- የዞኑን አስተዳደር ጨምሮ አምስት ሰዎች የደኢሕዴን ስብሰባ አቋርጠው ወጥተዋል
የወላይታ ዞን ምክር ቤት ክልል ለመሆን ያሳለፈውን ውሳኔ ደኢሕዴን በደቡብ ክልል ምክር ቤት ጣልቃ በመግባት ጥያቄውን አዘግይቷል ሲሉ የዞኑ አመራሮች ገለጹ። ታኅሣሥ 10/2011 የወላይታ ዞን ምክር ቤት ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄውን ቢያቀርብም፣ ደኢሕዴን ሕጉ በማይፈቅድለት መልኩ ጥናት እያደረኩ ነው በሚል ጥያቄውን ከምክር ቤቱ መቀበሉንም ታውቋል።
የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ(ወብን) የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ተከተል ላቤና፣ ዞኑ እስካሁን ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አለመቻሉን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀው ጥያቄውንም ለማስተጓጎል የክልሉ ምክር ቤትም ለሰባት ወራት ያህል ስብሰባ አለማድረጉንም አክለው ገልጸዋል።
በደኢሕዴን 10ረኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከተሳተፉት ስድስት የዞኑ አመራሮች ውስጥ የዞኑን አስተዳደር ጨምሮ 5ቱ ስብሰባውን ረግጠው መውጣታቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታውቀዋል።
የደኢሕዴን ውሳኔ ኢዴሞክራሲያዊ ነው የሚሉት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ዞን ከፍተኛ አመራር፣ ንቅናቄው ሰኞ ባወጣው መግለጫ የሲዳማ ብሔር ጥያቄ በአስቸኳይ ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቦ፣ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያደራጅና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስተላልፍ ሲጠይቅ፣ የወላይታን ጥያቄ ግን ችላ ብሏል ሲሉ ይወቅሳሉ።
ደኢሕዴን ባስጠናው ጥናት መሰረት ምላሽ ሰጠሁ ማለቱን የሚናገሩት ተከተል፣ መግለጫው በክልሉ የሚገኙ ዞኖች የአወቃቀር ለውጥ እንዲደረግ መጠየቃቸውን ቢጠቅስም፣ ሕዝበ ውሳኔ ይካሔድባቸዋል የተባሉትን ግን በግልፅ አላሳወቀም ብለዋል።
መንግሥት ለጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ፣ የወላይታ ዞን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ጠብቆ ውሳኔውን በራሱ ለማስፈፀም እንዲዘጋጅ ወብን ጠይቋል። የወላይታ ዞን ምክር ቤት ታኅሣሥ 10/2011 ለደቡብ ክልል ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ፣ የዞኑ ምክር ቤት ወላይታ ራሱን የቻለ ክልል እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፎ ሕዝበ ውሳኔ እንዲዘጋጅ መጠየቁ ይታወሳል።
ተከተል እንደሚሉት፣ የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንዱ ብሔር ጥያቄ በሕገ መንግስቱ መሰረት ሕዝበ ውሳኔ ይደረግ ሲል፤ ከወላይታ ለቀረበው ጥያቄ ዳተኝነት ማሳየቱና በደቡብ ክልል ይቀጥል በማለት መወሰኑ ተቀባይነት የለውም።
በጉዳዩ ላይ ሰባት ወራት የፈጀ ጥናት ማካሔዱን የገለጸው ደኢሕዴን “የክልሉ ሕዝቦች አብሮ የመቀጠል ፍላጎት” እንዳላቸው ጥናቱ ድምዳሜ ላይ መድረሱን በማዕከላዊ ኮሚቴው በኩል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ወብን ግን የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሕግ አግባብ ውጭ የወሰነው ውሳኔ በክልሉ ምክር ቤት እና በፌዴራል መንግሥት ተቀባይነት እንዳይኖረው እና ውድቅ እንዲደረግ በመወትወት ላይ እንደሚገኝ ተከተል ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
ሰኞ፣ ሐምሌ 8 የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ በሚቀጥሉት አምስት ወራት ውስጥ የሲዳማን ሕዝበ
ውሳኔ ለማካሔድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ሲዳማ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ከምባታ እና ሐዲያን ጨምሮ በርከት ያሉ ዞኖች የየራሳቸው ክልላዊ መንግሥት ለማዋቀር ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011



