ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሥልጣን ከጨበጡበት የመጀመርያ ዕለት አንስቶ ባደረጓቸው ንግግሮች ስለቀጣዩ አጠቃላይ ምርጫ በተደጋጋሚ የተለያዩ አስተያየቶች የሰጡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ አስተያየቶችም የሚያጠነጥኑት ቀጣዩን ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ተዓማኒ፣ እንዲሁም አሳታፊ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን የሚያወሱ ነበሩ።
ቀኑ እየቀረበ ሲሄድም ጉዳዩ ከፖለቲከኞች ባለፈ ተርታውን ህዝብ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለበት እና የለም የምርጫው ጊዜ መራዘም አለበት በሚል በማከራከር ላይ ይገኛል።
በኢሕአዴግም ሆነ በመንግሥት የቀጣይ አገር አቀፍ ምርጫን በወቅቱ መካሄድ አለመካሄድን በተመለከተ መመካከር እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ የተጠቀሰ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ ቀጣዩ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ መካሄድ አለበት የሚል አቅጣጫ ማስቀመጡን ሰምተናል።
ከዚህ አንፃር፣ ቀጣዩ ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ይካሄድ ከማለት ባለፈ፣ ከሁሉም በፊት ሰላም መስፈን አለበት። ለምርጫ የሚወዳደሩት ፓርቲዎች በየክልሉ እየተዟዟሩ መቀስቀስና የፖለቲካ ሥራዎችን መሥራት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው፣ ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል ከማናችንም የተሰወረ ባለመሆኑ፣ መጀመሪያ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የሰላም ጉዳይ መሆኑን አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ከሰላምና ደኅንነት መረጋገጥ ባሻገር ፣ እንደ ሲቪል ማህበራት፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የፍትህ ተቋማትና ገለልተኛ የጸጥታ ተቋማትን የመገንባት ሂደቱ በፍጥነት መጠናቀቅ ይኖርበታል። በነዚህ ተቋማት ላይ ሊኖሩ የሚገባቸው ማስተካከያዎችና እርምጃዎች ከምርጫው በፊት ባለው ግዜ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ማስወገድ ባይቻል እንኳን መሰረታዊ ለሆኑት ቅድሚያ በመስጠት ለምጫው መደላደልን መፍጠር ይቻላል።
የአገር አለመረጋጋቱም ሆነ የተቋማት ግንባታው መካሄድ የሚኖርበት ቅቡልነት ባለው መንግሥት አማካይነት እንደሆነ ቢታመንም በቅድሚያ ግን ለአገር ህልውና እና ለዜጎች ደሀንነት ዋስትና መስጠት ያስፈልጋል። ይቅርና በተለያዩ የማንነት ግጭቶች ተወጥራ ለወትሮው ማንም ሊነካቸው ከሚፈራቸው ቤተ እምነቶችን ጭምር ባስደፈረ ስር የሰደደ የቀውስ አዙሪት ውስጥ ባለች አገር ምርጫ ሰላማዊ ሃገሮችን ጭምር የማተራመስ ሃይል አለው፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለድርሻ አካላትና ተቋማት ባለፈው ታሪካችን ላይ የሚያደርጉትን ማለቂያ የሌለው እሰጥ አገባ አቁመው መጪው ትውልድ የእኔ ነው ብሎ የሚቀበለውን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የየራሳቸውን ብእር መያዝ ግዴታም ጭምር ነው።
