በምዕራብ ጉጂ ዞን በሚገኙ አራት ወረዳዎች 24 ሴቶች ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች መደፈራቸውን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል። ተጎጂዎቹ የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑም ተገልጿል።
ብሔርን መሰረት ባደረገ ጥቃት በርካታ ሰዎች ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ በወቅቱ መሳሪያ ያነገቡ የጸጥታ አካላትና ቡድኖች በበርካታ ሴቶች ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ ጉዳዮች (‘ኦቻ’) ጋር በጋራ በሰጠው የጋራ መግለጫ ላይ አትቷል። ከተፈናቃዮቹ ውስጥ 3 ሺሕ 166 ለሚሆኑት የጤናና ማኅበራዊ ድጋፍ እንደተደረገላቸውም አስታውቀዋል።
የሰብኣዊ መብት ኮሚሽን (ሰመጉ) በበኩሉ፣ ከሳምንት በፊት ባወጣው የ2010 እና 2011 ዓመታዊ ሪፖርቱ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ አህጉራዊና ዓለም ዐቀፋዊ ድንጋጌዎችን በመተላለፍ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥቶች ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች በተፈፀሙት ጥቃቶች እና ግጭቶች በሴቶች ላይ የአስገድዶ መድፈር ድርጊት ተፈጽሟል ብሏል። ጥቃት ከተፈጸመባቸው ሴቶች መካከል ጥቂቶቹ ለኮሚሽኑ ያመለከቱ ሲሆን፣ ሰመጉም አመልካቾቹ አስገድዶ መደፈር እንደተፈፀመባቸው የሚያረጋግጡ የሕክምና ማስረጃዎች ለማግኘት መቻሉን በሪፖርቱ ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተበዳዮች በወቅቱ ሕክምና አለማግኘታቸውን የሚያትተው ሪፖርቱ፣ መንግሥትም ሆነ ጉዳዩ የሚያሳስበው ማንኛውም አካል የአመልካቾችን አቤቱታ መሠረት በማድረግ ተገቢውን ማጣራት እንዲያደርግ፤ እንዲሁም በአጥፊዎቹ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ሰመጉ አሳስቧል።
ከተጠቂዎቹ መካከል፣ የጂጂጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነች የ17 ዓመት ወጣት፣ የ26 ዓመት ዕድሜ ያላት የሆቴል ባለቤትና ለ17 ዓመት በጂጂጋ በንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው ይሠሩ የነበሩ የኹለት ልጆች እናት የሆኑ የ40 ዓመት እናት ይገኙበታል። እያንዳንዳቸው ከ3 እስከ ስምንት በሚሆኑ የልዩ ኀይል አባላት በተደጋጋሚ መደፈራቸውን ሪፖርቱ አስነብቧል።
እንደ ሰመጉ መግለጫ፣ አስገድዶ መድፈር በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ መሰረት ማንም ሰው የኀይል ድርጊት በመጠቀም፤ ወይም በብርቱ ዛቻ ወይም አንድ ሴት ሕሊናዋን እንድትስት ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ መከላከል እንዳትችል በማድረግ ከጋብቻ ውጪ አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸም በሕግ እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያ ፈርማ የተቀበለችው “በሴቶች ላይ የሚፈጸም ማንኛዉንም ዓይነት ጥቃት ለማስወገድ የተደረገ ስምምነት” በግልጽ እንዳስቀመጠው በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጥቃት ማለት ጾታን መሰረት ያደረገና አካላዊ፣ ወሲባዊ ወይም ሥነ ልቦናዊ ጉዳት በሴቶች ላይ ሊያደርስ የሚችል ማንኛውም ድርጊት፣ ማስገደድ ወይም ተገቢ ያልሆነ ነጻነትን የማሳጣት ተግባር የሚያጠቃልል መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ ይህም በሴቶች የግል ሕይወትም ሆነ በማኅበራዊ ኑሮ ላይ ሊደርስ የሚችል እንደሆነ ያስቀምጣል። አገራችን ኢትዮጵያ የዚህ ስምምነት ፈራሚ እንደመሆኗ እነዚህን ሰብኣዊ መብቶች የማክበር፣ የማስከበርና የማሟላት ግዴታ ተጥሎባታል።
ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011


