በትግራይ ክልል የዞን መዋቅርን የሚያስቀር ጥናት ቀረበ

0
717

የትግራይ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ከ1997 ጀምሮ ሲቀርብ ነበረውን የዞን መዋቅርን የማስቀረት ጥያቄ ለመመለስ ባስጠናው ጥናት መዋቅሩ እንዲቀር ምክረ ሐሳብ መቅረቡ ታወቀ። አብዛኛው የዞን ሥልጣኖች ወደ ወረዳ መውረዳቸውን ተከተሎም ይህ ነው የሚባል ፋይዳ የለውም የተባለው መዋቅር ላይ ለሚኖረው ለውጥም እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ ወርዶ ውይይት እየተደረገበት ሲሆን በቅርቡ ለክልሉ ምክር ቤት እንደሚቀርብም ይጠበቃል።

ምሁራን ባቀረቡት ምክረ ሐሳብ መሰረት የወረዳ መዋቅሩ የዞኑን ሥራ ሙሉ ለሙሉ የሚያከናውን እንደሆነ እና የወረዳዎችን አቅም በማጠናከርም የወጪ እና አሰራር ሒደት መራዘምን ያስቀራል ተብሎ ይጠበቃል።

የትግራይ ክልል የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ሊያ ካሳ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት የገጠርና የከተማ መዋቅርን በተመለከተ አጠቃላይ የልማት እና የመልካም አስተዳደደር ሥራዎችን ወደ ፊት ሊወስድ በሚችል መልኩ መደራጀት አለበት ተብሎ ከተለያዩ ምሁራን እንዲሁም ከኅብረተሰቡ የሚነሳውን ጥያቄ ለመመለስ የሚደረጉ ጥረቶች አንድ አካል መሆኑንም ተናግረዋል። ለዚህም በየደረጃው ያሉ አመራሮችም ሆነ አደረጃጀቶች በጉዳዩ ላይ በሰፊው የተወያዩበት ሲሆን ምሁራኖች ያቀረቡት ጥናታዊ ጹሑፍም የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች መሰብሰባቸውንም አንስተዋል።

ሆኖም ግን እስከ ወረዳ እና ቀበሌ ድረስ ወርዶ ውይይት ከተደረገበት በኋላ የዞን መዋቅር ይቀራል ወይስ አይቀርም ፣እንዲሁም ደግሞ የትኛው ወረዳ ተጨመረ ወይም ተቀነሰ በሚለው ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ከተወያዩነት በኋላ የሚወሰን ይሆናል በማለት ገልፀዋል።

በክልሉም በቅርቡ ከ20 በላይ ወረዳዎች መጨመራቸውንም ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አንድ ግለሰብ የገለፁ ሲሆን ይህም በክልሉ ከዚህ ቀደም ብዙ የወረዳነት ጥያቄዎች ሲነሱ መቆየታቸውንም ተናግረዋል። አክለውም አሁንም ቢሆን በክልሉ ያሉ ወረዳዎች በጣም ሰፋፊ የሚባሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ የቀርበው ጥናትም ሲቀርቡ ለነበሩት ጥያቄዎች እንደመነሻ ይሆናል እንጂ የመጨረሻ ሰነድ ለመሆንም የሚመለከታቸው አካላትን ውሳኔ ይጠብቃል ያሉት ሊያ፥ በየወረዳው ያሉ የወጣቶች፣ የሴቶችና የአርሶ አደሮች አደረጃጀት እንዲሁም ደግሞ የምክር ቤት አፈ ጉባዬዎች እና በየደረጃው ያሉ አመራሮች በጉዳዩ ላይ ተወያይተውበታልም ብለዋል።

የዞን መዋቅሮቹ እንዲቀሩ ዋነኛው ምክንያት ሆኖ የተጠቀሰውም ለዞን ኀላፊዎች የደሞዝና እንዲሁም የሚመደብላቸው ሌሎች ወጪዎች ከሚሠሩት ሥራ ጋር ሲነጻፀር ያነሰ በመሆኑ ምክንያት መሆኑን ለጥናት ቡድኑ ቅርበት ያላቸው ግለሰብ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 39 ሐምሌ 27 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here