በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መካከለኛው እና ታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ላይ የተገነቡት የከሰምና ተንዳሆ የመስኖ ግድብ ከታሰበላቸው የግንባታ ወጪ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ቢያስወጡም ለተደጋጋሚ ብልሽት እየተዳረጉ መሆኑ ተጠቆመ።
እነዚህ ግድቦች ተሰርተው እስከሚጠናቀቁ ተይዞላቸው የነበረው የግንባታ ወጪ 5 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ዕድገት በማሳየት የ11 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ መድረሱ ታውቋል።
የመስኖ ግድቦች ተሰርተው ለመጠናቀቅ ከታሰበላቸው ወጪ የ6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወይም 120 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የፌደራል ዋና ኦዲተር የ2010 በጀት ዓመትን የሒሳብ አያያዝ መግለጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ለመረዳት ተችሏል። የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በመጀመሪያ ለከሰምና ለተንዳሆ መስኖ ግድቦች ግንባታ የተመደበው ገንዘብ ክለሳ ተደርጎበት ከ120 በመቶ በላይ ጭማሪ ማሳየቱንና ይህም አላስፈላጊ የገንዘብ ብክነት እንደታየበት ተገልጿል።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ብዙነህ ቶልቻ ለአዲስ ማለዳ ሲያብራሩ፤ ግንባታውን በተያዘለት የጊዜ ገደብና ወጪ አጠናቀው ለሚያስተዳድረው አካል እንዳስረከቡ እና በዋና ኦዲተር በኩል ተገኘ ስለተባለው የ120 በመቶ ጭማሪ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ምላሸቸውን ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ ሥማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ የስኳር ኮርፖሬሽን ባልደረባ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት ኹለቱም ግድቦች የተጠናቀቁት ከዓመታት በፊት ቢሆንም አሁንም ድረስ በየጊዜው ከሚያጋጥማቸው የቴክኒክ ችግር በመነሳት በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነና በዓመት ውስጥ ከበርካታ ጊዜያት በላይ የጥገና ወጪዎች እንደሚያስወጡ ጨምረው ገልፀዋል።
በአፋር ክልል አዋሽ ሰባት ኪሎ የሚገኘው ከሰም እና በቀድሞዋ የክልሉ ርዕሰ መዲና አሳኢታ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘው ተንዳሆ የመስኖ ግድብ በዋናነት በአካባቢው ያለውን ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክት ይደግፋል በሚል የተገነቡ እንደሆኑ የሚታወስ ነው። ግድቦቹ በአጠቃላይ ከ90 ሽሕ ሔክታር በላይ በቀጥታ ያለማሉ ተብለው የታሰቡ ሲሆኑ በተጓዳኝም የአካባቢው ነዋሪዎች ከመስኖው የመጠቀም ዕድላቸው ሰፊ ስለሚሆን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ይኖራቸዋል የሚል ሐሳብ በመንግሥት በኩል እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
ይጠናቀቃሉ ተብለው ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ኹለት ዓመታትን ዘግይተው በ2007 በጀት ዓመት የተጠናቀቁት የከሰም እና ተንዳሆ መስኖ ግድቦች የሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች የመዘግየቱ ዓይነተኛ ምክንያቶች እንደሆኑ በወቅቱ የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አለማየሁ ተገኑ ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011



