በኢድ አል ፈጥር በዓል ላይ የአድማ በታኝ የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው የፖሊስ አባል ፍርድ ቤት ቀረበ

0
1554

ዕረቡ ሚያዚያ 26 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ በተከበረው የኢድ አል ፈጥር በዓል ላይ በመስቀል አደባባይ አካባቢ የአድማ በታኝ የጭስ ቦንብ በማፈንዳት ወንጀል የተጠረጠረው የፖሊስ አባል በቁጥጥር ሥር ውሎ ፍርድ ቤት ቀረበ።

የፌደራል ፖሊስ አድማ ብተና ዘርፍ አባል የሆነው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ ከትናንት በስቲያ ሰኞ በአዲስ አበባ በተከበረው የኢድ አል ፈጥር በዓል ላይ፤ በመስቀል አደባባይ የሰማዓታት መታሰቢያ ሙዚየም አካባቢ ከፈነዳው የአድማ በታጭ የጭስ ቦንብ ጋር ተያይዞ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 1ኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ ረፋድ ላይ ቀርቧል።

መርማሪ ፖሊስ ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በኢድ አል ፈጥር በዓል ዕለት በተመደበበት ወንጀል የመከላከል ምደባ ላይ እያለ የታጠቀውን አድማ በታኝ የጭስ ቦንብ በአግባቡ መታጠቅ ሲገባው በአግባቡ ባለመታጠቅ የጭስ ቦንቡ እንዲፈነዳና ኹከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር አድርጓል ሲል መርማሪ ለችሎቱ አስረድቷል።

በዚህ በተፈጠረ ኹከትና ብጥብጥ የመንግስትና የግለሰብ ንብረት ጉዳት መድረሱንም አብራርቷል።

በተጠረጠረበት ኹከትና ብጥብጥ ማስነሳት ወንጀል ለተጨማሪ ማስረጃ አሰባስቦ ለመቅረብ 14 ቀን እንዲሰጠው መርማሪው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

ተጠርጣሪው ኮንስታብል አንቡላ ኡቴ በበኩሉ፤ በዕለቱ አስቀድሞ በተመደበበት ቦታ ከለሊቱ 7 ሰዓት ጀምሮ በሥራ ላይ እንደነበር እና በሰዓቱ በቦታው ላይ የነበሩ ሰዎች ቁጥር መጨመርና መጨናነቁን ተከትሎ ከታጠቀው ሦስት አድማ በታኝ የጭስ ቦንብ ውስጥ አንደኛው በማያውቀው ኹኔታ መሬት ላይ ወድቆበት በድንገት መፈንዳቱን ገልጿል።

ሆኖም ምንም አይነት ተንኮልም ሆነ ክፋት በውስጤ አልነበረም ወድቆ ሲፈነዳ እኔ እራሴ ደንግጬ ነበር ሲል እያለቀሰ ሁኔታውን ለችሎቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም ተጠርጣሪው ወላጆቹን በሞት ማጣቱን ገልጾ፤ እህትና ወንድሙን በሱ እርዳታ እያስተማራቸው እንደሆነ እና ከለሊት 7:00 ጀምሮ ለጥበቃ ሥራ ከመሰማራቴ ውጪ ሌላ ክፋት በውስጤ የለም ሲል ለችሎቱ ማብራራቱን ጋዜጠኛ ታሪክ አዱኛ ከችሎት ዘግባለች።

ጉዳዩን የተከታለው ፍርድ ቤቱ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ 14 ቀን የፈቀደ ሲሆን፤ ለግንቦት 10 ቀን 2014 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here