ችግኞችን መንከባከብ፥ ዛፎችን በዘላቂነት መጠቀም ያስፈልጋል

0
1981

የፊታችን ሰኞ፣ ሐምሌ 22 በመንግሥት ዋና አነሳሽነት በመላው ኢትዮጵያ ለማካሔድ የታቀደው በአንድ ጀንበር 200 ሚለዮን ችግኞችን በመትከል በዓለም ድንቅ መዝገብ መሥፈርም ሆነ በአጠቃለይ በያዝነው ክረምት ለመትከል የታሰበው 4 ቢሊዮን ችግኝ በጎ እርምጃ ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ካጋጠማት የፖለቲካ ምስቅልቅል ብቸኛውና ሁሉንም ዜጎች አስማሚ አገራዊ ጉዳይ ነው ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ዓለማችን ሆነ አገራችን በየጊዜው በአየር ንብረት መዛባት በድርቅ፣ በጎርፍ፣ በአውሎ ነፍስ፣ በሰደድ እሳት፣ በከፍተኛ ሙቀትና ቅዝቃዜ መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ሲጠቁ ኖረዋል። የእነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ሰበብ ደግሞ በሰው ልጆች ጣልቃ ገብነት የሚፈጠረው የተፈጥሮ ሀብት መራቆት ነው፤ የተፈጥሮ ሀብት መራቆቱ ደግሞ በዋናነት ከደን መጨፍጨፍ ጋር ይያያዛል።

እንደሚታወቀው የተፈጥሮ አደጋዎች የሰው ልጆችን ሕይወትን ብቻ ሳይሆን በምድራችን ላይ የሚኖሩ ፍጥረታትን አደጋ ላይ ጥሏል፤ ለአንዳንዶቹም ከምድረ ገጽ መጥፋት ምክንያት ሆኗል። ደኖች በካይ ጋዞችን በማጥራት ከሰዎች በተጨማሪ በምድር ላይ ለሚገኙ ፍጥረታት ንፁሕ አየር በመለገስ እስትንፋስ ሆነው ከማገልገላቸውም ባሻገር ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚሰጡ በመዘርዘር አዲስ ማለዳ ተደራሲዎቻችንን ማሰልቸት አትፈልግም።

ወደ ችግኝ ተከላው ዘመቻ ስንመለስ፥ ኢትዮጵያውያን ለዓመታት በክረምት ወቅት በሚሊዮኖች የዛፍ ችግኞች መትከል የተለመደ ባሕል አለን ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይሁንና ችግኞችን ለማዘጋጀትና ለመትከል ከሚወጣው ሀብት፣ ጉልበትና ጊዜ አንጻር የተተከሉትን ችግኞችን በመንከባከብ እንዲጸድቁ ብሎም እንዲያድጉ በማድረግ የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ሲሆኑ እምብዛም አይታዩም። ለምሳሌ ኢትዮጵያን ከአየር ንብረት መዛባት መታደግ አልተቻለም። ይህ በመሆኑም በየዐሥር ዓመት ልዩነት የምናስተናገደውን ድርቅ፤ እሱንም ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ለረሀብ ሲያጋልጥ ነበር፤ ጉዳቱ አሁንም አልቆመም።

አዲስ ማለዳ ከአካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ባገኘችው መረጃ መሰረት ባለፉት ዓመታት በክረምት ወቅት በተካሔዱ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ኅብረተሰቡ በርካታ ችግኞች ቢተክልም የመጽደቅ ዕድላቸው ግን በአማካኝ 70 በመቶ ብቻ እንደነበር ታውቋል። ይህም የሆነበት ምክንያት በዋናነት በዘመቻ ከመትከል በዘለለ እንክብካቤና ክትትል ስለማይደረግ መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል። የዚህ ዓመትን የችግኝ ተከላ ዘመቻ ለየት የሚያደርገው ካለፈው ልምድ ተወስዶ ችግኝ መትከልን ብቻ ማዕከል ያደረገ ሳይሆን መንከባከብንም ትኩረት ያደረገ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ነው።

በግለሰቦችም ይሁን በኅብረት የተተከሉ ችግኞች ከሚመለከተው የመንግሥት አካላት ጋር በሚገባ የፈቃደኝነት ውል መሰረት ችግኝ የተከሉ አካላት እንክብካቤና ክትትል እንዲያደርጉ እንዲሁም በተወሰነ መልኩ ለንግድ ለመጠቀም በታሰቡ ጥሩ እርምጃ ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታደንቃለች፤ ይሁንና በቂ ነው ብላ ግን አታምንም።

