ሕግ የመጣስ ባሕል ወደ አምባገነንነት እንዳይወስድ ይታሰብበት

0
699

አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፤ ሐምሌ 20 ባወጣችው 38ኛ ዕትሟ “የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕጋዊነት እስከ መቼ?” በሚል ርዕስ ሥር በሐተታ ዘ ማለዳ ዓምዷ፤ በአንድ ወገን በምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የሚመራው የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ ምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመኑ ሰኔ 30/2011 ላይ አጠናቋል በሚል፤ በሌላ ወገን እስከ መጪው ምርጫ ስለሚል የከተማው አስተዳደርም ሆነ ምክር ቤቱ ቀጣይ ምርጫ እስኪካሔድ ድረስ መቀጠል ይችላል በሚል፤ በኹለቱ አቋሞች ዙሪያ ማከራከሯ ይታወሳል።

የከተማው አስተዳደር ሕጋዊነት ላይ እንደ መፍትሔ መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎችም የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን ከሕግና ሕገ መንግሥት ባለሙያዎች ፈንጥቃ እንደነበርም ተደራሲዎቻችን ያስታውሱታል ብላ ታምናለች። ይህ ጉዳይ ሌላኛዋን የፌዴራል ከተማ ድሬ ዳዋ አስተዳደርንም እንደሚመለከት ግልጽ ነው።

የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች አስተዳደር ምክር ቤቶችን እንዲሁም፣ የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ረቡዕ፤ ሐምሌ 24 የቀረበለትን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔ አስተላልፏል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው አስተዳደር መንበረ ሥልጣኑን ከተረከበ ከመጋቢት 24/2010 ጀምሮ የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ መድብለ ፓርቲ ስርዓት ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕግ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት፣ የአመራሮች አመራረጥ፣ ዘመናዊ አሠራር መዘርጋት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ አሠራርና መድረክ እንዲፈጠርላቸው ማድረግና ሌሎች የሪፎርም ተግባራት በዘገምተኛ አካሔድ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሲያከናውን መቆየቱ፣ ወይም ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ መክረሙ የአደባባይ ምስጢር ነው።

በዚህም መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የሕግ ማዕቀፍ መሰረት፣ የቦርድ ሰብሳቢና ምክትል ሰብሳቢ እንዲሁም ሌሎች አካላትን አሟልቷል። በእርግጥ የቦርድ ሰብሳቢዋ ከተመረጡ ከበርካታ ወራት ቆይታ በኋላ ነው በቅርቡ በሰኔ 7/2011 ምክትል ሰብሳቢን ጨምሮ ሌሎች የቦርድ አባላት የተመረጡት። ይህ የምርጫ የቦርዱን አባላት ለማሟላት የተሔደበት መንገድም ሆነ ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን እንዲሁም ሕጎችን (ለምሳሌ የኢትዮጵያ የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግን) ለማጽደቅ የተሔደበት እና እየተሔደበት ያለው መንገድ አዝጋሚ እንደሆነ አዲስ ማለዳ በተደጋጋሚ አቋሟን ማንፀባረቋ ይታወቃል።

በዘመናዊ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ ውስጥ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚገዙ የሕግ ማዕቀፎች የማይተካ ሚና እንዳላቸው አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። እነዚህ የሕግ ማዕቀፎችም ነፃ፣ ፍትሓዊ እና ተዓማኒ ምርጫዎችን ለማካሔድ የሚያስችል ስርዓት ከመዘርጋት ረገድ ወሳኝ ቦታ እንዳላቸውም ግልጽ የሆነ ጉዳይ ነው።

ይሁንና የተቋማት ግንባታም ሆነ ሕጎች በሒደት ከተሞክሮ በየጊዜው ሊሻሻሉ መቻላቸው እየታወቀ፣ በፍጥነት መሠራትና ወደ ሥራ መግባት ሲገባቸው፤ “ፍፁም” እንዲሆኑ ከመጠበቅ ሊሆን ይችላል፤ እነዚህን ለማስፈጸም የተመደቡ የመንግሥት አካላት ላይ ዘገምተኝነት በመታየቱ አገሪቱን ዋጋ እያስከፈላት ነው ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

