ዐቃቤ ሕግ የአሃዱ ሬድዮን ክስ አቋረጠ

0
713

የበረክ ወረዳ ፍርድ ቤትን ሥም አጥፍተዋል በሚል እና በሌሎች ኹለት ክሶች ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት የአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኞች እና ሥራ አስኪያጅ ራሳቸውን ለመከላከል በቀረቡበት ቀጠሮ ሐምሌ 12/2011 ቀን ክስ መቋረጡን ፍርድ ቤት አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተከሰሱበት ክስ በድጋሜ መጣራት አለበት የሚል ትዕዛዝ በመስጠቱን ክስ መቋረጡን የአሃዱ ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የክልሉ ርዕስ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ የተከሰሱበት ጉዳይ አልፎም ታምራት አበራ ከስቱድዮ ታስሮ የተወሰደበት አካሔድ ተገቢ አይደለም በሚል ሥራ አስከያጁን ይቅርታ ጠይቀዋል።

ከዚህ ቀደም በአሃዱ ሬድዮ ሰንዳፋ አካባቢ የሚገኝ፣ ባለቤትነቱ የሌላ ግለሰብ የሆነ ንብረትን ሐሰተኛ መታወቂያ በማዘጋጀት እና ንብረቱ የእነሱ እንደሆነ በማስመሰል ንብረቱን ሕገወጥ በሆነ መልኩ ተወሰወዷል ሲል ዘገባ አቅርቧል። ሥሜ ጠፍቷል ያለው ፍርድ ቤትም ለግለሰቦቹ የሰጠው ፍርድ ተገቢ አይደለም በሚል በአሃዱ ሬዲዮ በመዘገቡ ምክንያት በክስ አቅራቢው የበረክ ወረዳ ፍርድ ቤት ክስ መመስረቱ ይታወቃል።

የበረክ ወረዳ ፍርድ ቤትን ሥም አጥፍተዋል ከሚለው ክስ ባሻገር ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ አድርገዋል እና ሚዛናዊ ያልሆነና አድሏዊ ዜና አቅርበዋል በሚል በሰኔ 4/2011 ክስ ከመመስረቱ ባሻገር ጋዜጠኛ ታምራት አበራን ከስቱዲዮ ተወስዶ ታስሮ እንደነበርም ይታወቃል።

በተጨማሪም የሬድዮ ጣቢያው ሥራ አስከያጅ ጥበቡ በለጠ ድርጅቱን ወክለው ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ተጨማሪ ኹለት ጋዜጠኞች ማለትም ሊዲያ አበበ እና ሱራፌል ዘላለም ክስ በተመሰረተበት ጉዳይ ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ናቸው።

የጋዜጠኞቹ ጠበቃ አበባው አበበ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ማለዳ “የፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅን መሠረት አድርገው ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ከሳሽ በረክ ወረዳ ፍርድ ቤት ሆኖ በዛው ፍርድ ቤት ጉዳያችን ሲታይ ከአድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ የሚካሔድ ፍርድ አይሆንም” ማለታቸው ይታወሳል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አሃዱ ሬዲዮ የሚገኘው በፌደራል ስለሆነ ጉዳያችን በፌደራል መታየት አለበት ብለው ሲከራከሩ እንደቆዩ ይታወቃል።

ሰኔ 27/2011 በበረክ ወረዳ የተገኙት ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ5 ሺሕ ብር ዋስ እንዲወጡ ወስኖ በአጠቃላይ 20 ሺሕ ብር ከፍለው መውጣታቸውን ይታወሳል።

ዓለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄ የኢትዮጵን የሚዲያ ሁኔታ በቃኘበት ሪፖርቱ በአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ላይ በተለይም በታምራት አበራ ላይ የተፈፀመውን እስር ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። ለመብት ተሟጋች ድርጅቱ ቃሉን የሰጠው እና ታምራትን ሊጠይቅ በሄደበት እሱም ታስሮ የነበረው ጌትዬ ያለው ያለምንም ማብራሪያ በነፃ የተለቀቀ ሲሆን ታምራት ግን በዋስ መፈታቱንም ተቅሶ ነበር።

ዓለማቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሲፒጄን ጨምሮ የተለያዩ ዓለማቀፍ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት በጋዜጠኞች እና በመገናኛ ብዙኀን ነጻነት ላይ እየተወሰዱ ያሉ አለአግባብ እርምጃዎች እንዳሳሰቧቸውም ተናግረው ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here