“ለምን ትለምን?”

0
750

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“ሲያሳዝኑ!…ሴቶቹስ ቢለምኑም ችግር የለም። ወንዶቹ ሲለምኑ ስመለከት በጣም ነው የደበረኝ…ቢሠሩ አይሻልም!?” አለ። የአውቶብሱ የወንበሩ አቀማመጥ ትይዩ ነበርና የተናገረውን ሰው በትኩረት አየሁት፤ አጠገቡ ከተቀመጠች ሴት ጋር እየተነጋገሩ ነው። ለምን እንደሆነ ዘግይቶ የገባኝ ቢሆንም በአነጋገሩ ግን ተናደድኩ።

በእርግጥ ንግግሩ ከሐዘኔታ የመነጨ እንደሆነ ያስታውቃል። ደግሞ የተነገረላቸው በልመና ላይ ያሉ ሰዎች በአገራቸው ሰላም ማጣትና መፍረስ ምክንያት የተበታተኑት የሶርያ ሰዎች ናቸው። እነዚህን ሰዎች በጾታ ከፋፍለን እንሟገት ካልን ነገሩ “የደላው ሙቅ ያኝካል” ይሆንብናል። ነገር ግን ተናጋሪው አስተያየቱን የሰጠው በለመደ ዓይኑ ታዝቦ ነው። ዓይኑ ምን ለምዷል? ምን ወጣት ብትሆንና ሠርታ ለመብላት አቅም እንዳላት ብታስታውቅም፤ ሴት ስትለምን ምንም ችግር የለም፤ ‘ደንብ’ ነው።

የሁላችን ዓይን የዚህን ሰው ዓይን ይመስላል፤ በልመና ላይ የተሰማሩ ሴቶችና እናቶችን ለምዷል። ከልመና የሚገኘውን ገቢ ከመገመት ባፈ ባናውቅም የሰው ፊት ማየትና ከክብር ዝቅ ማለት የሚባል ነገር እንዳለበት ግን በሚገባ እንረዳለን። ታድያ ሐዘኔታ የሚመስለን አኳኋናችን ሳናውቀው ድርሻ አከፋፍሏል፤ ለሴቷ ዝቅ ማለትን ትክክል ሲያደርግ ወንዱን “ወንድ አይደለህ? ሠርተህ አትበላም?” ሲል ይገስጻል። ለምን? ሴትም ብትሆን ሠርታ ትበላ እንጂ ለምን ትለምን?

በእርግጥ በልመና ላይ በስፋት የተሰማሩት ወንዶች ይሁኑ ሴቶች ለማወቅ ዳሰሳ ሳያስፈልግ አይቀርም። ነገሩማ ድኅነት ባይኖርብን ኖሮ ልመናም በቀነሰ ነበር። ብቻ ግን በብዛት ሴቶችን ያውም ብቻቸውን ያመጧቸው ይመስል በርከት ያሉ ሕፃናትን ይዘው ነው የምናየው። በአንጻሩ በልመና ላይ ያሉ ወንዶች በዕድሜ የገፉ አልያም የአካል ጉዳታቸውን በምክንያትነት የሚያቀርቡ ናቸው።

ከልጆቻቸው ጋር የሚታዩት ሴቶች በርካታ ናቸው። ልጅ አቅፈውና መለመኛ ጨርቅ አንጥፈው እንቅልፍ የሚያዳፋቸው፤ በልጆቻቸው ጨዋታና ፈገግታ የአላፊ አግዳሚውን ቀልብ ስበው ፍራንክ ለማግኘት የሚማጸኑ፤ ጨቅላ ሕፃናትን አስተኝተው “የማርያም አራስ ናት! አትለፏት” የሚሉትን በእግር መንገዳችን እናያለን።

“በችግራቸው ላይ ለምን ልጅ ይወልዳሉ?” የሚለው ፈራጅ ብዙ ነው፤ አንድም ምክንያት የሆነው ወንድ ግን እንደደመና በንኖ የጠፋ ያህል ሥሙን የሚያነሳ የለም።

እኔ በበኩሌ ልጆች ይዛ ስትለምን በማያት በእያንዳንዷ ሴት ውስጥ ራሱን አብልጦ የሚወድና ለስሜቱ ያደረ ወንድ፤ ሥራውን ተደራሽ ያላደረገ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የሴቶቹም ዝንጋኤና በልመና ተስፋ ማድረግ ይታየኛል። ስለእርሷ ብቻ አይምሰላችሁ፤ የልጆቿ ትንንሽ የእጅ መዳፎች ያለጊዜያቸው ሳንቲም ሊጨብጡ ሲዘረጉ ማየት ትክክል ስላልሆነም ነው።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here