- የሟቾች ሁኔታ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ ይገለፅ ሲሉም ጠይቀዋል
ኢሕአዴግ ኢ-ሕገ መንግሥታዊነቱ አለቀቀውም ሲሉ ሰባት የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ። የሰኔ 15/2011 የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ግድያን ተከትሎ እየተፈፀሙ ያሉ የጅምላ እስራት፣ ማሳደድና ማሥፈራራት በአስቸኳይ እንዲቆሙ ሲሉ ፓርቲዎቹ ሐሙስ፣ ሐምሌ 18 በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ እየተስተዋሉ ያሉ የሰብኣዊ እና የዲሞክራሲያዊ መብት ረጋጮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያቆጠቆጡ መምጣታቸው፣ ኢሕአዴግ ትላንት ይዞት የነበረው ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ አካሔድ ያለቀቀው መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
መግለጫውን በጋራ የሰጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴኅ)፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ፓርቲ (ኦነንፓ)፣ የአፋር ሕዝብ ነፃነት ፓርቲ (አሕነፓ) እና የአፋር ሕዝብ ፍትሐዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አሕፍዴፓ) ናቸው።
በመላ አገሪቱ እየታሰሩ ያሉት የፓርቲ አመራሮችና አባላት ሰበብ እየተፈለገ የተወሰደው የስህተት እርምጃ ከዚህ ቀደም የአሸባሪነት ታርጋ በመለጠፍ ከተወሰደው ጋር ተመሳሳይነት ያለው ነው ያሉት ፓርቲዎቹ፣ ይህ ድርጊት ቆሞ ንፁሓን ዜጎች ከእሥራት ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል። በአማራ ክልል ውስጥ ታስረው የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ንፁሓን ዜጎችም ጉዳያቸው ተጣርቶ ከእሥራታቸው እንዲለቀቁም ጠይቀዋል። የሟቾች ሁኔታ በገለልተኛ ወገን ተጣርቶ በማያሻማ መልኩ ለሕዝብ ሊገለፅ ይገባዋልም ሲሉ በመግለቸው ላይ ጠይቀዋል።
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት የሚያደርጋቸውን ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች በተገቢው መንገድ እንዲስተናገዱ ፓርቲዎቹ የጠየቁ ሲሆን፣ በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ የሚደረገው ማዋከብ መቆም እንዳለበትም አስታውቀዋል።
መግለጫው እንደሚያትተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ሳናጣራ አናስርም፤ አስረንም ማስረጃ አንፈልግም” ባሉት መሰረት፣ ማንም የተለየ ሐሳብ ይዞ በመምጣቱ ሊታሰርም ሆነ ሌላ ጫና ሊደርስበት አይገባም። በዚህም መሰረት የዜጎችን የሐሳብ ነፃነትን እንዲያከብር መንግሥትን እንጠይቃለን ብለዋል።
በትግራይና በአማራ ክልል የሚደረጉ የተንኳሽነት እሰጥ አገባ ንትርክ በአስቸኳይ ቆሞ፤ የኹለቱን ሕዝብ ታሪካዊ ግንኙነት መሰረት ባደረገ መንገድ የሚነሱ ጉዳዮችን መፍትሔ መስጠት ይኖርባቸዋል ብለን በጽኑ እናምናለንም ብለዋል ፓርቲዎቹ። በመሆኑም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እየጠየቅን፣ ጉዳያቸው በፓርቲዎች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲታይ እንጠይቃለን ሲሉም አሳስበዋል። አሁን እየተወሰዱ ያሉት ዘርን መሰረት ያደረጉ እስራቶች፣ ጅምላ ፍርጃዎች በአስቸኳይ ቆመው ሕግን መሰረት ያደረገ አሰራር እንዲዘረጋ ፓርቲዎቹ ጠይቀዋል።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011


