ሜጋ ማተሚያ በ390 ሚሊዮን ብር የማስፋፈፊያ ሥራ እያከናወነ ነው

0
625

ሜጋ ማተሚያ ድርጅት በመቀሌ እና አዲስ አበባ በሚገኙት ማተሚያ ድርጅቶቹ ላይ በ390 ሚሊዮን ብር አዳዲስ የህትመት መሳሪያዎች ግዢ፣ ተከላ እና የህንፃ ግንባታ ሥራዎችን የሚጨምር ማስፋፊያ በማከናወን ላይ መሆኑን ገለጸ።

በአዲስ አበባ የሚገኘው ድርጅት 350 ሚሊዮን ብር የሚሆነውን የሚወስድ ሲሆን በመቀሌ ከተማ ያለው ቅርንጫፍ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ እንደተመደበለት እና የማስፋፊያ ግንባታውንም ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ገ/እግዚአብሔር ሀዲሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በድርጅቱ ሲታተሙ የነበሩ የትምህርት መጻሕፍት ቀለም የሌላቸው ሲሆን በሀገር ውስጥ የመጣውን የፍላጎት ለውጥ መሰረት በማድረግ ለባለቀለም ህትመት ሲባል ወደ ህንድ፣ ቻይና እና ዱባይ ሲሄድ የነበረውን የህትመት ሥራ በሀገር ውሰጥ ለማከናውን የሚያስችል አቅም በማስፋፊያው ለመፍጠር መታሰቡንም ተናግረዋል። የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታየውን የመማሪያ መጻሕፍት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመመጣጠን ከመቅረፉም በላይ መጻሕፍቱን ለማሳተም የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በሀገር ውስጥ ለማስቀረት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ሥራ አስኪያጁ ጨምረው ተናግረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በ2012 መጨረሻ ይጠናቀቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የውጪ ምንዛሬ ዕጥረት ዕቅዶቹን ለማሳካት በድርጅቱ ላይ እክል መፍጠሩን ገልጸዋል። ለአብነትም ከወራት በፊት ከጀርመን ሀገር ከ1.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጥቶባቸው የተገዙ የህትመት መሳሪያዎች በውጪ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ሀገር ውስጥ እንዳልገቡ እና በዚህ ወር ለንግድ ባንክ የ3.2 ሚሊዮን ዶላር ጥያቄ ቀርቦ መልስ አለመሰጠቱን ገልፀዋል።

‹‹ከውጪ ሀገራት ታትመው የሚመጡ የህትመት ውጤቶች ከቀረጥ ነፃ እየገቡ የምርት ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት ቀረጥ መጣሉ፣ የምርት ጥሬ ዕቃዎችን ጥራቱን ጠብቆ እና አሟልቶ የሚያቀርብ ተቋም አለመኖሩ፣ በዘርፉ በበቂ ሁኔታ የሰለጠነ የሰው ኃይል በሚፈለገው ደረጃ አለመገኘቱ እና መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑ ለእድገቱ ውስንነት ምክንያት ነው›› ሲሉ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

በዘረፉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ በድርጅቱ ውስጥ በኦፕሬተርነት እና በጥገና ሥራ ላይ የሚገኙ አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ወደ አውሮፓ እና ቻይና በመላክ አጫጭር ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ለማፋጠን እየተሠራ መሆኑን ገ/እግዚአብሔር ሀዲሽ ተናግረዋል።

ማስፋፊያ ሥራው መቀሌ ላይ መደረጉ መቀሌ የሚገኘው ቅርንጫፍ ከምስረታ ጀምሮ የነበረ እና የክልሉን የህትመት ሥራዎች እንኳን ለመሸፈን አቅም በማጣቱ ማስፋፊያው ማስፈለጉ የተገለጸ ሲሆን በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዳዲስ ማተሚያ ድርጅቶች መከፈታችውን ተከትሎ ወደፊት ማተሚያ ድርጅቶች ባልተስፋፉባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች ቢሮዎችን በመክፈት የማስፋፋት ዕቅድ መኖሩ ተገልጿል።

በ1987 ኢፈርት፣ ጥረት፣ ቱምሳ እና ወንዶ በተባሉት አራቱ የልማት ድርጅቶች የአክሲዮን ባለቤትነት ከ30 የማይበልጡ ሠራተኞችን በመያዝ የተመሰረተው ሜጋ ማተሚያ በአሁኑ ወቅት ከ450 በላይ ሠራተኞችን የሚያስተዳድር ሲሆን በአዲስ አበባ እና መቀሌ የሚከናወኑት የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ የሠራተኞቹን ቁጥር ወደ 600 የማሳደግ ዕቅድ መኖሩን ገ/እግዚአብሔር ሀዲሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 43 ነሐሴ 25 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here