አልቀመስ ያለው ኑሮ

0
1254

ለዓመታት በአገሪቱ የታየው የምግብ ሸቀጦች ዋጋ መናር ዕለት ተዕለት እየጨመረ መጥቶ፣ የሚሊዮኖችን ህልውና በመፈታተን ላይ ይገኛል። የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት፣ የምንዛሬ እጥረት፣ የትምህርት ቤት ክፍያዎች ማሻቀብና ሌሎችም ማኅበረሰቡን ሰቅዘው ከሚገኙት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የገንዘብ የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ሲሔድ እንጂ ከወቅቱ የገበያ ሁኔታ ጋር ሲጣጣም አይታይም። የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ ሸማቾችን፣ ነጋዴዎችን እና የዘርፉን ባለሙያዎች በማነጋገር የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ዕድሜው በ30ዎቹ መጨረሻ ላይ የሆነው ተዘራ ዓለምነው ነዋሪነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ነው። ዘወትር ከታዛው ሥር የሦስት ሕፃናት ልጆቹ ከርታታ ዓይኖች ይጠብቁታል። ወጣት ነው፤ ግን ቋሚ ሥራ የለውም። በሥራ አመራር የትምህርት ዘርፍ በዲፕሎማ የተመረቀ ቢሆንም ቅሉ፣ በቀን ሠራተኝነት በሚያገኘው አነስተኛ ገቢ ኑሮን ለመግፋት ይታትራል። የኑሮው ውድነት ግን ፈፅሞ አልገፋ ያለው ይመስላል።

“ከወራት በፊት 14 ብር ይሸጥ የነበረው ሽንኩርት 28 ብር ገብቷል፣ 70 ብር የሚሸጠው ዘይት 95 ብር እየተሸጠ ነው፣ ኩርማን የምታክል ዳቦ በ3 ብር መግዛት ከጀመርን ወር ሆኖናል፤ ጤፍ 2300 ብር እንገዛው የነበረው 3500 ብር እየተባለ ነው፤ ታዲያ በዚህ ዋጋ ገዝቼ ልጆቼን መመገብ እችላለሁ?” ሲል የሚጠይቀው የሦስት ልጆች አባት የሆነው ተዘራ፣ ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ሳይሆን፣ ለመኖር የሚያበቃ አመጋገብ እየመገባቸው መሆኑን ይገልጻል።

የኑሮ ውድነቱ በዚህ ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪ ላይ ብቻ አይደለም ቀንበሩን የጫነ የሚመስለው። በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነው ሌላኛው ወጣት የቤተሰብ አስተዳዳሪም ቢሆን፣ ተመርቆ የያዘው ዲግሪ የሕይወት አስቸጋሪ ዳገትን ከመቧጠጥ ሊታደገው አልቻለም። “ኻያ ኪሎ ጤፍ ከስድስት መቶ ብር በላይ ተገዝቶ፣ አምስት ሊትር ዘይት 430 ብር ተገዝቶ ለኹለቱ አንድ ሺሕ ብር ገደማ ወጥቶ፣ ሌሎቹን የምግብ ሸቀጦች መግዛት የማይታሰብ እየሆነ ነው” የሚሉት ሚሊዮን ማንደፍሮ በበኩላቸው፣ “የቤት ኪራይ፣ የኤሌትሪክ ፍጆታና ሌሎችም ወጪዎች ሲታሰቡ መኖርህን እንድታማርር ያደርጋሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ ዓይነቱ ችግር የተከሰተው ባለፉት ተከታታይ ኹለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ንረት እና የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ እየታየ መምጣቱን ተከትሎ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በተለይም ባለፉት ሦስት ወራት ችግሩ በስፋት ተስተውሏል። ይባስ ብሎ በሰኔ ወር 2011 በወጣው የማዕከላዊ ስታስቲክስ ሪፖርት መሠረት በስድስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የሆነው የምግብ ዋጋ ግሽበት ተከስቷል። ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚነሳው የአገሪቷ ምጣኔ ሀብት የተረጋጋ ሁኔታ ላይ አለመሆኑ ነው።

