በሰሜን ሸዋ ዞን ኹለት አዳዲስ ማዕድናት ተገኙ

0
980
  • የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይም ስለማዕድናቱ ማረጋገጫ ሰጥቷል

በሰሜን ሽዋ ዞን በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፊልድስፓር እና ፑሚስ የተባሉ ነጭና አብረቅራቂ ብርሃናማ ቀለም ያላቸው ማእድናት መገኘታቸው ታወቀ። ማእድናቱ ለመስታወት፣ ሴራሚክ፣ ኮምፒዩተር ስክሪን፣ ለላብራቶሪ አገልግሎት የሚያገለግሉ መስታወቶችና ሌሎች ከመቶ ስልሳ በላይ ለሚሆኑ አገልግሎቶች የሚውሉ ናቸውም ተብሏል።

የክልሉ የኢንዱስትሪና የኮንስትራክሽን ማዕድናት ባካሔደው ጥናት ማዕድኖቹን ያገኘ ሲሆን፣ ናሙናቸውም ወደ ኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተልኮ በምርምር ማረጋገጡንም የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ይታየው ተስፋሁን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።

የክልሉ የማዕድን ሀብት ክምችት ዳይሬክተር ደረጀ አሰፋ በበኩላቸው፣ እነዚህ ማዕድናት ፊልድስፓር 10 ነጥብ 2 ካሬ ኪሎ ሜትር እና ፑሚስ 42 ነጥብ 6 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ላይ ጥናት ተካሒዶባቸው በጥናቱ ከተሰበሰቡ 7 የአለት ናሙናዎችን ላይ በተደረገ ጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

ፊልድስፓር በጣሊያን፣ ቱርክ፣ ስፔይን፣ ፖላንድና ራሺያ በብዛት እንደሚመረት ያስታወቁት ደረጀ፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ማዕድኑ በበቂ ሁኔታ ባመገኘቱ ከፍተኛ የሆነ የምርት እጥረት መኖሩን አስታውቀዋል።

“ፊልድስፓር ምርቱ ዝቅተኛ በመሆኑ ዓመታዊ ሽያጩ አንድ ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነው፤ ፑሚስም ያለው የገበያ ድርሻ ተመሳሳይ ነው” ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጠዋል። “የምርት እጥረቱን ተጠቅሞ መሥራት ከተቻለ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ ማስገባት የሚቻል ሲሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታትም የራሱ ሚና ይኖረዋል።”

በተመሳሳይ በክልሉ በምሥራቅ ጎጃም ዞን በጎዛምን ወረዳ 33 ነጥብ 29 ካሬ ኪሎ ሜትር፣ በባሶ ሊበን 33 ነጥብ 78 እና ደብረ ኤሊያስ 28 ካሬ ኪሎ ሜትር የመስክ ጥናት ተከናውኖ፣ ከአካባቢው የተሰበሰቡ 10 የአለት ናሙናዎችም ወደ ላቦራቶሪ መላካቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

“የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ኤጀንሲ የክልሉን የማዕድን ሀብት ክምችት በጥናት በመለየት ልማት ላይ እንዲውል እያደረገ ይገኛል” ያሉት ዳይሬክተሩ በቀጣይ ከ20 በላይ በሆኑ አዳዲስ ማዕድናት ላይ ጥናት ለማድረግ ዝግጅቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

አዳዲስ የተገኙት ማእድናትን ወደልማት ለማምጣት፣ የክልሉን ወጣቶች በማደራጀት፣ የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶችን በመጋበዝ ወደምርት ለመግባት መታሰቡን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በክልሉ ምዕራብ ጎጃም ዞን በወምበርማ ወረዳ ጃምቢ ቀበሌ የኦፓል ማዕድን በመገኘቱ፣ በ6 ካሬ ኪሎ ሜትር ላይ ጥልቅ ጥናት ተጠንቶ ሪፖርት እየተዘጋጀ መሆኑን ያወሱት የክልሉ ማዕድን ሀብት ክምችት ዳይሬክትር ደረጀ፣ ከአጠቃላይ ጥናቱ 70 ከመቶ የሚሆነውን ማጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here