የዚህ አዲስ ታሪክ የመጀመርያው ምዕራፍ በፍትሕ፣ በዴሞክራሲና በፖለቲካ ተቋማት ግንባታ መጀመር አለበት። ምን ዓይነት የፌዴራል አወቃቀር ነው የሚበጀን? ምን ዓይነት የመንግሥት ቅርፅ ነው የሚያስፈልገን? ለሚሉ የአገራችንን የወደፊት አቅጣጫ በሚወሰኑ ትልልቅ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለድርሻዎች የሰከነ ምክክር ማድረግ እንጂ ከድጡ ወደ ማጡ የሚከት የክርክር አዙሪት ውስጥ መቆየት ትርፉ ለጠላት እንጂ አህብ አይደለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በውይይቱ ላይ የራሱን ድምፅ የሚያሰማበትን መንገድም መፍጠር አለባቸው።
ለዚህም የመገናኛ ብዙሃን ሚና የማይተካ መሆኑን አውቀው ከአሁኑ የአቅም ማጎልበት ስራዎችን በመስራት ዝግጅት መጀመር ይገባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር የሚያስተናግዳቸው ፓርቲዎችና ስብስቦች ለፓርቲ ፖለቲካ ሥራ ብቃት ይኖራቸዋል ተብለው ከሚታሰቡት ጀምሮ፣ ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ ጭምር ታጭቀውበታል። በቤተሰብ አባላት ከተደራጁት ጀምሮ ጊዜያዊ ዓላማ ያቆራኛቸውም አሉ። እጅግ በጣም ጥቂት የሚባሉት ካልሆኑ በቀር ለአቅመ ፖለቲካ ያልደረሱ፣ ወይም የፖለቲካ ሥልጣንን ለግል ጥቅም ማጋበሻ ለማድረግ የተሠለፉም ይገኛሉ። አደገኛ የሚበለውን የዓመታት ቁርሾና ቂማም ይዘው ለደጋፊዎቻቸውም የሚያቀርቡት የፖሊሲ አማራጭ ሳይሆን በዚህ ቂም ላይ የተመሰረተ ጥላቻ ከመሆን አልፎ አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ማድባት ከራሳቸው አልፎ ለደጋፊዎቻቸው የሚተረፍ መዘዝ አለው።
ይህንን የፖለቲካ ምኅዳር በእውቀት፣ በእርቅ እና ለህዝቡ የተሸለ ሃሳብ በማምጣት ላይ የሚመሰረት ካልሆነ በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት ህልም ሆኖ ይቀጥላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብና የአገራቸው ጉዳይ የሚያሳስባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች አባሎቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን በማነቃነቅ ይህ የሽግግር ጊዜ በሰላም ተጠናቆ ለነፃ፣ ለዴሞክራሲያዊ፣ ለፍትሐዊና እውነተኛ ምርጫ ለመብቃት በቁርጠኝነት መሥራት አለባቸው።
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በሰላም እንድትሸጋገር፣ የሕግ የበላይነት የሁሉም ነገር ምሰሶ እንዲሆን፣ ፍትሕ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ተደራሽ እንዲሆን፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሴረኝነትና በቀልተኝነት እንዲወገዱና መጪው ጊዜ ብሩህ እንዲሆን ይህንን የለውጥ ጉዞ ይደግፉ። ስህተት ሲፈጸም እያረሙ፣ አድልኦ እንዳይኖር እየታገሉ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል መልካም ግንኙነት እንዲመሠረት አርዓያ እየሆኑ፣ ጥቅም የሌላቸው ሥራ አስፈቺ ተግባራት ታቅበው የውይይትና የክርክር ባህል እንዲጎለብት ምሳሌ በመሆን፣ ኃላፊነታቸውን ይወጡ።
ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር የሚያስፈልገው አድርባይነትና ጠመንጃ ሳይሆን፣ የነጠረ የሐሳብ የበላይነት መሆኑን መተማመን ይገባል። ሰላማዊው ፖለቲካ የሕገ ወጦችና የሥርዓተ አልበኞች መጫወቻ እንዳይሆን እንደህዝብ መተባበር የግድ መሆን አለበት።
መጪው ምርጫ በሰላም ከመጠናቀቅ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያለው ሚና በቀላሉ የማይታይ እና የአገሪቱ ህልውና የሚመሰረትበት መሆኑን ክግምት በማስገባት ሁሉም የቤት ስራውን ጠንቅቆ በማገባደድ በጠበቅ ይገባል።
ቅጽ 1 ቁጥር 42 ነሐሴ 18 2011


