ከወርቅ እና እምነበረድ የተገኘው ገቢ በ90 በመቶ አሽቆለቆለ

0
985

የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ2011 የበጀት ዓመት 734 ኪሎግራም ወርቅ ወደ ውጪ መላኩን እና ዝቅተኛ የተባለውን ገቢ ማስገኘቱን አስታወቀ። በተለያዩ ኩባንያዎች ወደ ውጪ የተላከ 203.2 ኪሎግራም ወርቅ እና በባሕላዊ ማኅበራት ደግሞ 531.075 ኪሎግራም ወርቅ ተሰብስቦ መላኩን ጨምረው ገልፃል።

በኩባንያዎች አማካኝነት ከቀረበው ወርቅ እና 1 ሺሕ 811.53 ሜትር ኩብ ዕምነ በረድ ለውጪ ገበያ ቀርቦ ከኹለቱም ሽያጭ በአጠቃላይ 7 ነጥብ 179 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱንም ሪፖርቱ ያመላክታል። የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ2010 በጀት ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 75 ነጥብ 527 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በ 90.49 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱን የማዕድን ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሚካኤል መንገሻ አስታውቀዋል።

በባሕላዊ ማዕድን አምራቾች ከተገኘው ወርቅ በተጨማሪ 3 ሺሕ 165.985 ኪሎግራም ጥሬ እና 1 ሺሕ 8.703 ኪሎግራም እሴት የተጨመረበት ኦፓል፣ 6 ሺሕ 501.111 ቶን ከኦፓል ውጪ ያሉ የጌጣጌጥና ሌሎች ማዕድናት እንዲሁም 158.58 ቶን ታንታለም ለብሔራዊ ባንክና ለውጭ ገበያ ቀርቦ የነበረ ሲሆን በአጠቃላይ 36.863 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱንም ጨምረው ገልጸዋል።

የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ2010 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 54.883 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነጻጸር በ 32.8 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል።
በማዕድንና የነዳጅ ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር የውጪ ምንዛሬ ለመቀነሱ የተለያዩ ምክንያቶች አቅርቧል። ከእነዚህም መካከል የሚድሮክ ወርቅ አምራች ኩባንያ በአካባቢ ብክለት ችግር በጊዜያዊነት ሥራ እንዲያቆም መደረጉ እና የአካባቢና የጤና ብክለት ችግር በዓለም ዐቀፍ መስፈርት እንዲጠና ለማድረግ ረጅም ጊዜ ወስዷል ሲል ሪፖርቱ አስታውቋል።

በተጨማሪም ኢዛና ወርቅ ኩባንያ ኬሚካልና ሌሎች ግብዓቶች ከውጭ ለማስገባት ተገቢውን የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ ከብሔራዊ ባንክ ባለማግኘቱ፣ በሁሉም ወርቅ አምራች ክልሎች የኮንትሮባንድና ሕገ ወጥ ንግድ መስፋፋት፣ ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠት እንዲሁም በተለያዩ ድንበር አካባቢዎች ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ ሸቀጣ ሸቀጦችን መገበያያ (በጥቁር ገበያ ሒሳብ) ወርቅን መጠቀማቸው የሚጠበቀውን ያክል ወርቅ ማምረት አልተቻለም። በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር አምራቹ በተረጋጋ መንፈስ ማምረት አለመቻሉ ለገቢ መቀነሱ አስተዋጽዖ አድርጓል።

በ2004 ከአጠቃላይ የወጪ ንግድ ገቢ ውስጥ የማዕድን ዘርፉ በተለይም የወርቅ ማዕድን የ19 በመቶ ድርሻ ነበር። በመሆኑም በወቅቱ 654 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ከቡና ቀጥሎ በኹለተኛ ደረጃ የአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ነበር።

በ2010 የበጀት ዓመት በዓለም ዐቀፍ ገበያ የወርቅ ዋጋ መውረድ፣ በኢትዮጵያ በተከሰተው የጸጥታ አለመረጋጋት እና ሕገ ወጥ የማዕድናት ምርትና ግብይት በመበራከቱ ምክንያት የዘርፉ ለአገራዊ ምርት እና ለወጪ ንግድ በጣም ዝቅተኛ አስተዋጽዖ ነበረው።

በመንግስት በኩል ከተነሱ ችግሮች መካከልም ከፍተኛ ትኩረት የሚደረገው በወርቅ ብቻ ላይ በመሆኑና በሌሎች የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ አማራጭ ማዕድናት ላይ ትኩረት ባለመደረጉ ዘርፉ ለውጭ ምንዛሪ ምንጭ በመሆን የሚጫወተው ሚና አናሳ አድርጐታል ሲል ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here