በሰሜን ሸዋ ዞን የተከሰተው የሽምብራ በሽታ ምርቱን አዳክሞታል

0
493

በተያዘው የመኸር ወቅት በሰሜን ሸዋ ዞን በሚገኙ ሽምብራ አብቃይ አካባቢዎች በዞኑ በተከሰተው “ሥር አበስብስ” በተባለው የሽምብራ በሽታ ሳቢያ ምርቱ በተጠበቀው መንገድ እንዳይከናወን እንቅፋት መሆኑን የዞኑ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አበበ ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ሽምብራ ለመዝራት ከታቀደው 16 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ 5 ሺሕ 180 ሔክታሩ የሚሆነው መሬት በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚገኝ ነው። በኩታ ገጠም ሽምብራ ለመዝራት ከታቀዱ ሦስት ወረዳዎች ምንጃር ሸንኮራ አንዱ ቢሆንም የሽምብራ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ እንዳይዘራ ተወስኗል።

“ሥር አበስብስ” የተባለው በሽታ ሰብሉ ከበቀለ በኋላ ሥሩን በማበስበስ፣ የሽምብራ ምርትን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ የሚያደርግ መሆኑን ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ጽሕፈት ቤቱ የበሽታውን አሳሳቢነት ለደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር፣ ለደብረ ዘይት እርሻ ምርምር፣ ለኮምቦልቻ ዕፅዋት ኳራንታይን እና ለክልሉ ግብርና ቢሮ ማስታወቁን አበበ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ተቋማቱ አርሶ አደሮች የሽምብራ ሰብልን ደረቃማ ቦታ እንዲዘሩ፣ እርጥበታማ ቦታዎችን እንዲያጠነፍፉ እና ዘግይተው እንዲዘሩ ምክረ ሐሳብ ከማቅረብ ባለፈ ሳይንሳዊ መፍትሔ እንዳላገኙለት ያስታወቁት አበበ፣ የምንጃር ሸንኮራ አርሶ አደሮች ከተቋማቱ የተሰጡትን ምክረ ሐሳብ ተግባራዊ ቢያደርጉም በሽታውን ግን ማስቀረት እንዳልቻሉ ይናገራሉ።

አበበ እንደገለጹት፣ በሽታው በውሃና በነፋስ ከቦታ ወደ ቦታ የሚዛመት በመሆኑ በዘንድሮው የመኸር ወቅት በኩታ-ገጠም ለመዝራት ከታቀዱት ዋና ዋና ሰብሎች መካከል ሽምብራ አልተካተተም። ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እንደ ምሳሌ ይጠቀስ እንጂ በዞኑ ሽምብራ አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች በሽታው መከሰቱን ከዞኑ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

አበበ “እፊት” የተባለውን ነፍሳት ጨምሮ ከሰብሉ ጋር ንክኪ ያላቸውን ተባዮች መቆጣጠር ከተቻለ፣ በሽታው እንዳይዛመት ማድረግ እንደሚቻል ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ እንደደረሰበት አስታውቀዋል። ይህንን ዘዴ ለአርሶ አደሮች እና ለግብርና ባለሙያዎች መረጃ እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። የምርምር ማዕከሉም ቀጣይ ይህንን ተህዋሲያን የሚቆጣጠር መድኀኒት እና በሽታውን ሊቋቋም የሚችል ዝርያ ለመለየት እንደሚሠራ ነው ያስታወቁት።

ከሦስት ዓመት ወዲህ በሰብሉ ላይ በሽታ መከሰቱን ተከትሎ ምርታማነቱም ሆነ የሽፋን መጠኑ በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን የወረዳው ግብርና ቢሮ ያስታወቀ ሲሆን፣ የወረዳው አርሶ አደሮችም ሽምብራ መዝራት በማቆማቸው ከምርቱ ያገኙት የነበረውን ጥቅም ማጣታቸውን ገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 37 ሐምሌ 13 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here