የኑሮ ውድነት በዋናነት መነሻው የምጣኔ ሀብት ቀውስ መሆኑን የሚገልጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ሃቢስ ጌታቸው፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ስርዓት እና ፖለቲካውም የኑሮ ውድነቱ ማባባሻ አካል መሆናቸውን ገልጸዋል ። ምንም እንኳን አገሪቱ የነጻ ኢኮኖሚ መርሕን ብትከተልም፥ የነዋሪዎች የነፍስ ወከፍ ገቢ ያደገ አይደለም የሚሉት ሃቢስ፣ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ድህነትን ሊቀንስ በሚችል መልኩ አለማደጉን ነው የሚናገሩት። በሌላ በኩል መንግሥት ባወጣው ሪፖርት ከድህነት ወለል በታች ያሉ ኢትዮጵያውያን ባለፉት ዐሥር ዓመታት ውስጥ ከ56 ሚሊየን ወደ 23 ሚሊየን ቀንሰዋል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ መደምደሚያ ላይ መንግሥት የደረሰው አንድ ዜጋ በ600 ብር ለአንድ ወር ሊኖር ከቻለ ድሃ አይደለም በሚል ዕሳቤ ነው።

በሌላ በኩል የዓለም ባንክ ባወጣው መለኪያ መሠረት አንድ ሰው ድሃ ላለመባል ቢያንስ 1000 ብር ወርሃዊ ገቢ ማግኘት ይጠበቅበታል። በዚህ መሠረት ከዚህ በታች የሆነ ገቢ በአሁኑ ወቅት የሚያገኙት ከ70 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ከድህነት ወለል በታች ናቸው ማለት ነው። በተለይም ይህ በቅርቡ ከተከሰተው የምግብ ዋጋ ግሽበት ጋር ተዳምሮ በድህነት አረንቋ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር የበለጠ እንዳይጨምረው ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

መካከለኛ ኑሮ የሚኖረው ሰው፣ በአሁኑ ጊዜ የድሃ ድሃ ደረጃ ውስጥ ገብቶ በኑሮ ውድነት እየተሰቃየ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ድሃ የነበረው ኑሮን ፈፅሞ መቋቋም አልቻለም ሲሉ ያለውን አስከፊ የኑሮ ሁኔታ ይገልጻሉ።

የግብርናም ውጤቶች የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም ሁኔታ እየሰፋ መታየቱ፣ የኑሮ ውድነትን እንዳያባብሰው ሃቢስ ስጋታቸውን ይገልጻሉ። ለአብነትም በመኸር ወቅት 314 ሚሊየን ኩንታል ምርት አገሪቷ ታገኛለች ተብሎ እንደሚጠበቅ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ቢያስታውቅም ይህ ግን ሊሳካ አልቻለም። በተለይም እንደ ጤፍ፣ በቆሎና የጥራጥሬዎች ምርት ቀላል የማይባል ቅናሽ ማሳየቱንና ከታቀደቀው በታች መሆናቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኑሮ ውድነቱ እሮሮ
በአዲስ አበባ በመምህርነት ሥራ ላይ የተሠማሩት ሰለሞን አስታጥቄ፣ በአገሪቱ ውስጥ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ከካንሰርም የከፋ ሕመም እንደሆነባቸው ይናገራሉ። “በአምስት መቶ ብር ስንገዛው የነበረው 25 ኪሎ ግራም መካከለኛ ጤፍ፣ አሁን ላይ ስምንት መቶ ብር ገብቷል” የሚሉት ሰለሞን፣ አንድ ኪሎ ግራም ምስር ከ55 ብር ወደ 70 ብር፤ የሰባት ብር ድንች ወደ 15 ብር፣ የ10 ብር ቀይ ሽንኩርት ወደ 28 ብር፤ ነጭ ሽንኩርት ከ60 ብር ወደ 160 ብር ጭማሪ አሳይቷል ብለውናል። እኛም ባደረግነው የገበያ ምልከታ የሰለሞንን ገለጻ እውነትነት አረጋግጠናል።

“ያልጨመረ ነገር ቢኖር የኔ ቁመት ብቻ ነው” በማለት የኑሮ ውድነትን በስላቅ ሊያልፉት የሞከሩት ሰለሞን፣ በኻያ ብር ሲገዙት የነበረው አንድ ሊትር የአትክልት ዘይት በመንግሥት በኩል የጤና ችግር ያስከትላል በመባሉ፣ አንድ ሊትር የኑግ ዘይት በ95 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን ነው የነገሩን። “መንግሥት ለዓመታት ስንመገበው የነበረውን የአትክልት ዘይት ‘አትመገቡ’ ቢለንም፣ ዘይቱን በጥቁር ገበያ ከሚሸጡ ግለሰቦች ላይ አንዱን ሊትር በ60 ብር እየገዛን መመገባችንን አልተውንም” ያሉት ሰለሞን፣ የኑሮ ውድነቱ በጤና ላይ ችግር ያስከትላል የተባለውን ዘይት እንኳን እስከ መብላት ድረስ እንዳስገደዳቸው በምሬት ገልጸውልናል።

