የጅማ በርን የትራፊክ መጨናነቅ ይፈታል የተባለ መንገድ ሊገነባ ነው

0
695

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ከአየር ጤና በወለቴ አደባባይ ዓለምገና ወደ ጅማ የሚወስደውን 3 ነጥብ 4 ኪሜ መንገድ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ሊገነባ ነው።

የጨረታው ግዜ ሦስት ወር ይፈጃል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ ነገር ግን ለአንድ ዓመት ቀደም ተብሎ የወሰን ማስከበር እና የማስተር ፕላን ማጣጣም ሥራዎች መጠናቀቃቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ጥኡማይ ገ/እግዚአብሄር ገልጸዋል። በመዲናዋ ውስጥ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከሚያዘገዩ ምክንያቶች ዋነኛው ምክንያት የወሰን ማስከበር እንደመሆኑ፥ ይህንን ፕሮጀክት ከግንባታ በፊት ይህንን ሥራ መሰራቱን እና የአካባቢው ነዋሪም ካለው ከፍተኛ የመንገድ ችግር አንፃር ትብብር መደረጉንም ገልጸዋል።

ለአገር ውስጥ ተቋራጮች ክፍት የሆነው ይህ መንገድ በኮንክሪት ደረጃ በአንድ ግዜ አራት መኪኖችን የሚያስተናግድና የእግረኛ መንገዶችን የሚጨምር ሆኖ እንደሚገነባም የጨረታ ሰነዱ ያሳያል። ይህም ከስድስት መቶ እስከ ሰባት መቶ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ጥኡማይ፤ በተጨማሪም የአገር ውስጥ ተቋራጮችን አቅምም ያሳድጋል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። አክለውም በተዘዋዋሪ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ያሉት ጥኡማይ፣ በከተማው ውስጥ ከኹለት መቶ ሃምሳ ሺሕ በላይ የሥራ ዕድል በመጪው ዓመት ይፈጠራል በማለት ከተያዘው ዕቅድ ጋር የመንገድ ፕሮጀክቶች ክፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ሲሉ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ ከአምስት መቶ ሺሕ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶች አሉ ተብሎ ይገመታል።

በተያዘው የበጀት ዓመትም ለፕሮጀክቱ የ60 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለት ሲሆን፥ በኹለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በከተማ አስተዳደሩም በ2012 የበጀት ዓመት ወደ ግንባት ይገባሉ ተብለው ከሚጠበቁ 10 የመንገድ ፕሮጀክቶች አንዱ አካል እንደሆነ ጥኡማይ ገልጸው በ2012 የበጀት ዓመትም 20 ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ መያዙን ገልጸዋል።

በከተማዋ የእግረኞችን እንቅስቃሴ ለመጨመር 7 ነጥብ 3 ኪ.ሜ የእግረኞች መንገድ እና 190 ኪ.ሜ የኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። በአሁን ወቀት የከተማዋ መንገድ ሽፋን ከ20 ፐርሰንት በታች መሆኑ ከተማዋን ከዓለማቀፋዊ ደረጃዎች በታች እንደሚያደርጋትም የተለያዩ ጥናቶች አመላክተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here