እንደምሳሌ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተሻሻለው የሕግ ማዕቀፍ መሰረት የቦርድ አባላት ከተሟሉለት በኋላ ምርጫዎችን ለማካሔድ የሚያስፈልጉ ዝርዝር ሁኔታዎችን መመርመር ላይ እንደሆነ በመግለጽ፤ በዚህ መሰረት ካላው አጭር ጊዜ አንጻር ምርጫ አስፈጻሚዎችን መመልመል፣ ማደራጀት፣ ሥልጠና መስጠት፣ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን በክልል በተዋረድ አጠናቅቆ ማስፈጸም አይቻልም። ስለዚህም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች ምርጫዎች እንዲሁም የአካባቢ ምርጫዎች እንዲራዘምልኝ ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሐምሌ 4/2011 መጠየቁ ታውቋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከቦርዱ የቀረበለትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ፣ ሐምሌ 24/2011 በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የአዲስ አበባ እና የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶችን ምርጫ፣ እንዲሁም የአካባቢ ምርጫዎችን በጠቅላላ ምርጫ /General Election/ ወቅት፤ በቦርዱ በሚዘጋጀው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲካሔድ የውሳኔ ሐሳብ ፀድቋል።

አዲስ ማለዳ ለኹለተኛ ጊዜ የተራዘመው የከተሞቹ ምክር ቤቶች ምርጫን በተመለከተ “እስከ መቼ ድረስ በማራዘም መዝለቅ ይቻላል?” ስትል የሚመለከታቸውን ሁሉ ትጠይቃለች። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከአምስት ወራት በኋላ አካሒደዋለው ያለውን የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሔድስ ብቃት ይኖረው ይሆን የሚል ጥርጣሬም ያጭራል። የማራዘሚያ ጥያቄ ቢጠይቅ ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት።

እንደሚታወቀው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመንግሥት ሥልጣን ምንጭ በሕዝብ ነፃ፣ ፍትሓዊና ተዓማኒ ምርጫ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ላይ በየአምስት ዓመቱ የሚካሔዱት የጠቅላላ እና አካበቢ ምርጫዎች የሕዝብ ሥልጣን መገለጫዎች መሆናቸው በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጧል።

በእርግጥ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ሰላምና ደኅንነት ስሱ መሆኑ ይታወቃል። በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እና የሕግ ማሻሻሎች በከፍተኛ ዝግመት እየተካሔዱ ለመሆኑ ነባራዊው ሁኔታ ይመሰክራል። በአንጻራዊነት ከተሔደ ደግሞ የአዲስ አበባ እና የድሬ ዳዋ ከተሞች ሰላምና ደኅንነት ያን ያህል አስጊ የሚባል እንዳልሆነ ይታወቃል።

የመንግሥት ቁርጠኝነት፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዝግጁነት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደራጀ ቅስቀሳና ደጋፊዎችን ማደራጀት፣ እንዲሁም ሌሎች ከምርጫ ጋር በተያያዘ ሊሠሩ የሚችሉ ተግባራት ላይ በአጠቃላይ የኤሊ ጉዞ ይታያል። መጪው አጠቃላይ እና የአካባቢ ምርጫዎች አሁን ባለው አያያዝ መቼ ሊካሔዱ እንደሚችሉ አዲስ ማለዳ እርግጠኛ መሆን አይቻልም ትላለች። ምርጫዎችን ደግሞ በሰበብ በአስባቡ ማራዘም ሲደጋገም ለአምባገነን ስርዓት መፈጠር አመቺ ሁኔታ እንዳይሆን ስትል ሥጋቷን ትገልፃለች።

ሁሉም የሚመለከታው ባለድርሻ አካላት ‘የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ’ ከሚል ምክንያት በመውጣት የሚጠበቅባቸውን ማድረግ አለባቸው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ምርጫ ማካሔድ ወሳኝ ብቻ ሳይሆን ምትክ አልባ በመሆኑ አዲስ ማለዳ ትኩረት ተሰጥቶት ይሠራበት ስትል መልዕክቷን በአፅንዖት ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here