ፅጌረዳ ደሴ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በሾላ ገበያ አካባቢ ከሚገኝ የባልትና ውጤቶች መሸጫ ሱቅ ነበር ያገኘናቸው። እዚህ አገር የሚታየው የኑሮ ውድነት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳስገባቸው የተናገሩት ግለሰቧ “በተለይ ደግሞ የአገር ውስጥ ምርቶች ላይ ይሄን ያክል የዋጋ ጭማሪ መደረጉ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል።” ነው ያሉት። በኑሮ ውድነቱም በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች እጅግ ከፍተኛ ሥጋት ውስጥ መሆናቸውን ነው ትዝብታቸውን ያጋሩት። “መካከለኛ የሚባል ወርሐዊ ደመወዝ አለኝ፤ ነገር ግን ከወር እስከ ወር ኑሮዬን መምራት አላስቻለኝም።

“ታዲያ ሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውስ…?” በማለት ነው የኑሮ ውድነቱን የገለጹት። “አገራችን የውስን ሰዎች ብቻ መኖሪያ እንዳትሆን እሰጋለሁ” ያሉት ፅጌረዳ፣ ኑሮን ለማሸነፍ አማራጭ በማጣትም የዝሙት ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች እንዳሉ ትዝብታቸውን አጋርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ለስርቆት መስፋፋት መንስዔ እንደሚሆን ተናግረዋል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የጠቆሙት።

የምግብ ነክ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት
በጤፍ፣ በቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ በዱቄት፣ በምስር፣ በቂቤ፣ በዘይት፣ በስኳር፣ በሞኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ሩዝና በተለያዩ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አዲስ ማለዳ ወደተለያዩ ማከፋፈያዎችና ገበያዎች በማቅናት ካሰባሰበችው መረጃ ለማወቅ ተችሏል። በተለይም በከተሞች ላይ የኑሮ ውድነት በስፋት ተስተውሏል።
ነጭ ጤፍ በአማካይ ከ3000 ብር እስከ 3600 ብር እየተሸጠ ነው። ይህ ከባለፈው ወር ጋር ሲነፃፀር ከ500 እስከ 1000 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው። ነጭ ሽንኩርት ከወር በፊት ይሸጥ ከነበረበት 60 ብር የ100 ብር ጭማሪ በማሳየት በሾላ ገበያና በአትክልት ተራ 160 ብር ሲሸጥ፣ በየሰፈሩ በሚገኙ ሱቆችና አትክልት መሸጫዎች ደግሞ የ140 ብር ጭማሪ በማሳየት እስከ 200 ብር በመሸጥ ላይ ይገኛል። 70 ብር በሊትር ይሸጥ የነበረው ዘይትም፣ የ25 ብር ጭማሪ በማሳየት በተለያዩ የአዲስ አበባ ገበያዎች 95 ብር ይሸጣል።

በቀበሌ ከሚከፋፈለው ዘይት በተጨማሪ በየመደብሮች የሚሸጠው ዘይት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማሳየቱም ታውቋል። 5 ሊትር የሱፍ ዘይት ከ320 ብር ወደ 415 ብር ጨምሯል። 20 ብር ይሸጥ የነበረው ፉርኖ ዱቄት የ10 ብር ጭማሪ አሳይቷል። ስኳር ከቀበሌ ውጪ 1ኪሎ በ40 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የ20ብር ጭማሪ እንደታየበትም አዲስ ማለዳ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ባደረገችው ቅኝት ታውቋል።

ምሥር የ20 ብር ጭማሪ በማሳየት በ75 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ አንድ ሊትር ወተት የወር ኪራይ ከ750 ብር ወደ 850 ገብቷል። እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ ሲሆኑ፣ በበርካታ የምግብ ሸቀጦች ላይ ከፍተኛ ጭማሬ መታየቱን አዲስ ማለዳ በስፍራው ተገኝታ አረጋግጣለች።