ይህ የዘመቻ ችግኝ ተከላን ተከትሎ የሚደረገው እንክብካቤና ክትትል የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶለትና ተቋማዊ እንዲሆን በማድረግ አገሪቱ ከዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን አያሌ በረከቶች አሟጥጣ መጠቀም ይገባታል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ትሰጣለች። ‘ነገርን በምሳሌ . . .’ እንዲሉ አባቶቻችን አዲስ አበባ የመንገዷን ጽዳትና በመንገድ ዳርና በየአደባባዩ ላይ የሚገኙ መናፈሻዎች እንክብካቤ ነዋሪዎቿ በሚጠቀሙት የውሃ ፍጆታ ልክ በሚከፍሉት ገንዘብ በመሆኑ ለበርካቶች የሥራ ዕድልን በመፍጠር በንጽጽር ጽዱና የአረንጓዴ ከተማ ለመሆን በዘላቂነት እንድትሠራ አስችሏታል።

በተመሳሳይ ይህንን በጎ ተመክሮም በመውሰድ ከችግኝ ተከላ ዘመቻ እንዲሁም እንክብካቤና ክትትል ጋር ማያያዝ ዘላቂነት ያለውን ጥቅም ማግኛ ማድረግ ይቻላል ስትል አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

መንግሥት በዋናነት በየዓመቱ በክረምት ወቅት የሚካሔደውን አገር ዐቀፍ የችግኝ ተከላ ዘመቻን በቋሚነት የሚያስተባብር እንዲሁም ከተከላው በኋላ የሚደረገውን እንክብካቤ፣ ክትትልና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ዘላቂ እንዲሆን የሚያደርግ ተልዕኮ ያነገበ ተቋም ማቋቋም ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ ጥሪዋን ታቀርባለች። የተቋሙ የገንዘብ ምንጭ በሕግ በተደነገገና ቋሚ በሆነ አትራፊ ከሆኑ የመንግሥት ድርጅቶችና የግል ኩባንዎች ትርፍ በመቶኛ ተሰልቶ የሚከፈል እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። የሚሰበሰበው ገንዘብ ድርጅቶቹን ጫና ውስጥ ሳይከት ነገር ግን በቋሚነት እንዲያግዝ ለማስቻል ማኅበራዊ ኀላፊነትን ለመወጣት ከሚበጅቱት በጀት ጋር ማስተሳሰር አንዱ አማራጭ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይህንን በማድረግ አገሪቱን ቀስፎ ከያዛት የወጣት ሥራ አጥነት በሺዎች ሊሠማሩበት የሚችሉ የሥራ ዕድል የመፍጠር እምቅ አቅም አለው። ወጣቶቹ አንድም በቀጥታ ችግኞቹን በመንከባከብና ክትትል ላይ በማሰማራት የተተከሉት ዛፎች በአብዛኛው የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ ማስቻል ይቻላል። በሌላ በኩል ደግሞ ከደን ልማትና ሌሎች ተያያዥ ከሆኑ ዘርፎች ጋር በማያያዝ በልማት ላይ እንዲሳተፉ በማድረግ ሥራ ፈጥረው ራሳቸውን፣ ኅብረተሰቡን ብሎም አገርን የሚጠቅሙበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይቻላል።

በሦስተኛ ደረጃም ለተለያዩ የንግድ ተቋማት ደኖችን በማስተላለፍ ዛፎቹ በማይጎዳበት መልኩ ለንግድ እንዲውሉ በማድረግ የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩና አገራዊ ምጣኔ ሀብቱን እንዲያግዙ ማድረግ አንድ አማራጭ ነው። በመጨረሻም ወጣቶችን በጥቃቅንና አነስተኛ በማደራጀት ሥልጠና ልዩ ድጋፍ በማድረግ በደን ልማትና ተያያዥ ሥራዎች እንዲሰማሩ ማድረግም ይቻላል፤ ስትል አዲስ ማለዳ ምክረ ሐሳቧን ታቀርባለች። በርግጥ ምክረ ሐሳቦቹ የበለጠ እንዲዳብሩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችን ማሳተፍ ይገባል።

ችግኞችን በዘመቻ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ብሎም በዘላቂነት ጥቅም ላይ ማዋል ያስፈልጋል በማለት አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ትደመድማለች።

አዲስ ማለዳ ሐምሌ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here