የኦሮምያ ሚዲያ ኔትወርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ ከሆኑት ጀዋር መሀመዱ የሚመራው (ኦ.ኤም.ኤን) ከቀድሞው ዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬድዮ ጣቢያ እና ከአሁኑ የአዋሽ ኤፍ.ኤም ለጊዜው የአየር ሰዓት በመግዛት እንዲሁም በአጭር ግዜ ውስጥ ደግሞ ድርሻ በመግዛት ለመሥራት ስምምነት ላይ ደረሱ።
ከሬዲዮ ጣቢያው ስያሜ ለውጥ ባሻገር የአስተዳደር ለውጥም እንደተደረገ እና በመጪው መስከረም ወር ኦ.ኤም.ኤን በገዛው የአየር ሰዓት ስርጭት እንደሚጀምርም ለማወቅ ተችሏል። በአብዛኛው የአማርኛ ቋንቋ ስርጭት ይኖራቸዋል ያሉት ምንጫችን ምንአልባትም ለአንድ ሰዓት የኦሮሚኛ ቋንቋ ፕሮግራሞች ሊኖሩ ይችላሉም ብለዋል።
ኦ ኤም ኤን ከአንድ ዓመት በፊት የሬድዮ ጣብያ ለመክፈት ለብሮድካስት ባለስልጣን ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም እስከአሁን መልስ ባለማግኘቱ ከዛሚ ኤፍ ኤም ጋር ለመሥራት እንዲወስን እንዳረገውም ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል። ታቅዶ ለነበረው የሬዲዮ ጣቢያም ሙሉ እቃ ከውጪ አገር ገብቶ እንደነበርም ለማወቅ ተችሏል።
እነዚህን እቃዎች በመጠቀምም በአዳማ ከተማ አዲስ ሬድዮ ጣቢያ በማቋቋም ስርጭቱን በኦሮምኛ ቋንቋ ለማድረስ መታሰቡንም ምንጮች ጨምረው ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ግንቦት 26/2010 በፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የናሁ ቴሌቪዥን እናት ድርጅት በሆነው ጎልደን ኮፊ ሮስተሪ አመልካችነት በዛሚ ኤፍ ኤም 90.7 ሬዲዮ ላይ በቀረበው አቤቱታ መሰረት የሬዲዮ ጣቢያው እንዲሁም በድርጅቱ ስም ተመዝግበው የነበሩ ሁለት ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ እግድ ማውጣቱ ይታወቃል።
በመሆኑም ሚሚ ስብሃቱ እና ዘሪሁን ተሾመ በዛሚ በኩል እንዲሁም ደረጄ ተክሌ እና አንድ ሌላ ግለሰብ በጎልደን ኮፊ በኩል ሬዲዮ ጣቢያውን በ16 ሚሊዮን ብር ለመሻሻጥ ተስማምተው የነበር ቢሆንም ለዚህም ቅድሚያ ክፍያ ወደ 5 ሚሊዮን ብር ገደማ ለሻጮች በቼክ ተፈፅሞ ነበር። ሆኖም ግን ድርጅቱ ያሉበትን የግብር እዳዎች ፈፅሞ ለመጨረስ እና ከዛም የቀረውን ገንዘብ በመክፈል በአጭር ጊዜ ውስጥ ድርጅቱን ለመረካከብ የተስማሙ ቢሆንም በፊርማቸው ድርጅቱን መሸጣቸውን ያረጋገጡት ግለሰቦች በሚዲያ ወጥተው ድርጅቱ አልተሸጠም የሚል ማስተባበያ በመስጠት እና ውሉንም ለማፍረስ ጥያቄ በመምጣቱ ናሁም ጥያቄውን መቀበሉ ይታወሳል።
ኹለቱም ወገኖች ውል ለማፍረስ ተስማምተው የነበረ ሲሆን ገንዘቡ ሲመለስ ግን ሕጋዊ የባንክ ወለድ ሊሰላበት ይገባል በሚለው ላይ አለመስማማቶች ስለመጡ ወደ ህግ በመሄዳቸው ጉዳዩ እስካሁን በክስ ሂደት ላይ ይገኛል።
ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011