ነዋሪዎች ቀደም ሲል ከነበረው አመጋገብ በጥራትና በመጠን ባነሰ ሁኔታ ለመመገብ መገደዳቸውንና የኑሮ ውድነቱ ከመሻል ይልቅ በየጊዜው እየናረ መምጣቱን በመግለጽ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መግባታቸውን ነው የገለጹት።

የምግብ ዋጋ ግሽበት
ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰሞኑን ያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ በራሱ የሚናገረው አለ። ይኸውም የሐምሌ ወር 2011 የዋጋ ግሽበት ከ2010 ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 15.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። የምግብ ዋጋ ግሽበት የሐምሌ ወር 2011 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ20 በመቶ ጨምሯል።
ከሰኔ ወር ጋር ሲነፃፀር በሐምሌ ወር ዋና ዋና የእህል ዓይነቶች (በተለይ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ገብስ፣ ስንዴ፣ ማሽላና በቆሎ) ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ አሳይተዋል። በተለይም በክረምቱ ወራት ይቀንሳል ተብሎ የተጠበቀው የበቆሎ ዋጋ በየወሩ እየጨመረ በመሆኑ ቅናሹ ሊሳካ አልቻለም ብሏል ኤጀንሲው።

ከኤጀንሲው በተገኘው መረጃ መሠረት፣ የዳቦ ዋጋም ላይ የተወሰነ ጭማሪ ተመዝግቧል። አንዳንድ የአትክልትና ጥራጥሬ ዓይነቶች (አበሻ ጎመን፣ ጥቅል ጎመን፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ድንች፣ ባቄላና አተር) በተከታታይ ቅናሽ አሳይተዋል። በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች የዋጋ ግሽበት፣ የሐምሌ ወር 2011 ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር 2010 ጋር ሲነፃፀርም የ10.3 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በተለይ ልብስና መጫሚያ፣ የቤት ኪራይ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማስጌጫዎች፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ሕክምና እና ትራንስፖርት (በተለይ የቤት መኪና) ላይ የዋጋ ጭማሪው ጎልቶ ታይቷል።

የዋጋ ንረት መንስዔዎች
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር)፣ የዋጋ ንረቱ የታተመ ገንዘብ ነክ ችግር መሆኑን ያስረዳሉ። በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የታተመ ገንዘብ ብዛት ለዋጋ ንረቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን የሚገልጹት ዓለማየሁ፣ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የብር ብዛት ዋጋው እንዲንር ያደርገዋል ብለዋል።
ባለፉት ዐሥርት ዓመታት በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የታተመ ገንዘብ መጠን በ11 እጥፍ አድጎ 741 ቢሊየን ብር መድረሱን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል። ይህ መንግሥት የበጀት ጉድለት ሲያጋጥመው ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዲያትምለት ግፊት ማድረጉ ጋር ተዳምሮ ዛሬ ለተከሰተው የዋጋ ግሽበት አንድ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ለአብነትም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አጥላው እንደሚናገሩት፣ የፖለቲካ ግፊትና ተቃውሞዎችን ለማስታገስ ሲባል መንግሥት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመጀመር፣ ብዙ የበጀት ቀዳዳዎችን እየከፈተ፣ ከሚሰበስበው ገንዘብ በላይ ወጪው ስለሚሔድበት ይህንን ለማሟላት ሲል ብሔራዊ ባንኩን ገንዘብ አምጣ እያለ ሲወስድ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚገባው ገንዘብ በጣም ብዙ ይሆንና የዋጋ ንረት እንዲከሰት ያደርጋል። የውጭ ምንዛሬዎች በሚገቡበት ጊዜ በውጭ ገንዘቦች ፋንታ፣ መንግሥት ገንዘብ በብር ለውጦ በሚሰጥበት ጊዜ በመንግሥት በኩል እጥረት የሚገጥመውና የሚያራባ ከሆነም የዋጋ ንረት እንዲከሰት መንስዔ ይሆናል ሲሉም ያክላሉ።

