“ለሴተኛ አዳሪነት መፍትሔው ክልከላ አይደለም”

0
692

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሳቅ በሞላበት፣ እንባ በራቀበት፣ ችግር ድርሽ በማይልበት እና ስቃይ በማይገኝበት ስፍራ የሚመኙትን የሥራ ዓይነት እየሠሩ መኖርን የሚጠላ ሰው የለም። ነገር ግን የሚመኙትን ዓይነት ኑሮ መኖር ሁሉም አልታደለምና የሕይወትን ትግል ለማሸነፍ እያንዳንዱ ሰው በየፊናው መሮጡ አይቀሬ ነው። በዚሁ መሰረት ድህነት የከፋባቸውና መጠጊያ ያጡ እህቶች ድህነትን ማምለጥ ባይችሉ እንኳን ነፍስን ለማቆያ የሚሆን የዕለት እንጀራ ፍለጋ ወደ ሴተኛ ዳሪነት ሕይወት የሚገቡበት ሁኔታ ሰፊ ነው።

ድህነት ሲባል በጉስቁልና መኖር ብቻ አይደለም። በእጃቸው ምንም ዓይነት ገንዘብ ባለመኖሩ በሕመም ለሚሰቃዩ የቤተሰባቸው አባል መድኀኒት ለመግዛት፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ፣ ረሃብን ለማሸነፍና ጎዳና ከመውደቅ ይሻላል በሚል የሴተኛ አዳሪነትን ሕይወት የሚመርጡ ሴቶች ቁጥር ቀላል አይደለም። ከድህነት በተጨማሪ በልጅነት ጊዜ የሚደርስ ጥቃት በተለይ ከተገዶ መደፈር ጋር የተያያዘ ሌላው ምክንያት ነው። በልጅነታቸው ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችም ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንደሚገቡ በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያሳያሉ። ሱሰኝነት፣ ተገቢውን የወላጅ ክትትል ማጣትና የአቻ ጓደኛ ግፊትም ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው።

በዓለም ላይ 42 ሚሊዮን ሰዎች በወሲብ ንግድ ሥራ ላይ የተሠማሩ ሲሆን አብዛኞቹ ሴቶች ናቸው። በኢትዮጵያ ደግሞ 19 ሺሕ 305 ያህል በሴተኛ አዳሪነት ሕይወት ላይ የተሰማሩ እህቶች እንዳሉ በ2016 የወጣ ጥናት ይጠቁማል። ከዚሁ ሥራም በዓለም ላይ በየዓመቱ 100 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል። በአንዳንድ አገሮች ሴተኛ አዳሪነት በሕገወጥ ሥራነት ተፈርጆ በሕግ የሚያስቀጣ ተግባር ሲሆን በሌሎች አገሮች ደግሞ ሕጋዊ ነው። እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ሴተኛ አዳሪነት በወንጀል የማያስቀጣ ቢሆንም አሁን ግን ድርጊቱን በሕገወጥነት የሚፈርጅ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው። ነገር ግን ሴተኛ አዳሪነት ውጤት ነው። እናም ሴት እህቶቻችን ወደ ሴተኛ አዳሪነት ሕይወት እንዲገቡ የሚያደርጋቸው ገፊ ምክንያት ላይ በቂ ጥናት ሳይደረግና ለእነዚሁ ምክንያቶች በቂ መፍትሔ ሳይሰጥ ሴተኛ አዳሪነትን በሕግ ለመከልከል ቅድሚያ መስጠት ከፈረሱ ጋሪውን እንደማስቀደም ነው።

በየዓመቱ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎች ሥራ አጥተው እየተንከራተቱ ባለበትና የኑሮ ውድነት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረና ለአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮ እየከበደ ባለበት ወቅት አማራጭ የሥራ ዘርፍ ሳይዘጋጅ ሴተኛ አዳሪነትነ በሕግ መከልከል አዋጪ መፍትሔ አይደለም። ሕይወቱ በጣም ከባድና በአብዛኛው ማንም ሰው ካልቸገረው እንደ አማራጭ የሚያየው አይመስለኝም። ነገር ግን ከከባዱ ሕይወት የከበደ የሕይወት ፈተናን ለማምለጥ የመረጡት መንገድ ይመስለኛል። እናም ውጤቱ ላይ ከመረባረብ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ትኩረት ቢደረግ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ።

ኪያ አሊ
kiyaali18@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 41 ነሐሴ 11 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here