ከ50 በመቶ በላይ ወጣቶች የጫት ሱስ ተጠቂ ሆነዋል ተባለ

0
1937

የሴቶች ሕፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ባሳፍነው ሳምንት ይፋ ባደረገው ጥናት በኢትዮጵያ ካሉ አዋቂዎች እና ወጣቶች መካከል 51 በመቶ የሚሆኑት ጫት ቃሚዎች መሆናቸውን እና ከዚህም ውስጥ የወንድ ጫት ቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛው እንደሆነ ጥናቱ አመላክቷል።

ከከተሞች ይልቅ በገጠራማ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጫት መቃም እንደበለጠ የገለጸው ጥናቱ፤ በተለይም በድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሶማሌ እና በአማራ ክልሎች ከሌላው የአገሪቱ አካባቢዎች በበለጠ በገጠራማ ክፍሎቻቸው የጫት ቃሚዎች ቁጥር እንደሚበዛም አመላክቷል።ጥናቱ በማከልም ከተለዩት የጫት ቃሚዎች በአማካኝ በ17 ዓመት ዕድሜያቸው ጫት መቃም እንደሚጀምሩ ገልጿል።

በጫት ምርት፣ ንግድ እንዲሁም ማኅበራዊ ውጤቶች ላይ በርካታ ምርምሮችን እንዲሁም መጽሐፍትን ያዘጋጁት ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ፤ ጥናቱ በተለይም የጫት ቃሚዎች ቁጥር በገጠራማ አካባቢዎች ቁጥሩ ከፍ ያለ ነው የሚለውን እንደማይስማሙበት ገልጸው በተለያዩ ዓመታት በሠሯቸው ጥናቶች ከተሜው የበለጠ ጫትን እንደሚቅም ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

“ዕድገቱ በተለይም በከተማ ውስጥ አያጠራጥርም፤ በከተማ ያለው ሥራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ ለዕድገቱ ምክንያት መሆናቸውን የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ” ያሉት ሕዝቄል “ጫት ጊዜ ለማሳለፍ ስለሚሆን በከተማ እንደቀድሞው ዕድሜ፣ ሃይማኖት፣ ፆታ ወይም ጊዜ ሳይለይ በመላው አገሪቱ ቁጥሩ ጨምሯል” ሲሉ ያብራራሉ።
ጫት መቃም ለከፍተኛ የደም ግፊት፣ ለልብ ሕመም፣ እንዲሁም የአዕምሮ ጤናን እንደሚያዛባ የሚገልጸው ጥናቱ፣ ከዚህ በተጨማሪም ሲጋራ ማጨስ እንደ ኮኬን እና ሄሮይን ያሉ ሱስ አስያዥ ዕፆች ለመጠቀም ምክንያት በመሆን በተጠቃሚዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራን እንደሚስከትልም ያስረዳል።

የአላህ ቅጠል (Leaf Of Allah) የተባለውን ጥናታዊ መጽሐፍ ጨምሮ ስድስት የተለያዩ ጥናቶችን እና ጽሑፎችን በጫት ላይ የጻፉት ሕዝቅኤል ግን “ጫት የጤና ጉዳቶች ያደርሳል የሚለው ላይ መሥማማት የለም፤ አንድ ጥናት ለጤና ጠንቅ ነው ያለውን፣ ሌላ ጥናት ጫት ለተመሣሣይ ችግር መፍትሔ ነው ይላል” ሲሉ ተናግረዋል።

“ጫት ሱስ ውስጥ የሚከት መሆኑ እና ይህንን ሱስ ለማከናወንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግጭት ውስጥ መክተቱ አይቀርም” የሚሉት ሕዝቅኤል ጫት የራሳቸው ገንዘብ ምንጭ በበቂ ሁኔታ በሌላቸው ሰዎች ላይ ያለው ጫና ቀላል አለመሆኑን ይናገራሉ።“ማኅበራዊ ግንኙነትን ግን የሚያጠናክር፣ ሰዎች ተቀራርበው እንዲነጋገሩ የሚያደርግ እና በአንዳንድ አካባቢዎች ላይም የንግድ ድርድሮች እንዲሁም ውሎች የሚደረጉበትን ትሥሥር የሚፈጥር ነው” ሲሉም ይሞግታሉ።

ጫት ኢኮኖሚያዊ አቅም ላይ የሚያሳድራቸው ተፅዕኖዎች እንዳሉ ሆነው ቤተሰብ እስከ መበተን የሚደርሱ ችግሮችን በመፍጠር ማኅበረሰብ ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚሉ ጥናቶች ቢኖሩም፥ ጥልቀቱ ያለመገለጹን የሚናገሩት ሕዝቅኤል፥ እሳቸውም እነዚህ ጉዳቶች መኖራቸውን እንደሚስማሙባቸው ግን ይናገራሉ። አክለውም “በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዘንድ ግን አብሮ በመሆን አምላክን ለማምለክ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል፤ ይህም ጫት በኹለቱም አቅጣጫ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ምሳሌ ነው” ብለዋል።

በጫት ሱስ ውስጥ ካሉት ወጣቶች እና አዋቂዎች መካከልም 45 በመቶ የሚሆኑት በወር ውስጥ ቢያንስ ስድስት ግዜ አልኮል መጠጥ እንደሚጠቀሙ ጥናቱ ጨምሮ ገልጿል። በተለይም በአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ትግራይ እና አፋር ክልሎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጫት ቃሚዎች አልኮል መጠጥም እንደሚጠቀሙ ጥናቱ አመላክቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here