ዓለማየሁ እንደሚሉት፣ ከባንኮች በተለያዩ ምክንያቶች በቀላሉ መበደር እና ገንዘብ አግኝቶ መንቀሳቀስ በቀላሉ የሚቻል ከሆነም በገበያ ውስጥ የሚንሸራሸረው ገንዘብ ይበዛና ለዋጋ ንረት የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ ሊኖረው ይችላል። በኢኮኖሚ ውስጥ ብዙ ገንዘብ መኖሩን የሚናገሩት ዓለማየሁ፣ ያ የዋጋ ግሽበቱን ከፍ እንዳደረገው ያመላክታሉ። ገንዘቡ ተሠርቶበት ሳይሆን፣ በተለያዩ ምክንያቶች ወጪ መደረጉንና መንግሥትም ሲቸግረው ገንዘብ ስለሚያትም የዋጋ ንረቱን ከፍ እንዳደረገው ያወሳሉ።

ገንዘብ ገበያ ውስጥ ባይገባ ኖሮ አንዱ ዕቃ ሲወደድ ሌላኛው ዕቃ ሊረክስ ይገባ ነበር የሚሉት አጥላው በበኩላቸው፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው ገንዘብ ውስን ቢሆን፣ ሁሉም እቃዎች ሲጨምሩ መግዣ ይጠፋ እንደነበር ገልጸው፣ ነገር ግን ብዙ ገንዘብ ኢኮኖሚው ውስጥ ስለተረጨ በሁሉም ዕቃዎች ላይ ዋጋ መጨመሩን ያስረዳሉ።
ኹለቱም የምጣኔ ኀብት ባለሙያዎች ለዋጋ ንረቱ ዋናው መንስዔው ገንዘብ አያያዝ መሆኑን ያምናሉ። ሌሎች ምክንያቶች አባባሽ ናቸው። ሃቢስ በበኩላቸው፣ የሰላም ሁኔታም ከዋና አባባሾቹ አንዱ ነው ይላሉ። ሰላም ከሌለ ሥራ በየጊዜው ስለማይሠራ አቅርቦት እንዲያንስ ያደርጋል። አቅርቦት ሲቀንስ ደግሞ ዋጋው ወደ ላይ ከፍ እንዲል ያደርጋል በማለት የሰላም ዕጦት የኑሮ ውድነትን እንዴት እንደሚያባብስ ያስረዳሉ።

ከሰላም ማጣት ጋር ተያይዞ፤ ዋጋ በአድማ እየተወሰነና የምርቶች ሥርጭት ሥልታዊ በሆነ መንገድ እየተስተጓጎለ፣ ስለ ነጻ ገበያ መነጋገር ፈፅሞ አይቻልም የሚሉት ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ ከአምራች ወይም ከአስመጪ እስከ ችርቻሮ ንግድ ድረስ ያለው መጠኑ የበዛ ሰንሰለት፣ በፍላጎትና በአቅርቦት ሕግ መተዳደር ያለበትን ጤናማ ግብይት ጤና እያሳጣው ነው ይላሉ። ጥቂቶች ገበያውን እንደፈለጉ በሚያሾሩበት አገር ውስጥ የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን እየገረፈው ነውም ብለዋል።

በሌላ በኩል ሕዝቡን ከአልጠግብ ባዮች ይታደጋሉ የተባሉ የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራትና በመንግሥት የተቋቋሙ የማከፋፈያ ድርጅቶች ጥቅም ግልጽ እየሆነ አይደለም የሚሉት ሃቢስ ጌታቸው፣ እነዚህ ዋጋን በማረጋጋት የምርቶችንና የሸቀጦችን ሥርጭት ፍትሐዊ ያደርጋሉ የተባሉ ተቋማት፣ ሕዝቡን ከሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት ሊከላከሉ አለመቻላቸውን ያወሳሉ። ብዙዎቹ የተቋቋሙበትን ዓላማ እየሳቱ በአልጠግብ ባዮች መጠለፋቸው እየተነገረ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ሕዝቡን አስመራሪ ከሆነው የኑሮ ውድነት ሊታደጉት ካልቻሉ ሚናቸው ምንድን ነው? ሲሉም ይጠይቃሉ።

እንደ ሃቢስ አባባል፣ የግብይት ስርዓቱ የተመሰቃቀለና ለሕዝቡ ሕልውና አደገኛ እየሆነ ነው። ምንም ዓይነት አሳማኝ የሆኑ ምክንያቶች ሳይኖሩ በጣም መሠረታዊ የሆኑ የምግብ ፍጆታዎች ዋጋቸው ሲጨምር ይታያል። ምሥር፣ በርበሬ፣ ሥጋ፣ ድንች፣ ዘይት፣ ወተት፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንቁላል፣ ወዘተ. ድንገት ዋጋቸው ሲጨምር፣ ለጭማሪው አጥጋቢ ምክንያት አይሰማም የሚሉት ሃቢስ የግብይት ስርዓቱን ጤናማነት መከታተልና መቆጣጠር የሚገባቸው መንግሥታዊ አካላት ምንም ሲሉ አይደመጡም ሲሉ ያወሳሉ።

