅሳሉ።
ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በተደረገ ድርድር መሰረት፣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ በየሰፈራችን ይግባልን፣ መብራት ይግባልን በማለታቸው ለውሃ ፕሮጀክት 8 ሚሊዮን ብር ከፍለናል የሚሉት አብዱላኪም፤ 15 ሚሊዮን ብርም የካሳ ክፍያ እንደተፈጸመ ያስረዳሉ። በአጠቃላይ ለመልሶ ማልማት ብቻ 59 ሚሊዮን ብር ካሳ መከፈሉን በማውሳት።
ባለቤቱ ፈረንሳዊ የሆነ አንድ ሎጅ በመቃጠሉ ባለሀብቱ የ25 ሚሊዮን ብር ካሳ ጠይቋል፤ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት አብዱላኪም፣ ባለፉት ስድት ወራት በከተማዋ በነበረው አለመረጋጋተ ሳቢያ ክልሉ ዋጋ መክፈሉን ያወሳሉ።
የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በከተማዋ ዙሪያ የሚስተዋሉት ሥርዓት አልበኝነቶች ሥርዓት ሊበጅላቸው ይገባል። የከተማ አስተዳደሩም ከነውጠኞች ጋር ከመደራደር ይልቅ በሕግ እንዲመሩ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉ ሥጋታቸውን ያስረዳሉ።
የክልሉ መንግሥት ገንዘብ በተጠየቀ ቁጥር እያነሳ የሚሰጥ ከሆነ፣ ሥርዓተ አልበኝነትን ከማስፋቱም በተጨማሪ፣ ወጣቱ ሳይሠራ በአመጽ ገንዘብ ማግኘት እንደሚችል ያሳምነዋል የሚሉት የሶፊ ወረዳ ነዋሪ ለማ ከዚህም ባለፈ ክልሉን ለኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋታል ይላሉ።
አብዱላኪም ግን በዚህ አይስማሙም፣ አመጽን በኀይል ለማስቆም መሞከር ተገቢ አይደለም ባይ ናቸው፣ የችግሩን ምንጭ በማወቅ፣ ለዛ መፍትሔ ማበጀቱ የተሻለ እንደሆነ በማውሳት። አብዛኛውን የከተማዋ ነዋሪዎች ከድኅነት ወለል በታች መሆናቸውንና፣ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥሩም በእጅጉ መጨመሩን እናውቃለን፤ የሚሉት የቢሮ ኀላፊው፣ ስለዚህ ግርግር ሲፈጠር፣ ሥራ አጥ ወጣቱ አጋጣሚውን በመጠቀም ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ያመላክታሉ።
ስለዚህ መጀመሪያ መደረግ ያለበት ነገር ለወጣቱ የሥራ ዕድል መፍጠር መሆኑን ያስገነዝባሉ። ያንንም ለማድረግ በ2011 በጀት ዓመት 118 ሚሊዮን ብር በመመደብና ለወጣቱ ብድር በማዘጋጀት በማኅበር ተደራጅቶ እንዲሠራ መደረጉን ጠቁመዋል። አክለውም፣ በጀቱ ለአንድ ዓመት ብቻ የተመደበ ነው። በየዓመቱ ይህንን በማሻሻል ወጣቱ እራሱን በሥራ እንዲይዝ እያደረግነው ነው ብለዋል።
የባለቤትነት ስሜት ላይ የነበሩ ክፍተቶችን ማስተካከል ሌላው መሠራት ያለበት ሥራ መሆኑን ያመላከቱት አብዱላኪም፣ “ወጣቱ ላይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው መሥራት ባለመቻላችን የራሱን ንብረት ሲያቃጥል፣ ሲመዘብርና ወገኑን ሲያንገላታ ከርሟል፤ የአመጽ ውጤት ሆኖ የምናየውም ለዚህ ነው። በዚህ ላይ በስፋት ለመሥራት ዕቅድ ይዘን መንቀሳቀስ ጀምረናል” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011