የምጣኔ ሀብት ዕድገት (GDP growth) በአብዛኛው ቁሳቁሶችንና የአገልግሎቶች ዕድገትን ነው የሚያሳየው የሚሉት ሃቢስ፣ ይኼ የሕዝብን ልማትና ደኅንነት አያሳይም ብሎ የተባበሩት መንግሥታት ልማት ፕሮግራም ይፋ ማድረጉን ይገልጻሉ። ልማት የሚለካው በሕዝቡ ጤንነት፣ የትምህርት ደረጃና ሕዝቡ በሚኖርበት የዕድሜ ወሰን ነው የሚሉት ሃቢስ በዚህ ደረጃ በጣም ገና ነን ሲሉም ያክላሉ። ይኼንንም ከግምት ወስጥ በማስገባት፣ ኢትዮጵያ አሁን ያለውን የኑሮ ውድነትና ድህነት ከመቅረፍ አኳያ የሚሠራው ሥራ በአጭሩ ሊሠራ የሚችል ነገር እንደሆነም ሃቢስ ይጠቁማሉ።

በሌላ በኩል፤ ከዋጋ ግሽበት ጋር ተያይዞ ቁጠባ ሊቀነስ እንደሚችል ባለሙያዎች ያነሳሉ። በዕቃዎች ጭማሪ የተነሳ ዜጎች ገንዘብ ከመቆጠብ ይልቅ የራሳቸውን ጊዜያዊ ፍላጎት ማሟላት ላይ ብቻ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚችሉ ከዚህ ቀደም በዋጋ ግሽበት ላይ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። በሌላ በኩል፤ የዋጋ ግሽበቱ መጨመር የመንግሥትን ወጪ የበለጠ ሊጨምረው እንደሚችልና የበጀት ጉደለትን በማስፋት የበለጠ አገሪቷን ችግር ውስጥ እንዳይከታት ባለሙያዎች ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
እንደ መፍትሔ

በተለይ በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦችና አገልግሎቶች የዋጋ ግሽበት በሕዝቡ ውስጥ ምሬት እየፈጠረ መሆኑን የሚናገሩት ዓለማየሁ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ በመካከለኛ የገቢ ደረጃ ላይ ይገኛሉ የሚባሉ ዜጎች ጭምር ኑሮውን መቋቋም አቅቷቸዋል ሲሉም ያስረዳሉ። በአንድ ወቅት ጋብ ብሎ የነበረው የዋጋ ግሽበት እያንሰራራ መሆኑን አስታውሰው፣ መፍትሔው ደግሞ ሙሉ ኃይልን በዚህ ላይ በማዋል የዋጋ ግሽበቱን ቢቻል መቀነስ፣ ካልሆነ ደግሞ ባለበት ማስቆም የግድ ይላል ሲሉ ይገልጻሉ።

አጥላው፣ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እስካሁን የመጣንባቸውን አገሪቷ ያለፈችባቸው ሒደቶችና አፈፃፀሞች በመመርመርና ጉድለቶችን በመንቀስ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ እንዲሁም ፖሊሲዎችን መፈተሽ ባለ ኹለት አሐዝ ሆኖ መመዝገብ ከጀመረ ኹለት ዓመት ከግማሽ የሆነውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ተገቢ እንደሚሆን አውስተው፣ በተለይ በመዋቅራዊ ለውጥ ሒደት ውስጥ ከነፍስ ወከፍ ገቢ ዕድገት ባሻገር የሰው ኃይል፣ የቁሳዊ ካፒታል እና የቴክኖሎጂ አጠቃላይ አገራዊ አቅሞቻችንን መፈተሽ እንዳለበት ይናገራሉ።

ምጣኔ ሀብቱ የሚመራው በተወዳዳሪነት በሚዘልቅ አቅም ወይም መሬት ባልያዘ አቀባባይ የአገልግሎት ዘርፍ ስለመሆኑ መለየት አለበት የሚሉት አጥላው የአንድን አገር ምጣኔ ሀብት በዘላቂነት የሚያሳድገው ቁሳዊ ካፒታል በየትኛውም መንገድ ማከማቸት ስለተቻለ ሳይሆን ሀብቱን በፍፁም ተወዳዳሪነት፣ ቅልጥፍና ማምጣት በሚያስችሉ ዘርፎችና አግባቦች ማዋል ሲቻል ነውም ባይ ናቸው። ይህም ዋጋ ግሸበቱን ለመቆጣጠር ወሳኝ መሆኑን ያነሳሉ።

በመጨረሻ በልማት ሒደት ውስጥ ወሳኙ ነገር ስርዓታት ወይም ተቋማት መሆናቸውን የሚናገሩት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ሰይድ ኑሩ (ዶ/ር) መንግሥትንና ማኅበረሰብን ጨምሮ የስርዓታት ወይም ተቋማት ለውጥ ከሌለ፣ ልማትና ምጣኔ ሀብቱን ዋጋ ግሽበትን በሚገባ መቆጣጠር ማሰብ አይቻልም ይላሉ።

ግብርናው በራሱ የኢንዱስትሪውን ግብዓት ይፈልጋል የሚሉት ሃቢስ በበኩላቸው፣ ግብርናው ዘመናዊ ለማድረግ የኢንዱስትሪ ምርት ያስፈልገዋል ሲሉ ያወሳሉ። ግብርናው ገበያ እንዲያገኝ እንደገና ኢንዱስትሪውን ይፈልጋል ይላሉ። “ሰሊጥ እያመረትን የዘይት ችግር አለብን። ኢንዱስትሪውን ተጠቅመን ስለማናመርተው እኛው የላክነው ሰሊጥ ዘይት ሆኖ እንደገና ይመጣልናል። የእኛ ገበሬ ሰሊጥ አምርቶ ወደ ቻይና ይልካል፤ እኛ ደግሞ የረጋ ዘይት ከውጭ እናስመጣለን። ይህ መሠረታዊ ችግር ነው። እናምርተው አላልንም እንግዛው እንጂ፤ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ጥረት መደረግ አለበት” ሲሉ ባጠቃላይ የአገራችንን የኑሮ ውድነት ለመቅረፍ እነዚህ መታየት እንዳለባቸው ሃቢስ ይመክራሉ።

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ከውጪ የምናስገባቸውን ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት እንችላለን የሚሉት አጥላው በበኩላቸው፣ ቅጥ ያጣ የምግብ ስርዓት ባለበት ሁኔታ ችግሮችን መቅረፍ የማይታሰብ በመሆኑ፣ ትክክለኛውን የምጣኔ ሀብት ፍኖተ ካርታ በመዘርጋት ችግሩን መቅረፍ አዋጪ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ዓለማየሁ፣ መንግሥት በጣም መሠረታዊ የሚባሉ የምግብ ምርቶች (ዘይት፣ ዱቄት…) ዋጋ እየደጎመ ቢሆንም፣ ከሁሉም በላይ ግን ሥርዓት አልባ የሆነው የግብይት ስርዓት አንድ ሊባል እንደሚገባውም ያሳስባሉ። መንግሥት ገበያው ውስጥ ገብቶ ዋጋ ይወስን፣ ወይም በዚህና በዚህ ይሸጥ እንዲባል ሳይሆን ይህ ያልጎለበተ የግብይት ስርዓት ተቆጣጣሪ እንደሚያስፈልገውም ይገልጻሉ።

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር መንግሥት በትኩረት እንደሚሠራ ማስታወቃቸው ይታወሳል። ይሁን እንጂ በጉዳዩ ላይ የተለያዩ መፍትሔ በባለሙያዎች ቢቀርብም ለቤተሰብ አስተዳዳሪው ተዘራ ወሳኙ ነገር መንግሥት ለችግሩ በጊዜ አፋጣኝ እልባት በመስጠት ዜጎች በነጻነት ተመግበው ኑሯቸውን እንዲመሩ ማድረጉ ላይ ነው። “በዚህ ዘመን፣ ባልተገባ ድንገተኛ ዋጋ ግሽበት ምክንያት በየቀኑ በልተን እንደምናድር የማንጨነቅበት አገር ሊኖረን ይገባል” ሲል ተዘራ ንግግሩን ያጠቃልላል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here